ህዝብ የመከራው ቀንበር ከብዶት ” በቃ ” ሲል /ነቢዩ ሲራክ/

ህዝብ የመከራው ቀንበር ከብዶት ” በቃ ” ሲል /ነቢዩ ሲራክ/

      ፕሬ.ሮበርት ሙጋቤ በክብር ስልጣን ላይ ወጥተው በውርደት ስልጣን ለቀቁ የሚለውን መረጃ ተከታተልን ። ጨቋኙ በውርደት ስልጣን ለቀቁ ፣ ተጨቋኙ ህዝብ አሸነፈ !  የአፍሪካ አምባገነኖች ሀገራቸውን ከጨቋኞች ታድገው ጨቋኝ ይሆናሉ ። የአንባገነኖች መጨረሻቸው በውርደት የመሆኑ ሚስጥር በአደባባይ ስልጣንን ሙጥኝ ብለው የፈጸሙት ጥፋት ፣ ውድመት መሆኑ ነው ። አምባገነኖች  ክፉዎች ናቸውና ስልጣንን መከታ አድርገው ” ከጨቋኞች ነጻ አወጣነው !”  የሚሏቸውን ዜጎች ሰብአዊ መብት መርገጣቸው ለውርደቱ ስንብት ቀዳሚ ምክንያት ነው ።
  የአፍሪካ አንባገነኖች ካስወገዷቸው ጨቋኞች በላይ የገዛ ወንድም እህታቸውን ፣ ወገናቸውን ጨቁነው በመግዛት ለከፋ ውርደት  ፣ ስቅየትና ስደት ዳርገዋል። ህዝብ ” ጭቆናው በቃ!  እንቢ ! ” ብሎ ከሚወዱት መንበረ ስልጣን ያስወግዳቸዋል ። አምባገነኖች ስልጣናቸውን ለመጠበቅ የገነቡት ብርቱ ጦር የወገኑ መገፋት የተረዳው ቀን ህዝብ ከፍቶት ሲያምጽ ለህዝብ ጎን ወገንተኛ መሆናቸውን ደጋግመው አሳይተውናል ። ይህንን እውነት በአፍሪካ አረብ ሀገራት በቱኒዝና በግንጽ ተመልክተናል  !
   የጨቋኝ አንባገነን መሪዎች የፍርድ ቀን እስኪደርስ የፖርቲ ሹሞቻቸውን እየቀያየሩ በምርጫ ስም ጭቆናውን ማራዘም ልማዳቸው ነው ። በዲሞክራሲ ግንባታና በልማት ስም አገዛዛቸውን ማስፋፋት ተንኮላቸው ነው ። ያም ሆኖ ህዝብ የመከራው ቀንበር ከብዶት ” በቃ ”  ሲል የሚያበቃ መሆኑን ደጋግመን ታዝበናል። ይህንን ደረቅ ሃቅ አምባገኖች እና ደጋፊ አጫፋሪ የጥቅም ተጋሪዎቻቸው አይቀበሉትም ። ይህንን እውነት የአንባገነኖችና የደጋፊዎቻቸው እዝነ ልቦና  መረዳት አይቻለውም  !!! ከዚህ ሁሉ አንባገነኖች ስልጣን በውርደት መልቀቅ ግድ ይሆንባቸዋል።  የአፍሪካ መሪዎች የህዝብን ድምጽ መስማትና ስልጣንን ለህዘብ ጥቅም ማዋልን  የሚማሩ አይመስልም የሚባለውም ለዚህ ነው
   የአንባገነንነት መጨረሻ  ውርደቱ እስኪደርስ ቀጥቅጠው ይገዛሉ  ! ፕሬ ሮበርት ሙጋቤ ለዚህ ማሳያ ጥሩ ምሳሌ ናቸው ። እነሆ ባለፉት ቀናት ካየነው የዚንባብዌ የህዝብ አመጻ የምንረዳው እውነት ሆኗል።   ፕሬ ሮበርት ሙጋቤ መጨረሻቸው አላማረም ። በውርደት ስልጣናቸውን ለቀዋል  !!!  የዚምባቡዌ ህዝብ ባለውለታ የሆኑት ፕሬ ሮበርት ሙጋቤ እንደ ታላቁ የአፍሪካ መሪ እንደ ፕሬ ማንዴላ የሰላም አባት ፣ አስታራቂ መሪ መሆን ሲችሉ ክብር አልወደደላቸውም  ! በክብር መሸኘት ተስኗቸው በውርደት እንደ ውሻ ከኮሎኒ ነጻ ባወጡት ሀገር ይባረሩ ዘንድ የእጃቸውን የሚያገኙበት ቀን አቅርበውታል
እዝነ ልቦና ያላቸው መሪዎች ይስጠን   !
ነቢዩ ሲራክ
ህዳር 12 ቀን 2010 ዓም

LEAVE A REPLY