ግልጽ ደብዳቤ ለዶ/ር ፀጋዬ ረጋሣ አራርሣ /ከአዲስ ጀምበር/

ግልጽ ደብዳቤ ለዶ/ር ፀጋዬ ረጋሣ አራርሣ /ከአዲስ ጀምበር/

አስቀድሜ የተለመደውን ኢትዮጵያዊ ሠላምታ ላቅርብ ፤ የጽሑፉ ትኩረት የሆንከው ዶ/ር ፀጋዬ ረጋሣ አራርሣ ከኦሮሞ አባት እና ከአማራ እናት መወለድክን፣ ከትግራይ ሴት ጋር መጋባትህን መረጃዎች ያመለክታሉ። የውልደት ውጤት የሆንከው ዶ/ር ፀጋዬ ምርጫ የለህም እና ይህንን ማንነት ይዘህ ትቀጥላለህ። ከዚህ ውጪ ከሕይወህ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለምሳሌ ጋብቻ፣ ዕምነት፣ ፖለቲካ… ወዘተ በተመለከተ በፍላጎትህ እና በምርጫህ ትወስናለህ ።

ስለ አንተ ምንነት እና ማንነት ለመናገር ወይም ለመጻፍ አመታት ይፈጃል ፣ ያን ያህል ፈጅቶም አንተን አገኘሁህ ፣ አወኩህ ማለት ያስቸግራል ያም ሆኖ ስለማንነት፣ ስለአማርኛ ቋንቋ እና ስለአማራ እና ትግሬ መጤነት ከተናገርካቸው ላይ በማተኮር ትንሽ ልበል። የምለው ሁሉ ከራሴ ፍላጎት ወይም ስሜት ወጥቼ ከራስህ አባባል እና የተመዘገቡ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ ነው።

1.ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም ዶ/ር ፀጋዬ መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ ብለሃል፤ መታወቅ ያለበት እንደማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ፀጋዬም መጀመሪያ ሰው ነው፣ ይህንም ያገኘው ከኦሮሞ አባቱ እና ከአማራ እናቱ ነው። ይህ ዕውነታ በዶ/ር ፀጋዬ ፍላጎት የሚቀየር አይሆንም፣ እሱ ግን ተፈጥሮውን ቀይሬዋለሁ እያለ ነው። ከሁለት ብሔረሰብ አባላት መወለዱ የሚቆጨው ዶ/ር ፀጋዬ በራሱ ላይ የደረሰውን እና የማይመቸውን በልጆቹ ላይ እንዲደርስ ወዶ እና ፈቅዶ የትግራይ ሴት አገባ። በነገራችን ላይ የዶ/ር ፀጋዬ ልጆች ልጆቹ እንጂ ዶ/ር ፀጋዬ ባለመሆናቸው በራሳቸው መንገድ ማንነታቸውን እንደሚያገኙ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

የተፈጥሮ ማንነትን መቀበል ያቃተው የፈለገውን ማንነት የመረጠ ያልፈለገውን የተወዎ ፣ በራሱ ላይ እንዲደርስ የማይፈልገውን በልጆቹ ላይ እንዲደርስ የፈቀደው፣ ለራሱ ክብር መቆም ያልቻለው፣ በአጠቃላይ በማንነት ውዥንብር ውስጥ የገባው ዶ/ር ፀጋዬ ወደ አደባባይ ወጥቶ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ላስተምር፣ ልናገር፣ ጥብቅና ልቁም፣ ላደራጅ፣ ልምራ፣ ነፃ ላውጣ ቢል የሚነሳበትን የተአማኒነት፣ የአቋም ፣ የዓላማ ፅናት፣ ወገንተኝነት ፣ ሚዛናዊነት ፣ የሙያ ሥነ ምግባር፣ የሞራል ብቃት፣ ሕዝባዊነት፣ የመርህ… ወዘተ ጥያቄዎችን የተገነዘበ አይመስልም ። ዶ/ር ፀጋዬ ኢትዮጵያዊ ማንነት የሚባል የለም፣ መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ፣ ኦሮሞነት የማንነት መገለጫዬ ነው፣ ኢትዮጵያ ሀገሬ ናት ብሏል። ከዚህ አነጋገር መረዳት የሚቻለው ዶ/ር ፀጋዬ ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም ብሎ ተነስቶ አለ ብሎ እንደደመደመ ነው።

ዶ/ር ፀጋዬ ኢትዮጵያ ሀገሬ ናት ካለ ኢትዮጵያ ሀገሬ ናት የሚል ሁሉ ዶ/ር ፀጋዬን ጨምሮ ኢትዮጵያ የምትባል የጋራ ሀገር አላቸው ማለት ነው ፣ ሀገር የጋራ ማንነት መነሻ እንደመሆኑ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን የመጀመሪያው የጋራ ማንነት መገለጫቸው ናት ። አገራዊ ማንነት የተወሰነ ወርድ እና ስፋት ያለው ጉዳይ ሳይሆን ከዜግነት ከእኩል መብት እና ግዴታ ፣ ከዲሞክራሲ ፣ ከፍትህ ፣ ከእኩልነት ፣ ከነፃነት ፣ ከውክልና … ወዘተ ጋር ተያይዞ በሚዳብር የጋራነት የአገራዊ ማንነት ይዘት እየተሟላ ይሄዳል ። ኢትዮጵያዊ ማንነት መኖሩ ግልጽ ነው ፣ጥያቄው ያለው ኢትዮጵያዊ ማንነት የሁሉንም ፍላጎት ያስተናግዳል አያስተናግድም የሚለው ነው ። ይህም በመነጋገር መስተካከል የሚችል ጉዳይ ነው።

አገራዊ ማንነት ከመንግሥት አወቃቀር ፣ አደረጃጀት እና አሠራር ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም ፣ በሕዝብ መካከል ሰፊ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የአግድሞሽ ግንኙነት አለ ፣ ይህ ግንኙነት የቋንቋ እና የባህል መወራረስን ፣ የእርስ በርስ ጋብቻን ፣ እንደ እድር ፣ እቁብ … የመሳሰሉ ማህበራት ምሥረታን ያስከትላል ፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ በረጅም ጊዜ የጋር ማንነት እና ሥነልቦና ይፈጠራል ፣ ይዳብራል ።

2. አማራ እና ትግሬ መጤዎች ናቸው አማራ እና ትግሬ መጤዎች ናቸው ፣ አይመቹኝም ፣ የአቢሲኒያ ኢምፓየር መሠረት እንደመሆናቸው ለደረሰው ሁሉ ተጠያቂ ናቸው ይላል ፣ የዶ/ር ፀጋዬ የመጀመሪያው ሥህተት አገዛዝ እና ሥርዓትን ከሕዝብ መለየት አለመቻል ሲሆን ፣ ሁለተኛው ስህተት የገዢዎች ፍላጎት መግዛት እና ማስገበር እንደመሆኑ አልገዛም አልገብርም ባለው ላይ ዱላው በቅድሚያ የሚያርፈው በአካባቢው ሰው ላይ መሆኑን ካለመረዳት አማራን እና ትግሬን የሥራዓቱ ተጠቃሚ እና ተጠያቂ እንደሆኑ አድርጎ ያቀርባል ። ሥልጣን በተለያዩ አደረጃጀት በየአካባቢው ይፈጠራል ። የሥልጣን መገለጫ የጎበዝ አለቃ ፣ ንጉሥ ፣ ሱልጣን ፣ አባ ገዳ ፣አሚር…ወዘተ ሊሆን ይችላል።

ሁሉም የበላይ ለመሆን ስለሚፈልጉ ግጭት ይፈጠራል ፣ አቅም ያለው ሥልጣን ይጠቀልላል። ይህ የሥልጣን መነጣጠቅ ጉዞ ከአክሱም ንጉሥ ኢዛና ጀምሮ ወደ ዮዲት ጉዲት ፣ ዛጉዌ ሥርወ መንግሥት መልሶም ወደ ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት ፣አህመድ ግራኝ እያለ ወያኔ እጅ ገባ። በሌላ በኩል በገዳ ሥርዓት ላይ የተመሠረተው የኦሮሞ የሥልጣን ፍላጎት እንቅስቃሴ ከደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ሰሜን እና ምዕራብ ኢትዮጵያ ከ16ኛው መ.ክ. ዘ. ጀምሮ ይደረግ ነበር።

ይህ ጉዞ የተለየ ቅርጽ እና ይዘት ቢኖረውም የመጨረሻ ግቡ መግዛት ማስገበር ነው ። በተጨማሪም ከምሥራቅ ኢትዮጵያ ወደ መሀል ሀገር እና ሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው የአህመድ ግራኝ የልግዛ ላስገብር ጦርነት እንደ ሌሎቹ የሥልጣን ሽሚያዎች ተመሳሳይ ባህሪ ያለው ነው ። በሁሉም የሥልጣን ሽሚያ ጉዞ ብዙ ሕይወት ጠፍቷል ፣ ንብረት ወድሟል ፣ ሕዝብ ተፈናቅሏል ፣ አዲስ የሕዝብ አሰፋፈር ተፈጥሯል ፣ ዛሬ በኢትዮጵያ የሚታየው የሕዝብ አሠፋፈር የሁሉም የሥልጣን ሽሚያ ጉዞ እና በየአቅጣጫው የተደረገ ፍልሰት ውጤት ነው ። ዶ/ር ፀጋዬ አፉን ሞልቶ አማራ እና ትግሬ መጤዎች ናቸው ይላል ። ሰው በሀገሩ እንዴት መጤ ይሆናል ? ዛሬ የሚታየው የኢትዮጵያ የሕዝብ አሰፋፈር ከሞላ ጎደል የዘመናት የሕዝብ የሀገር ውስጥ ፍልሰት ውጤት መሆኑ እየታወቀ እንዴት አንዱ መጤ ሌላው ነባር ይሆናል ? በአንድ ሀገር ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ሕዝብ ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳል ፣ ይፈናቀላል ፣ ይሠፍራል ፣ ይኖራል ፣ ችግሩ ከአለፈ በኋላ በመረጠው ሕይወቱን ያስቀጥላል ፣ ይህ አባባል ከሰሜን ወደ ደቡብ ፣ ከደቡብ ወደ ሰሜን እና ከምሥራቅ ወደመሐል ሀገር እና ሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገውን እንቅስቃሴ በእኩልነት ይመለከታል ። በዚህ ሁኔታ አማራን እና ትግሬን ነጥሎ መጤ ማለት ሚዛን ያልጠበቀ ፣ተጨባጭ ሁኔታውን ያላገናዘበ ፣ ከሙያ ሥነምግባር የወጣ ፣ጭፍን ስሜታዊነት እና ወገንተኝነት ነው ። የኦሮሞ መስፋፋት ኦሮሞን ከደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ እስከ ሰሜን መዕራብ ኢትዮጵያ ጫፍ አድርሶታል፤ለምሳሌ በደቡብ ጎንደር የጋራ ጀልዱ ፣ በጎጃም የኢልማ እና ዴንሳ ፣በወሎ የራያ ፣ በሰሜን ሸዋ የከሚሴ ኦሮሞዎች በሀገራቸው ኢትዮጵያ እንደማንኛውም ነዋሪ በእኩልነት ስለሚኖሩ አንድም ቀን መጤ ተብለው አያውቁም ። 3. አማርኛ ቋንቋ በዕቅድ ፣ በሕግ ድጋፍ ነው የሥራ ቋንቋ የሆነው ዶ/ር ፀጋዬ ፣ አማርኛ የመንግሥት የሥራ ቋንቋ የሆነው በአጋጣሚ ሳይሆን በዕቅድ ፣ በአዋጅ ፣ በሕግ እና በተቋም ተደግፎ እንደሆነ ይናገራል ። አሁንም እውነቱን ከመረዳት ፍላጎቱን እና ስሜቱን አስቀደመ ፣ አማርኛ የሥራ ቋንቋ መሆኑ ፣ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አማርኛ ባልሆኑ ላይ መጫኑ እውነት ነው ። የሆነው ግን ዶ/ር ፀጋዬ ባለው መንገድ አይደለም ። በ13ኛው መ.ክ. ዘ. በዛግዌ ሥረወ መንግሥት ጊዜ በኤርትራ በሚገኘው ሎጎሳርዳ ወረዳ የአካባቢ ሕግ በትግርኛ ተጽፎ ቢገኝም አማርኛ በ12ኛው መ.ክ. ዘ. መጨረሻ ጀምሮ የመንግሥት የሥራ ቋንቋ መሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ ። የመጀመሪያው ገዢ በራሱ ምክንያት አማርኛን የመንግሥት የሥራ ቋንቋ ሊያደርገው ችሏል ። ከዚያ በኋላ ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ገዢዎች ተፈራርቀዋል ። እነዚህ ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች ላገዛዛቸው የማይመቻቸውን ሁሉ ያለ ርህራሄ ያስወግዳሉ ። ሁሉበእጃቸው በደጃቸው የሆነላቸው ዓፄዎች በአማርኛ ቋንቋ ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ አቅም አልነበራቸውም ማለት አይቻልም ፣ ማለት የሚቻለው የራሳቸውን ቋንቋ ጨምሮ አማርኛን ተክቶ የመንግሥት የሥራ ቋንቋ ለመሆን የሚችል አማራጭ በማጣታቸው ሳይወዱ በግድ አማርኛ እንዲቀጥል አድርገዋል ። አማራጭ ቋንቋ ቢኖራቸው ኖሮ ዛሬ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቀድሞ ፕሬዚደንት ኦባማ ጊዜያት የተላለፉ እና የማይፈልጓቸውን ውሣኔዎች እየቀየሩ እንዳሉት ሁሉ አማርኛን አህመድ ግራኝ በአረብኛ / ሱማሊኛ ፣አፄ ዮሀንስ እና መለስ ዜናዊ በትግሪኛ ፣ ትልቁ ራስ አሊ ፣ ተፈሪ መኮንን ጋዲሳ እና መንግሥቱ ኃይለማሪያም ወልዴ አያኖ በአፋን ኦሮሞ ሥልጣን እንደያዙ እንደሚቀይሩ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል።

ምርጫ ባለመኖሩ ግን ሁሉም የአገዛዛቸው እና የሥርዓታቸው የደም ሥር የሆነው አማርኛ ቋንቋ እንዲቀጥል ፣ እንዲያድግ በመላ ሀገሪቱ ተደራሽ እንዲሆን ገዢዎች አስፈላጊውን ሁሉ አድርገዋል ። ዶ/ር ፀጋዬ ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ለሁሉም ይሰራል ፣ ጥያቄ የሚነሳው ይህን መብት ስንጠቀም ከስሜት ውጪ ሆነናል ፣ ምን ያህል ሚዛናዊነትን ጠብቀናል ፣ የሞያ ሥነምግባርን አስከብረናል ፣ መረጃን መሠረት አድርገናል ፣ ሰብዓዊ ሆነናል፣  ከወገንተኝነት ርቀናል ፣ ከድብቅ ፍላጎት ወጥተናል ፣ የሕዝብን ፍላጎት አክብረናል … ወዘተ የሚሉት ናቸው ፣ ሁላችን ለራሳችን መልስ እንስጥ ።

ዶ/ር ፀጋዬ ማንነትህን በውስጥህ ይዘህ ፍለጋ ወጣህ ፣ አላገኘኸውም ። ለራስህ ክብር ሳትቆም ለሌላው አትቆምም ፣ በራስህ ላይ እንዲደርስ የማትፈልገውን በሌላው ላይ አድርገሃል ፣ ተፈጥሮህን እቀይራለሁ ብለህ ግማሽ አካልህን ጥለህ በግማሽህ መኖርን መርጠሃል። በአጠቃላይ ማንነትህን በማጣትህ በዘውገኝነት ተደብቀሃል። የኦሮሞ ብሔርተኝነት አቀንቃኝ መሆን አለመሆን ምርጫው ያንተ፣ ዳኝነት የኦሮሞ ብሔረሰብ እንጂ እኔን ጨምሮ የማንም አይደለም።

ጃዋር በአማራ ድምጽ ራዲዮ ቃለ መጠይቅ የኢትዮጵያ አንድነት ግዴታ ነው ፣ ኦሮሞ የሠራውን ቤት አያፈርስም ፣ ዶ/ር መስፍን አብዲ ኦሮሞ በደሙ እና በእንባው የገነባትን አገር ኢትዮጵያ ስትፈርስ ዝም በሎ አይመለከትም ፣ ብቻውንም ሆነ ከሌሎቹ ጋር ይታደጋታል ፣ ዶ/ር ዲማ ነገኦ አማራ እና ኦሮሞ አሸዋ እና ሲሚንቶ ናቸው ፣ የኦሮሞ ወጣቶች ጣና ኬኛ ፣ ዶ/ር አብራሃም ዓለሙ ኦሮሞን አታሳንሱ አታዋርዱ ፣ ባሪያ ሆኖ አያውቅም ፣ ኦሮሞ ያልተሳተፈበት መንግሥታዊ ሥርዓት የለም ፣ ዶ/ር ጳውሎስ ሚልኪያስ በኢትዮጵያ ላይ የኦሮሞ አሻራ ያላረፈበት የለም … ሌሎችንም ማንሳት ይቻላል ፣ የሚሉትን ዶ/ር ፀጋዬ የራስህን ማንነት እና አቋም መለስ ብለህ ለማየት መልካም አጋጣሚ ተፈጥሮልሃል ብዬ አምናለሁ ። የነሱን አባባል በሚዛኑ አንድ ጎን የአንተን በሌላው ጎን አስቀመጠህ አመዛዝነው። ዶ/ ር ፀጋዬ፣ የኢትዮጵያን ሁኔታ ለመረዳት የአንተን የዶክትሬት መመረቂያ ጽሑፍ እንድናነብ ጋብዘሃል ፣ ግብዣህ ጥሩ ነው ግን አንተ የጽሑፉ ጥሩ መስታወት በመሆንህ ገለፃህ ፣ ትረካህ እና ትዋኔህ ጽሑፍህን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል ብዬ አምናለሁ ፣ እኔ በሃይጅን ፈተና መቶ ከመቶ አግኝቶ እጁን ሳይታጠብ እንደበላው ተማሪ ነኝ ካላልክ በቀር!

ከሠላምታ ጋር

LEAVE A REPLY