“ለመብትህ የምንታገልልህ ተራው አማራ…

“ለመብትህ የምንታገልልህ ተራው አማራ…

“ለመብትህ የምንታገልልህ ተራው አማራ… እንኳን ወደ አማራ መናገሻ በሰላም መጣህ” አለኝ አብሮ አደግ ጓደኛዬ ደመላሽ ትናንት ምሽት ባሕር ዳር እንደተገናኘን። አብሮት የነበረው የደመላሽ ጓደኛም ቀበል አድርጎ “አሃ… አብሮ አደግህ ‘ከሽሜው ግሩፕ’ ነዋ!? ለማንኛውም እንኳን ደህና መጣህ… ስላወቅሁህ ደስ ብሎኛል” አለ… መጀመሪያ ወደ ደሜ ቀጥሎም ወደ እኔ እየተመለከተ። የንግግራቸው ግራውም ስላልገባኝ ፊቴ ላይ የመደናገር ስሜት ታየብኝ መሰለኝ… ደሜ ፈገግ ብሎ “ስንፎግርህ ነው መሌ… ደህና ነህ ግን?” በማለት ነገር ለማስቀየስ ሞከረ። “ደህናስ ደህና ነኝ… ግን ንግግራችሁ እንደምንድነው? እኔ በምን መስፈርት ነው ተራው አማራ የሆንሁት? የሽሜው ግሩፕ አባልነቴስ ከምንድነው? እስኪ ነገራችሁን ግልጥ አድርጉት” አልሁ የማፈር ስሜት እየተሰማኝ። ተሳሳቁብኝ። ስሜቴ ከማፈር ወደ መናደድ ተሸጋገረ። “ምን ያስቃችኋል?” ናፍቆኝ እኔን በክብር ተቀብሎ ሻይ ቡና እየጋበዘኝ ባለው ደሜ እና ጓደኛው ላይ ጮሁባቸው።
“ኧረ አረጋጋው መሌ… እነዚህ መገለጫዎች በባሕር ዳር የተለመዱና ‘ለኢትዮጵያዊ ነኝ’ ባይ አማራዎች የተለጠፉ መፎገሪያዎች ናቸው።” አለኝ ደሜ አሁንም በሹፈት እየሳቀብኝ። ንግግራቸው አሁን ገና ዘለቀኝ 🙂

አሁን አሁን ባሕር ዳር ከውብ ዘምባባዎቿ ስር የጎጃም ሙዚቃ ብቻ ሲዘመርባት አይደመጥም። ከሙዚቃው ከፍ ብለው የፖለቲካ ድምጾች እየተሰሙ ነው። ባሕር ዳር ውበት እየፈሰሰባት ቅኔ የሚዘረፍባት የአእምሮና የስሜት ማዝናኛ ገነት ከመሆን ባለፈ የአማራ ብሔርተኝነት የሚቀነቀንባት የፖለቲካ ከተማም እየሆነች ነው። በተለይ ወጣቱ “አማራ ነኝ” ብሏል። አማራ ነኝ ሲልም የምር አማራነትን ከመቀበልም አልፎ “ኢትዮጵያዊ ነኝ” የሚለውን የሕብረተሰብ ክፍል ወደማሸማቀቅም ተሸጋግሯል። አማራ ሆኖ ‘ኢትዮጵያዊ ነኝ’ የሚል ሁሉ በባሕር ዳሩ አዲስ ትውልድ ፉገራ ይሸነቆጣል።
ይህ አዲስ ትውልድ በኢህአዴግ ዘመን ተወልዶ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቅኝት ያደገና ምድር ላይ ከሩብ ምዕተ ዓመት በታች ብቻ የኖረ ነው።

እግር ጥሎህ ባሕር ዳር ከመጣህና ስለኢትዮጵያዊነት አብዝተህ ካወራህ… “አይዞህ ወንድማችን… አንተ ለመብትህ የምንታገልልህ ተራው አማራ ነህ።” የሚል የነቆራ ቁርስ ያቀምሱሃል። በዚህ አልጠግብ ካልህም… “ውይ… እርስዎ እኮ የሽሜው ግሩፕ ነዎት… ዘመኑን ያልዋጁ የድሮ ሥርዓት ናፋቂ አረጋዊ አባታችን ሆይ! አማራ መሆን ካልቻሉ ወደ ኢትዮጵያ አምላክ ይጸልዩልን!” የሚል ጉርሻ ይጨምሩልሃል።
በወጣቶች እምነት ባሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ያለችው በሽማግሌው አማራ ጭንቅላት ውስጥ ብቻ ነው። ይህች በአረጋውያን አእምሮ የተወሰነች ኢትዮጵያ ለአማራው የትምክህት ምንጭ መሆኗ አብቅቶ የመገፋት ስም ተደርጋ ተፈርጃለች። እና ስሟን ደጋግሞ የሚጠራ ሁሉ በተደጋጋሚ የፉገራ ቃላት ይሸነቆጣል። “አማራነት ይለምልም” የባሕር ዳር ወጣቶች የጋራ ድምጽ ሆኗል።
……….
….
ይሁንና… እንዲህ በፉገራ ሲያሸማቅቅህ የዋለን አንድ የባሕር ዳር ወጣት ቀስና ለስለስ ባለ ወግ ስለ አንድ ሁለት የኢትዮጵያውያን አርበኞች የነፃነት ድል ብትተርክለት በገብርዬ መንፈስ እያቅራራ በበላይ ወኔ ይፎክርልሃል። በስሟ መገፋቱን እየነገረህ ስለ ስሟ በተሰው ጀግኖች ስትመጣበት ሲቃ ይተናነቀዋል።
ይህም… አማራው ምን ብሔርተኝነትን ቢዘምር በደሙ የተዋሐደችውን ኢትዮጵያ ፈጽሞ ከልቡ መፋቅ እንደማይችል ያሳይሃል።

ሰላም!

LEAVE A REPLY