በሕወሐት አዝጋሚ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ሴራ የኢትዮጵያ ህዝብ የነፃነት ትግል አይቀለበስም!!!

በሕወሐት አዝጋሚ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ሴራ የኢትዮጵያ ህዝብ የነፃነት ትግል አይቀለበስም!!!

/ከሰማያዊ ብሔራዊ ሸንጎ የተሰጠ መግለጫ/

ሕወሐት/ኢሕአዴግ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ጥልቅ ተሃድሶ የኢትዮጵያን ህዝብ በወታደራዊ አገዛዝ አፍኖ ለህዝብ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ሳይሞክር ለአለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ጊዚያት በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን የሚገልፁ ዜጎችን መግደልና በጅምላ ማሰር የእለት ከዕለት ስራው አድርጎ ቆይቷል፡፡

ገዥው ቡድን ለጊዜውም ቢሆን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያዳፍን የሞከረው የህዝብ የነፃነትና የእኩልነት ጥያቄ በአስቸኳይ ጊዜ አወጁ ወቅትና አዋጁም ከተነሳ በኋላ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ አገዛዙ ጥያቄ ያነሱ ዜጎችን በአደባባይ በጥይት መረሸኑን ቀጥሎበታል፡፡ ለ26 ዓመታት ኮትኩቶ ያሳደገው የዘር ጥላቻ ፍሬ አፍርቶ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት በአደባባይ እየታረዱ ቤት ንብረታቸው እየተቃጠለ በኢትዮጵያ ምድር የንፁሃን ደም እየጮኸ ነው፡፡ የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎችም የአገዛዙ የዘር ጥላቻ በረጨው መርዝ ምክንያት የታዳጊ ወጣቶች ህይወት አደጋ ላይ ወድቋል፡፡

በስልጣን ላይ ያለው የአራት የጎሳ ድርጅቶች ግንባር የሆነው ኢህአዴግ የየጎሳው መንግስታት የሚፈጥሩት የእርስ በእርስ ግጭትና አለመተማመን ለብዙ ኢትዮጵያውያን ሞትና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል፡፡

ሕወሐት በህዝብ የተቀጣጠለውን የህዝብ ተቃውሞ ተከትሎ በግንባሩ ውስጥ በተፈጠረው መከፋፈል ምክንያት ሀገራችንን እራሱ በፃፈው ህገ መንግስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅን ጨምሮ ቢጠቀምም የህዝቡን ተቃውሞም ሆነ የድርጅቶችን የውስጥ ሽኩቻ ማስቆም አልቻለም፡፡ በሁሉም መመዘኛዎች አቅመ ቢስ የሆነው ሕወሐት ደህንነቱንና መከላከያውን ቢቆጣጠርም አሁን ያለውን የህዝብ ተቃውሞንና የድርጅት ሽኩቻ አሁን ያለው የሲቪል አገዛዝ እስካለ ድረስ ተንፋሹን ማስቀጠል እንደማይችል አረጋግጧል፡፡

አሁን ካለው የዓለም ፖለቲካ አንፃር የለየለት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ማድረግ ኪሳራ እንደሚያስከትልበት የተገነዘበው ሕወሐት አሁን ያለውን ህገ መንግስት ሙሉ በሙሉ በመተው ለወታደሩ ትልቅ ስልጣን የሚሰጥና በሂደትም ሙሉ በሙሉ የሲቪል አስተዳደሩን ስልጣን ነጥቆ በወታደሩ እጅ እንዲገባ የሚያደርግ “የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት” በሚል አካል ስም “አዝጋሚ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት” በተግባር ደንግጓል፡፡ በመሰረቱ ይህ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት የተባለው አደረጃጀት ዓላማው በሀገር ደህንነት ጉዳይ ለአስፈፃሚው አካል ምክር ከመስጠት ውጭ በራሱ እርምጃ የመውሰድ ምንም ስልጣን የሌለው አካል ነው፡፡ ገዥው ቡድን በዚህ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት በተባለው አደረጃጀት ስም ሊወስደው ያቀደው እርምጃ አገዛዙ ያለው የመጨረሻ በትር ሲሆን የሚወስደው የመደናገጥና የተስፋ መቁረጥ እርምጃ ሀገራችንንና ዜጎቻችንን ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል ብንገነዘብም የኢትዮጵያን ህዝብ የነፃነት ጥያቄ ሊቀለብሰው እንደማይችል በፅኑ እናምናለን፡፡

በዓለም ታሪክ አገዛዝ ህዝብን ለዘለቄታው አሸንፎ አያውቅም፡፡ አሁን በአገዛዙ እየተወሰዱ ያሉ የጭካኔ እርምጃዎች የሚያረጋግጡልን የህዝብ ትግል ወደ ነፃነት እየተቃረበና አገዛዙ እየሞተ መሆኑን ነው፡፡

በመሆኑም ይህንን ከባድ ፈተና ለመወጣትና ትግሉን በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለመራራው ትግል በቆራጥነት እንዲነሱ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ በመጨረሻም ሕወሐት ችግሮችን ከማወሳሰብና ሀገራችንን በትኖ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ማምራት ለሁላችንም የኢትዮጵያ ልጆች የማይበጅ ከባድ የታሪክ ጠባሳ መሆኑን በመገንዘብ ከተያያዘው የአውዳሚነትና የተስፋ መቁረጥ እርምጃ ተቆጥቦ ስልጣን ለህዝብ እንዲያስረክብና ሁሉን አቀፍ የባለ አደራ መንግስት እንዲቋቋም ያለበትን ታሪካዊ ሃላፊነት እንዲወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ህዳር 03 ቀን 2010 ዓ.ም
አዲስ አበባ

LEAVE A REPLY