/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የውሀ ሀብት ሚኒስትሮች ትናንት በካይሮ የካሄዱት ስብሰባ ያለ ውጤት መበተኑ ታወቀ።
የሚኒስትሮቹ የሦስትዮሽ ስብሰባ ባለፈው ጥቅምት ወር በአዲስ አበባ ተጀምሮ የነበረን አጀንዳ ለመቋጨት ታስቦ የነበረ ቢሆንም አሁንም ያለ ስምምነት ስብሰባው መበተኑን የግብጹ የመስኖ ሚኒስትር መሐመድ አብዱል አቲን ጠቅሶ “ሀራም ኦን ላይን” የተባለ የሚዲያ አውታር ከካይሮ ዘግቧል።አጀንዳውም የአባይ ግድብ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚያመጣው ተጽዕኖ ካለ እንዲያጡ ለተሰጣቸው ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች “ረቂቅ የጥናት ማስጀመሪያ (guidelines) ለማስጽደቅ ነበር።ስብሰባው ያለ ውጤት ከተጠናቀቀ በሗላም ቀጥሎ መቼ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የደረሱበት ስምንነት እንደሌለም ታውቋል። አርቴሊያና ቢ.አር.ኤል የተባሉ ሁለቱ የዘርፉ ተቋማት በ2016 መጨረሻ ላይ ወደ ስራ እንዲገቡ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም የጥናት መመሪያውን የሦስቱ መንግስታት ስምምነት ላይ ደርሰው ባለማጽደቃቸው ለመዘግየቱ ምንክንያት እንደሆነም ተነግሯል።
በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት ሐሙስ እለት የግብጹፕሬዝዳንት አብደልፈታህ አልሲሲ በካይሮ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ኢትዮጵያ የምታስገነባዉን የአባይ ግድብን በተመለከተ በተዘዋዋሪ ጥብቅ የሚባል ማስጠቀቂያ መስጠታቸው ተዘግቧል። የቀድሞዉ ጄኔራል አልሲሲ በመግለጫቸው ላይ “የኢትዮጵያዉያን ወዳጆቻችንና ወንድሞቻችንን የልማት ፍላጎት በበጎ መልኩ እንመለከተዋን፤ ነገር ግን ለእኛ ውሃ የልማት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የህይወትና ሞት ጉዳይ ነው፡፡ ሀገራዊ ደህንነታችንን የማስጠበቅ አቅሙ አለን፡፡ ለእኛ ውሃ የብሔራዊ ደህንነት ጥያቄ ነው፡፡ አራት ነጥብ።” የሚል የዛቻ መልዕክት አስተላልፈዋል።“ኢትዮጵያ ግድቡን ውሀ መሙላት ብትጀምር መንግስታቸው ምን አይነት እርምጃ ይወስዳል?” የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች ቢቀርብላቸውም ምላሽ ሳይሰጡ በዝምታ አልፈውታል።የግብጽ ባለስልጣናት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ መተባበር አላሳየችም በማለት በተደጋጋሚ ስሞታ እያሰሙ ይገኛሉ።