ከባሕር ዳሩ የአማራ-ኦሮሞ ሕዝቦች የምክክር መድረክ አንደበት! /መላኩ አላምረው/

ከባሕር ዳሩ የአማራ-ኦሮሞ ሕዝቦች የምክክር መድረክ አንደበት! /መላኩ አላምረው/

“የአማራ እና የኦሮሞ ትልቅ ሐይቅ ነው፡፡ በሐይቁ ውስጥ ያሉ ሌሎች ነገሮች ሊረብሹን አይገባም፡፡

በኦሮሚያ ክልል አንድ አማራ ወንድ እና ኦሮሞ ሴት ተጋቡ፡፡ ወንድየው ኦሮምኛ አይችልም፡፡ ሴቷም አማርኛ አትችልም፡፡ ግን በመንፈስ ተግባቡ እና ተጋቡ፡፡ ተጋብተው የሁለቱንም ቋንቋ ተመማሩ፡፡ ሰው እንኳንስ በቋንቋ በመንፈስ ይግባባል። ይህ የሆነው ዛሬ አይደለም፡፡ ከ 50 ዓመት በፊት ነው፡፡ እና አማራ እና ኦሮሞ ህዝቦች እንዲህ ናቸው፡፡ በመካከላችን ማንም አይገባም፡፡ አንድ ነን፡፡”
(አንድ የኦሮሞ አባገዳ ከተናገሩት፡፡)


“የአማራ ተወላጆች ከአማራ ክልል ቀጥሎ በኦሮሚያ ይኖራሉ፡፡ የኦሮሚያ ተወላጆችም በአማራ ክልል ይኖራሉ፡፡ የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነትት ሊነጣጠል የሚችል አይደለም፡፡ ሁለቱን ሕዞቦች ለመነጣጠል አንዳንድ አካላት ጥረት ቢያደርጉም፣ የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት በደም የተሳሰረ በመሆኑ አልተሳካም፡፤ አይሳካምም፡፡ ጥላቻችን የሚናፍቁ ሁሉ አይሳካላቸውም፡፡ ፍቅርን ለትውልድ እናወርሳለን፡፡ የእኛ አንድነት ለሎሌችም ምሳሌ ነው፡፡
አንድነታችን በዘላቂነት ይቀጥላል፡፡”
(አቶ ገዱ አንዳርጋቸው!)


“የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነሳ የኦሮሞው ታሪክ የመገንጠል ሆኖ በውሸት ተቀርጿል፡፡ ኦሮሞ መገለጫው አብሮነት እና አንድነት እንጅ መገንጠል አይደለም፡፡ ‘ሞጋሳ’ እና ‘ጉድፊቻ’ ለዚህ ማሳያዎች ናቸው፡፡ አማራውም አንድነትን ወዳጅ ህዝብ ነው፡፡ ስለዚህ አማራ እና ኦሮሞ ተመሳሳይ ስነ-ልቦና አላቸው፡፡ የሁለቱ አንድነትና መግባባት ደግሞ ለኢትዮጵያ ትንሣኤ ልዩ ምዕራፍ ይከፍታል”።
(ዶክተር ብርሃኑ ለሜሶ – ጥናት አቅራቢ)፡፡


“የኦሮሞና የአማራ 19ኛው እና 20ኛው ክፍለ ዘመን ታሪክ በትክክል አለመፃፉ የፈጠረው ክፍተት የአማራውን ገዥ መደብ እና የአማራውን ህዝብ አንድ የማድረግ፣ እንደጨቋኝ መቁጠርና የህዝቡን መስተጋብር መሰረት ያላደረገ የልሂቃን የፖለቲካ ንትርክ የሁለቱን ህዝቦች አንድነት ሸርሽሮት ቆይቷል፡፡ ያለፈውን የተዛባ ትርክት መሰረት አድርጎ የብሔር ጭቆና አለ ብሎ ማሰብ የሁለቱን ብሄሮች አንድነት አሳስቷል፡፡
ስለዚህም ለወደፊቱ፥

—> ቋሚ የባህል ልውውጥ ማድረግ፣ የአማራ እና የኦሮሞ የጋርዮሽ ጊዜ መመደብና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠንከር፡

—> የሁለቱም ቋንቋዎች ትምህርት በሁለቱም ክልሎች ማካሄድ፡ አማርኛን በኦሮሚያ ማጠናከርና በአማራም ኦሮመኛን ማስተማር፤

—> ጠባብ እና ትምክህተኛ የሚሉ የፖለቲካን ቃላትን ማጥፋት፡ (እነዚህ ቃላት
በሁለቱ ህዝቦች ማንነት ላይ የወደቁ መስለዋል… መገለጫ ከሆኑም ግለሰባዊ መሆን ነበረባቸው፡፡ ማህበረሰብን አይገልፁም)።

—> የሁለቱም ሊሂቃን እና የፖለቲከኞች የአንድነት ሚና መጫዎት እና የፖለቲካ
ምህዳሩን ማስፋት፤

—> የመሰረተ ልማት ትስስርና የኢኮኖሚ ህብረት በመፍጠር የሁለቱን
ህዝቦች አንድነት ማጠናከር፤
ተገቢነት ያላቸውና ተፈፃሚ ሊሆኑ የሚገቡ እርምጃዎች ናቸው፡፡”
(ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው – የአአዩ ታሪክ ተመራማሪ/ጥናት አቅራቢ)


“መልካም ስራ ሰርተን ካስተማርነው ትውልዱ የዘራንበትን ነው የሚያበቅለው፡፡ በመልካም ሰብል ውስጥ የሚቀላቀለው ቀሪው እንክርዳድ ቆይቶ ይወገዳል፡፡ በመሆኑም ትውልድን መቅረጽ የመንግስትም የአባቶችም ሊሆን ይገባል፡፡

ትውልድን መቅረጽ ሀገርን መቅረጽ ነው፡፡ በእናት እና በሀገር ቀልድ ስሌለ ለሀገራችን እኩል መቆም አለብን”
(ከአማራ የሃይማኖት አባቶች)

ምንጭ: አማራ ብዙኃን መገናኛ

LEAVE A REPLY