/ቢቢኤን ህዳር 12/2010/
ጀግናዉ አህመዲን ጀበል በህክምና እጦት መሰቃየቱን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ከተለቀቁ በሗላ በህዝብ ዘንድ የተቀሰቀሰዉን አለም አቀፍ ቁጭት ሁሉም አስተዉሎታል። ህዝቡም አስቸኳይ ህክምና ማግኘት አለበት፣ብሔራዊ ጀግናችን አህመዲን ጀበልም ሆነ ሌሎች የህሊና እስረኞች መፈታት አለባቸው ወደሚል የጋራ አቋም መሸጋገሩ የሚዘነጋ አይደለም።
ጉዳዩ በተለያዩ አለማት ባሉ ድርጅቶችና ማህበራት ዘንድ አትኩሮት አግኝቶ የአህመዲን ጀበል ስቃይ አንድ ሊያረገን ይገባል በሚል ልዩነቶችን አስወግደው በጋራ ለመስራት የሚመካከሩበት ሆኗል። ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ በበጎ ፈቃድ የሚንቀሳቀሱ (pro bono) ጠበቆች የአህመዲን ጉዳይ ዳግም አለም አቀፋዊ አትኩሮት እንዲያገኝ ስራ መስራት መጀመራቸዉን የሚያሳዩ ኢሜይሎች ቢቢኤን እጅ ይገኛሉ። የአህመዲን ጀበልም ሆነ የሌሎች የህሊና እስረኞች የእስር ቤት ጓደኛ የነበሩና ካገር የወጡ ወገኖች አህመዲንንም ሆነ ሌሎች ጓደኞቻቸውን ከአሸባሪው ህወሃት ለመታደግ በህዝብ የሚታገዝ ዘመቻ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ናቸው። ሌሎችም በጊዜ ሒደት ዉስጥ ለህዝብ ይፋ የሚደረጉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ቢቢኤን ለማወቅ ችሏል። ጉዳዩ አህመዲን ጀበል ባስቸኳይ ይታከም እና አህመዲን ጀበልም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ ሊሆን ሲገባ በድንገት ተቀልብሶ፤ «አህመዲን ህክምና ተፈቀደለት፣አህመዲን ህክምናን ተከለከለ» የሚል ትርክትን (narrative) እየያዘ መሆኑ አደገኛ መሆኑን ለማመላከት እንወዳለን።
ቀደም ሲል ጀግናዉ ኦቦ በቀለ ገርባ «የዋስትና መብታቸው ተከበሮ ሊፈቱ ነው!» የሚለው ዜና ለአሸባሪው ህወሃት ፖለቲካዊ ትኩሳትን ቀንሶለት እንደነበር ማስታወሱ ግድ ይላል።ከቀናት በሗላ በማፍያዎች የሚመራዉ የካንጋሮ ፍርድ ቤት የኦቦ በቀለ ገርባን የዋስትና መብትን መከልከሉ የሚዘነጋ አይደለም። ስለዚህ ስለጀግናዉ አህመዲን ጀበል የተጋነኑ አርእስተ ዜናዎችን በመፍጠር፣ በህዝብ ፊት ለጉዳዩና ለምንጮች ቅርበት ያለ መስሎ መታየቱ የህዝብን አስተሳሰባና አትኩሮት ለመበታተን አስተዋጽኦ እያበረከተ በመሆኑ ከወዲሁ ጥንቃቄ ያሻል ለማለት ማሰሰቡ ተገቢ ነው።
የአህመዲን ጉዳይ የውስጥ ህመም ነው! ይህ የዉስጥ ህመም ደግሞ ሊሽር የሚችለው ጀግናንን እንደ አዉሬ ከሚበላዉ ህወሃት መንጋጋ አህመዲንን ፈልቅቀን ስናወጣው ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ተጠናክሮ፣ተደራጅቶ፣ ተቀራርቦ፣ተወያይቶ መታገልን ይሻል። እነዚህን የጋራ እሴቶች አሸባሪው ህወሃት በሚሰጣቸው ጊዜያዊ መደለያዎች ለማምከንና ለማዘናጋት የሚደረገውን ጥረት ቢቢኤን ይሞግታል፣እንደከዚህ ቀደሙም ያከሽፋል። ስለዚህ ጥያቄው «አህመዲን ጀበል ይታከም!» ከሚለው ዘለግ ብሎ «አህመዲን ጀበልም ሆነ ሌሎች የህሊና እስረኞች ባስቸኳይ ይፈቱ!» ወደሚለው መሽጋገር አለበት።
የአህመዲን ጀበል የጤና ሁናቴ ሳይሻሻል፣ አህመዲን ለከፋ ችግር ቢጋለጥ፤ አሸባሪው ህወሃትም ሆነ የህወሃትን ገመና ሸፍነው በጫንቃቸው ላይ የተሸከሙት ደጋፊዎቹ ግዜና ዘመን ይቅር ለማይለው ኪሳራ እንደሚዳረጉ እሙን ነው። ባንጻሩ የአህመዲን ጀበል ጉዳይ አንገብግቦት ከህክምና እስከ ነጻ አህመዲን ጀበል በሚል የወል አላማ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለማቀዛቀዝ የሚደረጉ ማዛናጊያዎች ከተጠያቂነት አያድኑም። መከራው አልፎ ነገ የዛሬው የተግባር መዝገባችን…ከታሪካችን ላይ ለቅኝት ሲገለጥ…ጠላቶች ከፈጸሙት ስዉርና ግልጽ ደባ ተለይቶ የማይታይ ሊሆን ይችላል።ለማጠቃለል በሶሻል ሚዲያ ላይ የሚፈጥሩ ብቃትና ስልታዊነት ያልታከለባቸው ግለሰባዊ ግርግሮች እልባት ሊያገኙ ይገባል የሚል ምክርና አቋም አለን።