/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ የሚመራ የልዑካን ቡድን ከነገ ወዲያ ቅዳሜ ወደ ባህር ዳር ከተማ ሊያመራ መሆኑን ተነገረ።
የልዑካን ቡድንም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ከ250 በላይ ሰዎችን ያካተተ መሆኑ ታወቋል። ይህን ዜና ይፋ ያደረገው የባህር ዳር ከተማ የወጣቶች ፌዴሬሽን “የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ለማ መገርሳ ወደ ባህር ዳር ከተማ እንደሚመጡ ሲሰሙ እጅግ ደስ እንዳላቸውና ከተፈቀደ ለክብራቸው መድፍ ተኩሰው፣ ካልሆነ ደግሞ ጨፌ ጎዝጉዘው በደስታ ለመቀበል ሽር ጉድ እያሉ መሆኑን ገልጸዋል። ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ “የአንድነት አቀቃኝ” ሲሉም አሞካሽተዋቸዋል።
“ከሁለት ሳምንት በፊት የእንቦጭን አረም ለማስወገድ ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ ከ200 በላይ ወንድሞቻችንን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለን በደስታ ተቀብለን አስተናግደን ላደረጉልን ወንድማዊ ድጋፍ ከልብ አመስግነን በሰላም ግቡ ብለን ሸኝተናቸዋል፡፡ ክቡር ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ አባ ገዳዎችንና የሀገር ሽማግሌዎችን በክብር ተቀብለን ለማስተናገድ ዝግጅታችንን አጠናቀናል፡፡” በማለት የከተዋ የወጣቶች ፌዴሬሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
የኦሮሚያ ክልል የወቅቱ ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ለማ መገርሳ ከሁለት ዓመታት በፊት በክልሉ በተፈጠረው ህዝባዊ እቢተኝነት እየተፋፋመ በመምጣቱ የአቶ ሙክታር ከድር አስተዳድርን በማፍረስ ከአንድ ዓመት ፊት ነው መንበረ-ስልጣኑን የተቆጣጠሩ።አቶ ለማ መገርሳ የኢትዮጵን ህዝብ በማስገደልና በማሳሰር ግንባር ቀደም ተዋናይ ነው በሚባለው ደህንነት መስሪያ ውስጥ ለረጅም ዓመታት ሰርተዋል።
የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ከሆኑ ወዲህ ደግሞ የህወሓት ባለስልጣናትን የማያስደስት ከተለመደው አካሄድና አሰራር ወጣ በማለት በየ መድረኩ በድፍረት ሲናገሩ ይደመጣሉ።እሳቸው የሚመሩት ኦ.ህ.ዴ.ድም ስለ “ኢትዮጵያ አንድነት” በማቀንቀኑና የህወሓት አባላት በኦሮሚያ ክልል እንደፈለጉ መቀሳቀስ ባለመቻላቸው በግልጽ የሚታይ አለመግባባት እንደተፈጠረ የሚያመላክቱ በርካታ ምልክቶች ይስተዋላሉ። የፓርላማው አፈ-ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ “ህዝቤና ድርጅቴ ክብሩ ተነክቷል” በማለት ከሀላፊነታቸው ለመልቀቅ እንደወሰኑ ባለው ወር በይፋ መግለፃቸውም የሚታወቅ ነው።
የአሁኑ የፕሬዚዳንቱ የባህር ዳር ጉዞ ዓላማ በግልጽ የተባለ ነገር ባይኖርም ከአማራ ህዝብና ከብሄረ አማራ ዴሞክራሲዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ጋር ያለውን የወዳጅነት መንፈስ የበለጠ ለማጎልበት ሊሆን እንደሚችልና ይህም ለ26 ዓመታት ሀገሪቱን በበላይነት ሲገዛ ለኖረው ህወሓት መልካም ዜና ሊሆን እንደማይችል አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።