/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ ከሦስት ሳምንታት በፊት በሮበርት ሙጋቤ አስተዳድር ከምክትል ፕሬዚዳንትነት ተባረው የነበሩት ኤመርሰን ምናንጋግዋ የሀገሪቱ ርዕሰ-ብሄር በመሆን ዛሬ ቃለ መሀላ ፈጸሙ።
ምናንጋግዋ አዲሱ የዝምባብዌ ርዕሰ ብሄር ለመሆን ቃለ መሀላ በፈጸሙበት ወቅት “ለዝምባብዌ ህዝብ ታማኝና ታዛዥ እንደሚሆኑ እንዲሁም የሀገሪቱን ህገ-መንግስትና ሌሎችንም ህጎች እንደ እንደሚያስከብሩና እንደሚያስከብሩ ቃል ገብተዋል። ከሳምንት በፊት በወታደሩ በተቀነባበረ ስልት የቁም እስረኛ የነበሩትና በተለያየ ጫናና ግፊት ማክሰኞ እለት ስልጣናቸውን በፈቃደኝነት እንደለቀቁ ያሳወቁትን የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤን “አባታችንና የሀገር መሪያችን” በማለት አዲሱ ፕሬዚዳንት ምናንጋግዋ ምስጋና ችረዋቸዋል። ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ የሚመሰርቱት መንግስት ጊዜዊ ሲሆን በሚቀጥለው ሐምሌ ወር 2018 በሀገሪቱ ጠቅላላ ምርጫ እንደሚካሄድም የወጣው መርሃ ግብር ያሳያል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በፈቃዳደኝነት ስልጣን በመልቀቃቸውና በዝምባብዌ የነፃነት ትግል ወቅት ከፍተኛ አስተዋፅዖ በማድረጋቸው ያለመከሰስ መብት እንደተሰጣቸውና በሀገራቸው አሊያም በፈለጉት ሀገር መኖር እንደሚችሉ ትናንት የወጡ ዘገባዎች አረጋግጠዋል።
አንድ የዚምባቡዌ ፓርላማ አባል ትናንት ለዘ-ጋርዲያን ጋዜጣ እንደተናገሩት ሮበርት ሙጋቤ “ከስልጣን በፈቃዳቸው ስለለቀቁና በነፃነት ትግሉ ወቅት ከፍተኛ ሚና ስለ ነበራቸው” ያለመከሰስ ዋስትና ከነቤተሰባቸው እንደሚሰጣቸውና ንብረታቸውም ህጋዊ ከለላ እንደሚያገኝ ገልጸዋል። ዘምባብዌ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ የወጣችው እ.ኤ.አ በ1980 ነው።