/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ የዚምባብዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ስልጣናቸውን በራሳቸው ፈቃድ መልቀቃቸውን የሀገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ጃኮብ ሙንዴና ገለጹ።የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በጻፉት የስልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ ላይ ስልጣናቸውን በፈቃደኝነት የለቀቁት “ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር” እንዲኖር በማሰብ ነው ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ይህ የሮበርት ሙጋቤ ውሳኔ የሀገሪቱ ምክር ቤት ክስ መስርቶ ከስልጣናቸው በግድ እንዲነሱ ለማድረግ የጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲቋረጥ ማድረጉን የዝምባብዌ የሚዲያ ተቋማት እየዘገቡ ነው።የሮበርት ሙጋቤን በፈቃደኝነት ከስልጣን መልቀቅ ተከትሎ ዚምባብዌያውያን አደባባይ ላይ በመውጣት ደስታቸውን እየገለፁ ነው።ቅዳሜ እለት ባለቤታቸውን ግሬስ ሙጋቤን ከፓርቲው አባልነት ሰርዞ፤ እርሳቸውን ደግሞ ከፓርቲ ከአመራርነት ያወረደው ዛኑ ፒ ኤፍ የተባለው ፓርቲያቸውም በፈቃዳቸው ስልጣን መልቃቸውን ተከትሎ በቲውተር ገጹ ላይ “ዚምባብዌ አደረገች፤ አብረን አደረግነው፤ እኛ እራሳችን አደረግነው።” በማለት ደስታቸውን ገልጸዋል።
ለ37 ዓመታት ሀገሪቱን የመሩት የ93 ዓመቱ ሙጋቤ ካለፈው እሮብ ጀምሮ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው እንዲለቁ በተደጋጋሚ የቀረበላቸውን ጥያቄና ግፊት አልቀበልም ሲሉ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።
እ.ኤ.አ ከ2014 ጀምሮ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩትና ከሁለት ሳምንት በፊት በሮበርት ሙጋቤ ከስልጣን የተባረሩት የ75 ዓመቱ አዛውንት ኤመርሰን ማንጋግዋ በሚቀጥለው እሮብ የሀገሪቱን የፕሬዚዳንትነት በትረ-ስልጣን ለመረከብ ሰፊ እድል እንዳላቸው እየተዘገበ ይገኛል።