እስር ቤት ውስጥ ህይወቱ ያለፈው አርማዬ ዋቄ ማሞ /በጌታቸው ሺፈራው/

እስር ቤት ውስጥ ህይወቱ ያለፈው አርማዬ ዋቄ ማሞ /በጌታቸው ሺፈራው/

ስም:_ አርማዬ ዋቄ ማሞ
ዕድሜ:_ 25
አድራሻ:_ አዲስ አበባ፣ ኮልፌ ክ/ከ፣ ወረዳ 05፣ የቤት ቁጥር 1190
ስራ:_ ቧንቧ ጥገና
የታሰረበት ወቅት:_ነሃሴ 2008ዓም
መጀመርያ የገባበት ክስ:_ እፅ ይዞ መገኘት

ሁለተኛ ክስ (የተደበደበበት) :_ በ28/12/2008 በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ውስጥ ማረሚያ ቤቱ የሰጠውን ዩኒፎርም ና የሌሎቹን ዩኒፎርም ያቃጠለ በመሆኑ፣ የዞን አንድ መኝታ ቤት ሁለት መስታውት በመጥረጊያ እንጨት የሰበረና የዞን አንድ መኝታ ቤት ሶስቱን ግድግዳ ከሌሎች ግብረአበሮቹ ጋር በመሆን በብረት ያፈረሰ በመሆኑ
የክስ መዝገብ:_ በእነ ብስራት ብርሃኑ 15ኛ
የሞተበት ቀን:_ መስከረም 2/2010 ዓም ንጋት
የአርማዬ ዋቄ አባት፣ አቶ ዋቄ ማሞ ቃል:_
የአርማዬ ታናሽ ወንድሙ ቴዎድሮስ ዋቄ ተፈርዶበት ዝዋይ ታስሮ ነበር። በሌላ ክስ ቀጠሮ ስለነበረው ኮልፌ ቀራኒዮ የሚገኝ ፍርድ ቤት ይቀርባል። በወቅቱ አርማዬ የወንድሙን ችሎት ለመከታተል ፍርድ ቤቱ በር ላይ ተቀምጦ ነበር። በጊዜው የፅዳት ሰራተኞች ከሽንት ቤት ያገኙትን ነጠላ ጫማ የማን ነው እያሉ ይጠይቃሉ። ፖሊስ ግን ነጠላ ጫማውን ተቀብሎ ለአርማዬ ሰጠው። እሱ የእኔ አይደለም ብሎ ተከራከረ። ደብድበው፣ የአንተ ነው ብለው አስያዙት። እፅ ይዞ በመገኘት እሱንም ወንድሙንም ከሰሷቸው።

ከቂሊንጦ ቃጠሎ በኋላ ሸዋሮቢት ለምርመራ ተወስዶ ነበር። ሄጄ ጠይቄዋለሁ። ፊቱና እጁ አብጦ ነበር። እየደበደቡት እንደሆነ ነገረኝ። ቁጥጥር ስለነበር ብዙ ማውራት አልቻልንም። በቁምጣ፣ ራቁቱን ማለት ይቻላል የነበረው። እግሩ ላይም የድብደባ ምልክት ይታያል። ቂሊንጦ ሲመለስም ድብደባው የባሰ ነበር።ማታ ማታ እየደበደቡት መሆኑን ነግሮኛል። የጨብጥ በሽታ ነበረበት። ህክምና አላገኘም። ሸዋሮቢት ብልቱ ላይ ውሃ በሀይላንድ ሞልተው ስላንጠለጠሉበት ሱሪ መልበስም እንደሚቸገር ነግሮኛል። 2009 ክረምት ላይ ለ15 ቀን ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር ተወስዶ ጨለማ ቤት ገብቶ፣ ራቁቱን ተደብድቧል። ቂሊንጦ ውስጥ ይደበደብ የነበረው ታሳምፃለህ ተብሎ ነው። እሱ አዲስ አበባ ቢወለድም የቤተሰብ የትውልድ ቦታ አምቦ መሆኑ እየተጠቀሰ ኦነግ ነህ እየተባለ ተሰቃይቷል። እንደሚገድሉት ዝተውበት ነበር። ይህን ነግሮኛል።

ቤተሰብ በሳምንት አንድ ቀን ነበር የምንጠይቀው። ነገር ግን በድብደባውና በዛቻው ምክንያት እንደሚገድሉት ስለሚያውቅ “በሳምንት ሶስት ጊዜ ጠይቁኝ። ከገደሉኝ አስከሬኔን ለመውሰድ እንኳ ቶሎ ቶሎ መጥታችሁ ጠይቁኝ” ብሎናል። መስከረም 1/2010 በዓሉን ውለን በነጋታው ነው የሄድነው። መስከረም 2 ጠዋት ሄደን ስንጠይቅ ሆዱን አሞት ሀኪም ቤት እንደሄደ፣ ከሰዓት 9 ሰዓት ላይ እንደሚመለስ ነገሩን። ነገር ግን ቤት ከተመለስብ በኋላ ወደ ማታ ለእህቱ ደውለው ጳውሎስ ሆስፒታል አስከሬኑን ውሰዱ አሏት። በምን እንደሞተ ለእኔ ግልፅ ነበር። አስከሬኑን አይቸዋለሁ። መሃል አናቱ ተጎድቷል።ፈርሷል። ሌላ አካሉ በሙሉ አብጧል።ሆዱ ተቀዶ እንደነገሩ ተሰፍቷል። ልቡና ኩላሊቱ እንደሌለ ነው መገመት የቻልኩት። እንደነገሩ ስለሰፉት እነዚህ አካላቱ መውጣታቸውን ያሳያል። እኛ በምን እንደሞተ ስለምንገምት በፋሻ ነው እንጅ በባዶ እጃችን አልነካነም። የሆስፒታሉን ምርመራ ውጤት መቀበል አላስፈለገኝም ነበር። የተቀበረው ቀራኒዮ ወረዳ ቅዱስ ፋኑኤል ነው። ካስፈለገ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲታዘብልኝ ከተቀበረበት አውጥቼ እንዲመረመር ማድረግ እችላለሁ።

1ኛ ተከሳሽ ብስራት አበራ ጥቅምት 15/2010ጥቅምት ዓም ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ምድብ ችሎት የሰጠው ቃል:_

አይኔ እያየ ፊቴ ላይ ነው ልቡን ረግጥ የገደሉት። ሁላችንም ተደብድበናል። የእስር ቤቱ ኃላፊ ሱፐር ኢንተንደንት አሰፋ ኪዳነ እያለ ነው የተደበደብነው። 2009 ዓም ነሃሴ ላይ በነበረው ፍርድ ቤት” ከዚህ ማረሚያ ቤት አስወጡኝ። ይገድሉኛል ” ብሎ ተናግሮ ነበር። እንዲህ ሲል መሃል ዳኛው ሰምተዋል(ወደ ዳኛው እየጠቆመ)። ሁላችንም አደጋ ላይ ነን። የት እንሂድ? ገዳዮች እጅ ነው ያለነው። እኔ ተመልሼ ወደ ቂሊንጦ አልሄድም። ይገድሉኛል። እዚሁ በጥይት ይግደሉኝ ። የአርማዬ ጉዳይ ይመርመር። አንድ ቤት ውስጥ ያሉ በርካታ እስረኞች የተፈፀመበትን ድብደባ አይተዋል። አንድ ቤት ሰው በሙሉ ለዚህ ምስክር ነው።

LEAVE A REPLY