ኢትዮጵያ ያለው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ የ14 ቀን ጸሎተ ምህላ እንዲታወጅ ወሰነ

ኢትዮጵያ ያለው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ የ14 ቀን ጸሎተ ምህላ እንዲታወጅ ወሰነ

/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ ምልዓተ-ጉባኤውን ሲያጠናቅቅ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ስለ ተከሰተው ግጭትና ስለደረሰው ጉዳት በመነጋገር፤ ከሚቀጥለው ሰኞ ጀምሮ ለ14 ቀናት ጸሎተ ምህላ በመላ ሀገሪቱ ባሉ ገዳማትና አድባራት እንዲካሄድ ወሰኗል።

ሰሞኑን በተለያየ ምክንያት በወገኖቻችን መካከል የተከሠተው ግጭት በአስቸኳይ ተወግዶ ሰላም እንዲሰፍንም ለማድረግ ከመንግስት ጋር ውይይት እንዲደረግ እንደሚሰራ የሲኖደሱ መግለጫ ያመለክታል።

በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖችም ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ባለው መዋቅር የስድስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንዲደረግ ሲኖዶሱ መስማማቱ ታውቋል። የኢትዮጵያ ህዝብ የመቻቻል፣ መከባበር፣ መደማመጥና የመግባባት መንፈስን በማጎልበት በአንድነት ተባብሮ እንዲኖርም ጥሪ ተላልፏል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጸሎተ ምህላ እንዲካሄድ ማወጇን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው። ላለፉት 26 ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ በገፍ ሲገደልና ሲታሰር የመንግስት አጋር በመሆን የህዝብን ሰቆቃ በዝምታ ማለፏን በመጠቀስ አሁን የሚደረገው ጸሎተ ምህላ በቤተክርስቲያኗ ዶግማና ቀኖና ሳይሆን በመንግስት ይሁንታ ላይ የተመሰረተ ነው በማለት አንዳንድ ወገኖች ትዝብታቸውን እያካፈሉ ነው።

የ1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ የኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ ስርዓት በዜጎች ላይ የፈጸመውን የጅምላ ግድያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዝምታ ማለፏን እንደምሳሌነት ማንሳት ተገቢ ነው የሚሉ ወገኖች በ2000 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የአካዳሚ ነጻነት በመጠየቅ ባነሱት ተቃውሞ የመንግስትን ወታደራዊ እርምጃ በመሸሽ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተጠለሉ ተማሪዎችን አሳልፋ መስጠቷ በብዙዎች ዘንድ ቅዋሜ ቀስቅሶ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

LEAVE A REPLY