በባህርዳር ከተማ ጫት በየቦታው እንዳይቃም ተከለከለ

በባህርዳር ከተማ ጫት በየቦታው እንዳይቃም ተከለከለ

/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ የከተማዋ ኮምንኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ በሰላም ይመኑ ለአማራ ብዙኃን መገኛኛ ድርጅት እንደገለፁት ከጫት ጋር ተያይዞ ህገ-ወጥ ንግድ ቤቶች ተስፋፍተዋል፡፡ ከባህል የራቁ እንቅስቃሴች በርክተዋል፡፡ የጫትም አሉታዊ ጎን በወጣቱ ላይ እየሰፋ በመምጣቱ ጫት በየቦታው እንዳይቃም ተከልክሏል ብለዋል፡፡

የከተማዋን ዓለም አቀፋዊነት እና የቱሪስት ማዕከልነት ለማበልፀግ በሚደረገው እርምጃም ጫት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡ በመሆኑም ጫት በየቦታው እንዳይቃም የከተማ አስተዳደሩ ባወጣው ደንብ እና ሀገሪቱ በምትመራበት ህግ መሰረት ተደርጎ ጫት በየቦታው እንዳይቃም መከልከሉን አቶ በሰላም ለአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል ባልተለመደ ሁኔታ ከአንድ ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በጫት መሸፈኑንም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዚህም በወጣቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ይነገራል።

የባህርዳር ከተማ አስተዳድር በዚህ ሳምንት ጀምሮ ጫት በየቦታው እንዳይቃም የከለከለ ሲሆን የአማራ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን በጫት ላይ 5 በመቶ ተጨማሪ ታክስ በመጣል ጫት መቃም እንዳይበረታታ ለማድረግ እሰራለሁም ብሏል፡፡

የጫት ገበያም በውስን ቦታዎች ብቻ እንደሚሆን ተገልጿል። በክልሉ ከሚመረት ጫት ውስጥ 20 በመቶ ብቻ ወደ ውጭ እንደሚላክ ከገቢዎች ባለስልጣን የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡በመሆኑም ክልሉ ከጫት ተገቢውን ገቢ እያገኘ አይደለም፡፡ይልቁንም የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ እንደሚለው የጣና እና የአባይ አካባቢዎችን ውሃ በመሻማት የክልሉን የማምረት አቅም እየቀነሰው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ከአፍሪካ ሀገራት ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ በከፊል ኬኒያ ጫት መቃም ህጋዊ የሆነባቸው ሀገራት ናቸው፡፡ የሶማሊያ ወታደር ጫት ሲቅም በአልሸባብ በራሱ መሳሪያ እንደሚገደልና ጫት ለሶማሊያ አለመረጋጋት የራሱ አሉታዊ አስተዋፅዖ እንዳለው ይነገራል፡፡ለየመንም እንደዚሁ፡፡

በየመን 40% ውሃዋ ለጫት ይውላል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ1972 ጫትን ጎጂ እፅ ብሎ ከፈረጀው በኋላ በአውሮፓና አሜሪካ ተከልክሏል፡፡ በርካታ የአረብ ሀገራት መንግስታትም ጫት መቃምን አውግዘዋል። በሳውዲ አረቢያና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጫት ሲቅሙ መገኘት በህግ ያስጠይቃል።

LEAVE A REPLY