በንጹሃን ዜጎቻችን በተለያየ የሃገራችን ክፍሎች የተፈጸመውን ግዲያ፣ እስራትና መፈናቀል አጥብቀን እናወግዛለን!
ኖቨምበር 2017
በኢትዮጵያ ላለፉት 26 ዓመታት በትረ ስልጣኑን የያዘው ህወሓት/ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ህዝብ ከፋፍሎ ለመግዛት ብዙ ሴራዎችን እንዳሴረ፣ ብዙ ንጹሃን ዜጎችን እንደገደለና እንዳስገደለ፣ እንዲፈናላቀሉ እንዳደረገና እንዳስደረገ ሁላችን የምናውቀው መራራ ሃቅ ነው።
አገዛዙን በበላይነት ሲመራው በነበረው ህወሓት በግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነት ኢህአዴግን ሲመራው የነበረው አቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ በአገዛዙ ውስጥ የነበረው የህወሓት የበላይነት ቀሰ በቀስ ተሸርሽሮ የተለያዩ ቡድኖች እኔ የበላይ ልሁን በማለት በአገዛዙ ውስጥ በሚያካሄዱት የውስጥ ፍትግያ ምክንያት በገጂው ፓርቲ ውስጥ ልዩነት ተፈጥሮ አገዛዙ እስካሁን እንደ አንድ ቡድን የቀጠለው የከፋፍለህ ግዛ አካሄድ እንደ ቡድን ሊያስቀጥል የማችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ እያንዳንዳቸው እንወክለዋለን ከሚሉት ብሄረሰብ ጉያ ውስጥ በመወሸቅ እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ብሄረሰቦች መካከል አይተነውና ሰምተነው የማናውቅ ዓይነት ብሄረስብን ከብሄረሰብ ጋራ በማጋጨት ከዙሪያቸው ለማሰባሰብ ሩጫ ላይ ናቸው።
ይህ ሩጫ ከምንጊዜም በላይ ባሁኑ ጊዜ አይሎ ቀጥሎ እነሱ ራሳቸው በለኮሱት ግጭት ዛሬ በተለያየ የሃገሪቱ ክፍሎች በብሄረስቦች መካከል የተለያየ ግጭት ተከስቷል፣ በተከሰተው ግጭትም የበርካታ ንጹሃን ዜጎች ህይወት ተቀጥፏል፣ ብዙዎች ታስረዋል፣ ተፈናቅለዋል።
በዚህ ባሳለፍነ ከሁለት ወር በማይበልጥ ጊዜ ብቻ አገዛዙ በውስጡ በሚያደረገው የስልጣን ስሽኩቻና አንዱ ቡድን ሌላውን አንበርክኮ የበላይ ለመሆንና እወክለዋለሁ በሚለው ብሄረሰብ ጉያ ለመወሸቅ በሚደረገው ሩጫና በተለያዩ በጥላቻ በታወሩ ጽንፈኞች በሚራገበው የጥላቻ ፕሮፓጋንዳና ድርጊት በሃገሪቱ የተለያየ አከባቢዎች እስከዛሬ ታይተውና ተሰምተው የማይታወቁ በዘር ላይ የተመሰረቱ የህዝብ ለህዝብ ግጭቶች ተከስቶ ከባድ የርስበርስ ፍጅትና መፈናቀል በሃገራችን የተለያዩ አከባቢዎች ተከስቷል፣ ከነዚህ ዋና ዋናውቹን ለመጥቀስ፣
ሀ. ኦሮሞንና የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሄረሰቦች መካከል የክልል ደንበር እንደ ምክንያት በማድረግ የህወሓት ቡድን የኦህዴድ ቡድንን ለማንበርከ የሶማሌ ክልል ባለስልጣናትና ልዩ የአከባቢ ጥበቃ ሃይል በመጠቀ በሶማሌ ክልል ሲኖሩ በነበሩ የኦሮሞ ብሄረሰብ ወገኖቻችን ላይ በከፈተው መጠነ ሰፊ ዘመቻ በርካታ ንጹሃን ኦሮሞ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ተገድለዋል፣ ቆስለዋል፣ እጅግ ብዙዎችም ተፈናቅለዋል፣ በውል የማይታወቅ ንብረትም ወድሟል። እንዲሁም ይህን በሶማሌ ክልል ሲኖሩ በነበሩ ኦሮሞዎች ላይ የተወሰደውን ፍጅትና መፈናቀል እንደ ምክንያት በማድረግ በጽንፈኛ ኦሮሞዎች በተደረገው ቅስቀሳና በጽንፈኛ ኦሮሞዎች በኦሮሞ ክልል በአንዳንድ አከባቢ ሲኖሩ በነበሩ ሶማሌ ኢትዮጵያዊያን ላይ በተወሰደው የጅምላ እርምጃም ንጹሃን የሶማሌ ብሄረሰብ ወገኖቻችን ተገድለዋል፣ ቆስለዋል፣ ተፈናቅለዋል።
ለ. የኦሮሞ ህዝብ ከኣምባገነኑ የጭቆና አገዛዝ ነጻ ለመውጣት በሚያደርገው ሰላማዊ ትግል መካከል በተሰገሰጉ የኦሮሞ ጽንፈኞች በኢሉባቦር ዞን በሶስት ቀበሌዎች ለብዙ ዓመታት በሰላም ሲኖሩ በነበሩ አማራና ተጋሩ ወገኖቻችን በወሰዱት በዘር ላይ ያነጣጠረ አረመኔያዊ እርምጃ አማሮችና ተጋሩ ተገድሏል፣ ብዙዎች ተፈናቅለዋል፣ ንብረታቸም ተዘረፈዋል፣ወድሟል።
ሐ. ምንም ብረት ሳይታጠቁ ለነጻነታቸው በሰላማዊ መንገድ የታገሉ የኦሮም ወጣቶች እስከ አፍንጫው በታጠቀ የኢትዮጵያ ሰራዊት በአምቦ ከተማ ተገድለዋል፣ ተድብድበዋል፣ቆስለዋል፣ ታስረዋል።
መ. በበነሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማሺ ዞን በርካታ ንጹሃን የአማራ ወገኖቻችን አማራ በመሆናቸው ብቻ በዞኑ ባለስጣናት በተመራው የአከባቢ ታጣቂዎች ተገድለዋል፣ ቤታቸው ተቃጥሏል፣ ንብረታቸው ተዘርፏል፣ ብዙዎቹም ተፈናቅለዋል።
ሠ. በሚድያ ብዙ ያልተወራለት በደቡብ ትግራይ በራያ ተጋሩና በአፋር መካከልም በተለያየ ጊዜ በተፈጠረው ግጭት ንጹሃን ተጋሩና አፋር ወገኖቻችን ተገድለዋል፣ ተፈናቅለዋል።
ረ. በወሎ በአፋርና በአማራ መካከልም ሚዲያ ያልዘገበው የርስበርስ ግጭት ምክንያት ንጹና አማራና አፋር ወገኖቻችን እየተገደሉና እየተፈናቀሉ ናቸው. . . . ።
ስለሆነም ካሁን በፊት በተለያየ ጊዜ በህዝባችን ላይ ጥፋት ሲፈጸም እንደምናደርገው ሁሉ አሁንም እኛ በበተለያየ ክፍለዓለም በስደት የምንኖር ተጋሩ ኢትዮጵያዊያን ከላይ የዘረዘርናቸው በአገዛዙና በጥላቻ በታወሩ ጽንፈኛ ቡድኖች አማካይነት በተለያዩ አከባቢዎች በንጹሃን ዜጎቻችን ላይ የተፈጸመ ግድያ፣ መቁሰልት፣ እስራት፣ መፈናቀልና የንብረት ዝርፊያና ውድመት አጥብቀን እናወግዛለን።
ከዚህ ጋራ በማያያዝም ለሞላው ሃገርና ህዝብ ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ቀጥሎ የተቀመጠው አጭር መልእክታችን ለማስተላለፍ እንወዳለን፣
1. ስለ ሃገራችንና ህዝቧ ከግል ስልጣኑና ጥቅሙ ውጭ ምንም ሃላፊነት በማይሰማው በህወሓት በሚመራው የኢህአዴግ አገዛዝ ምክንያት አንዣብቦ ያለውን ከባድ አደጋ ተባብረን ማምከን ጊዜ የማይሰጥ የሁላችን ተቀዳሚ የቤት ስራ ሆኗል። ለዚህ አሁን ደርሰንበት ላለነው ትልቁ አደጋ ዋናው ምክንያት የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ስለሆነ ዛሬ ከምን በላይ ይህን አገዛዝ በጋራ ትግል አስወግደን ሁሉም ብሄር ብሄረሶቿ በእኩልነት ተከባብረው የሚኖርቡት ሉዓላዊትና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ከህወሓት/ኢህአዴግ መወገድ በኋላ ለመመስረት ከብሄር ሆነ ድርጅት ጎጆአችን ወጥተን ኢትዮጵያንና ህዝቧን ማየት የምንችል ዜጎች አገዛዙን በጋራ ማስወገድ ትልቁ የቤት ስራችን ሆኗልና ይህን የቤት ስራችንን በጋራ እንስራ።
2. ኢትዮጵያ የምትባል ለብዙ ዘመናት የኖረች የጋራ ቤታችን እንድትቀጥል ከፈለግን እስካሁን ለ27 ዓመታት በተናጠል ወይም በተለያዩ ትንንሽ ቡድኖች የተጓዝነው ጉዞ የትም እንዳላደረስን በግልጽ አይተናልና ሃገራችንና ህዝቧን ከህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ለመታደግ የምንፈልግ በጋራ መምከርና መስራት ነገ ሳይሆን ዛሬ እንጀምር።
3. ሃገርንና ህዝብን በከዱ ለፍርድ መቅረብ የሚገባቸው ከጅምሩ ጀምሮ የጥላቻ ፖለቲካ ጠንሳሾችና አራማጆች በሆኑት በነ ስብሓት ነጋ፣ ዓባይ ጸሃየና ስዩም መስፍን ዓይነት መሰሪዎች መሪነት በተነዛውና አሁንም እየቀጠለ ባለው የጥላቻ ፖለቲካ ሳንጠመድ ሀገርና ህዝብን ማእከል አድርገን ተመልክተን፣ ከድርጅትና ብሄረሰብ በፊት ሃገርንና አጠቃላይ ህዝቧን አስቀድመን ፣ በህዝብና በፖለቲካ ድርጅት መካለል ያለውን ግዙፍ ልዩነት በግልጽ አይተንና ለይተን አስቀምጠን፣ አሁን አገዛዙ ባቀጣጠለው እሳት ላይ በንዚን ከማርከፍከፍ ተቆጠብን፣ በምንችለው አቅም ሁሉ አንዱን ብሄረሰብ ከሌላው ብሄረሰብ ጋራ በሚያፋቅርና በሚያቀራርብ ስራ ላይ አተኩረን እንስራ።
4. ለሁላችንም መከራ ምክንያት(Cause) የሆነው የህወሓት/ኢህ አዴግ አገዛዝ ከተወገደ በኋላ ሁላቸው ጉዳዩ ያገባናል የሚሉ ሃይሎች ያለ አንዳች ማግለልና አድልው የሚሳተፉበት የሽግግር ሂደት ምን መመሰል እንዳለበት ካሁኑኑ በጋራ መነጋገር እንጀምር እንላለን።
ኢትዮጵያና ህዝቦቿ በተባበረ ትግል ከህወሓት/ኢህ አዴግ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት በጋራ እንታገል!!!
በተለያየ ክፍለዓለማት በስደት የምንኖር ተጋሩ ኢትዮጵያዊያን።