መግቢያ
ህወሓትና የቻይና ኮምኒስት ፓርቲ ከሊቃነ መናብርቶቻቸው ሞት በኋላ፡ የኮሚኒስትዋ ቻይና ታሪክ በሃገራችን ይደገም ይሆን?
የሊቀ መንበር ማኦ ዜዶንግ ሶስተኛዋ ባለቤት ጂያንግ ኲንግ (Jiang Qing) ከ1965 አ.ም.ፈ በፊት ከመካከለኛ እርከን የዘለለ ታዋቂነት አልነበራትም፡፡ የኋላ ኋላ ግን፣ ነብሰበላው የቻይና አብዮት (Cultural Revolution 1966-1976) ከመሩትና ‹‹አራቱ ማፍያዎች (Gang of Four)›› በመባል ከሚታወቁት ወግ አጥባቂ ኮምኒስቶች አንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡ ዋና ግባቸው የሊቀ መንበር ማኦ ‹‹ራዕዮችን›› ማስቀጠልና እንዳለ መተግበር ነበር፡፡
እመቤት ጂያንግ ከ Wang Hongwen፣ Zhang Chunqiao፣ Yao Wenyuan ጋራ በመሆን እና በሊቀ መንበር ማኦ ድጋፋ ለዘብተኛ በሚባሉትና በ”Liu Shaoqi” እና Deng Xiaoping የሚመሩትን ቁም ስቅላቸውን ያሳዩዋቸው ነበር፡፡ ቀዮቹ ጥበቃዎች (Red Guards) የሚባሉት የወጣቶች ቡድን፣ የሚድያ፣ የኮምኒስት ፓርቲ ረቂቅ ሐሳብና ትምህርት የሚሳሰሉትን ትካላት በመቆጣጠርም ኮምኒስት ፓርቲውን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረውት ነበር ማለት ይቻላል፡፡
‹‹አራቱ ማፍያዎች›› ሊቀ-መንበር ማኦ ከሞተ በኋላ በመስከረም 9፣ 1976 ዓ.ም ያልተሳካ መፈንቅለ መንግስት በማካሄዳቸው የባላንጣዎቻቸው ሰለባ መሆን ጀመሩ፡፡ Hua Guofeng ‹‹አራቱን ማፍያዎች›› በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል፡፡ለአራት ዓመታት በቁጥጥር ስር ውለው ከቆዩ በኋላም ከ1980 – 1981 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ እመቤት ጂያንግና ዣንግ በሞት ፍርድ ሲቀጡ (በኋላ ወደ ዕድሜ ልክ እስራት ተቀይሮላቸዋል)፣ ዋንግ በእድሜ ልክ፣ ያኦ ደግሞ በ20 ዓመት እስራት ተቀጥቷል፡፡
እመቤት ጂያንግ በፍርድ ሂደቱ ወቅት በተናገረችውና ‹‹የሊቀ መንበር ማኦ ውሻ ነበርኩ፤ እንድነክስለት የሚፈልገኝን ሁሉ ነክሸለታለሁ (I was Chairman Mao’s dog – I bit who he wanted me to bite.)›› በሚለው ኑዛዜዋን ትታወቃለች፡፡ ‹‹አራቱ ማፍያዎች›› ከታሰሩ በኋላ፣ ኋ ኩፈንግ ለደንግ ዢያኦፒንግ ወደ ፖለቲካዊ አመራር መልሶታል፡፡ በመሆኑም ደንግ፣ ሊቀ መንበር ማኦ ከመሞቱ በፊት ጀምሮ ሲያቀነቅናቸው የነበሩት ለውጦችን ለመተግበር እድል አገኘ፡፡ ደንግ የእርሻና የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎችን አሻሽሏል፤ የሕዝብ ብዛት ለመቀነስም ለአንድ ቤተሰብ አንድ ልጅ ፖሊሲ ተግባራዊ አድርጓል፡፡ ‹‹ድመት አይጦችን እስከ ያዘች ድረስ ጥቁር ትሁን ነጭ አይገደኝም›› በሚለው አባባሉ የሚታወቀው ደንግ ወገ-አጥባቂ ኮሚኒስቶችን ቀስበቀስ በማስወገድ የቻይና የልማት ግስጋሴ ማንቀሳቀስ የቻለ የተግባር ሰው ነበር፡፡
ወደ ሃገራችን ስንመለስ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር በ2004 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ወሬው ሁሉ ‹‹ራእይ መለስ›› ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ጠቅላይ ሚኒስተር ሃይለማርያም ደሳለኝ ሳይቀር ዓላማዬ ‹‹የመለስ ሌጋሲ ማስቀጠል ነው›› ብለው እንደ ነበር የሚታወስ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ እጅግ ወግ-አጥባቂዎቹ ግን ከአራት የማይበልጡ የህወሓት ባለስልጣናት ናቸው፡፡ የአቶ መለስ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍንን ጨምሮ ሶስቱ በህወሓት ውስጥ እየተካሄደ በሚገኘው መራራ ሂስና ግለ ሂስ ሰለባ የሆኑት የትግራይ ክልል ፕረዚደንት አቶ አባይ ወልዱና ምክትላቸው አቶ በየነ በክሩ ናቸው፡፡
ወይዘሮ አዜብ፣ ሂሱን መቋቋም አቅቷቸው መድርክ ረግጠው መውጣታቸውን ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን ይቅርታ ጠይቀው ወደ ግምገማው ቢመለሱም ከስራ አስፈፃሚና ከማእከላይ ኮምቴ አባልነታቸው ታግደዋል፡፡ የአራተኛው እጣ ፈንታ ግን እስካሁን ድረስ በውል አልታወቀም፡፡ ነገር ግን፣ የመከላከያ የበላይ ሃላፊው ኢታማዦር ሹም ሳሞራ የኑስ እንደሆኑ ይነገራል፡፡ አንዳንዶቹ ድግሞ ከሶስት ዓመታት በፊት ክፉኛ ተገምግመው ከማእከላይ ኮምቴ አባልነታቸው የተባረሩት አቶ ቴድሮስ ሐጎስም ‹‹የመለስ ራእይ›› አቀንቃኝና የወይዘሮ አዜብ ደጋፊ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡
ለመሆኑ ‹‹ከአራቱ ማፍያዎች›› ከስልጣን ከተወገዱ (ዝቅ እንዲሉ ከተደረጉ) በኋላ ሊከሰቱ የሚችሉት ስጋቶችና መልካም ዕድሎች ምንድን ናቸው?
ስጋት፦ የተለመደው አዙሪት ይቀጥል ይሆን?
በህወሓት ታሪክ የስልጣን ሽኩቻ እንጂ የአስተሳሰብ ለውጥ ተከስቶ አያውቅም፡፡ አንዱ ቡድን ሌላኛውን በማሸነፍና ከስልጣን በማባረር ነው የሚጠናቀቀው፡፡ ለዚህም የ1967፣ የ1969፣ የ1977 ና የ1993 ዓ.ም የድርጅቱ ህውከቶች (ሕንፍሽፍሽ) በዋቢነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሁሉም ህውከቶች የተፈቱት በሃይልና አሸናፊው ተሸናፊውን በመቅጣት ወይም ከድርጅቱ በማባረር ነበር፡፡ በመሆኑም የአሁኑም እንደቀድሞዎቹ በተመሳሳይ መልኩ እንዳይጠናቀቅ ያሰጋል፡፡
የአሁኑ ችግር አንዱ ቡድን ሌላኛውን በማባረሩ ብቻ የሚፈታ አይደለም፡፡ የችግሮቹ ምንጭ አጥንቶ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ያሻል፡፡ ይህ ከሆነም ህዝቡ የሚያነሳቸው የልማትና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ላይመለሱ ይችላሉ፡፡ ካልተመለሱ የህዝቡ ጥያቄ ይቀጥላል፡፡ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እየተቀጣጠለ የመጣው የሀገራችን ቀውስም እንዲሁ ይቀጥላል፡፡
መልካም ዕድል፦ የትግራዩ ደንግ ዢያኦፒንግ ማን ይሆን? ዶክተር ደብረፅዮን ወይስ ጌታቸው አሰፋ?
አሁን ከስልጣን የተወገዱት ሰዎች በሁሉም መለክያዎች የውድቀት ተምሳሌት ናቸው፡፡ ብዙዎች ‘የሚናገሩትም ሆነ የሚሰሩት አያውቁም’ ይሏቸዋል፡፡ ‹‹የመለስ ራእይ›› ማስቀጠል ከሚለው በስተቀር ሌላ ወሬ አልነበራቸውም፡፡ አቶ አባይ ወልዱ በቀድሞ ጀነራሎች (አበበ ተክለሃይማኖትና ፃድቃን ገብረተንሳይ) ላይ የሰነዘሩት ‹‹መለስ የሌለ መሆኑን አይተው የተዳከምን መስሏቸው ሊያጠቁን ያስባሉ›› የሚለው ወቀሳቸው መራራ ትችት ቀርቦበታል፡፡
ዶክተር ደብረፅዮን በበኩላቸው “እንኳን እነዚህ ታጋዮች ማንም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ የመናገርና የመፃፍ መብት አለው” የሚል አስተያየት ነበር የሰጡት፡፡ በሀገር ደረጃ የተከሰተው ቀውስ መንስኤም የተሻለ ግንዛቤ አላቸው፡፡ በባህሪያቸው የተለየ ሓሳብና ምክኒያታዊ የሆነ ትችት የመቀበል ችግርም የለባቸውም፡፡ በመሆኑም ከሌሎቹን ሁሉ በተሻለ አዲሱን ትውልድ የማቀፍ አዝማምያ ሳይኖራቸው አይቀርም፡፡ አሁን እያሸነፈ ያለው ቡድን ከሳቸው ጋራ ተመሳሳይ አቋም ያለው ስለሆነ በተነፃፃሪ የተሻለ መፍትሔ ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ ምናልባትም በድርጅቱ ውስጥ የአስተሳሰብ (የእይታ) እና የፖሊሲ ለውጥ ሊያስተዋውቁም ይችላሉ፡፡
ማጠቃለያ
በአሁኑ ወቅት ሃገራችን በአደገኛ አጣብቅኝ ውስጥ ትገኛለች፡፡ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ነን! የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ቀውሶች ይቀረፋሉ ሲባል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ ነው፡፡ በመሆኑም የተለየ እይታና አፈፃፀም ያለው አመራር ያስፈልጋል፡፡ አመራሩ የለውጥ እንቅፋት የሆኑትን ገሸሽ በማድረግ ለውጡን ተቀብሎ ለሃገራችን በሚጠቅም መልኩ ማስኬድ የሚችል መሆን አለበት፡፡ ከልሆነ ግን፣ በሃገራችን የእርሰ-በእርስ ጦርነት ጭምር ሊከሰት ይችላል፡፡ ይህም የሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ቀውሶች ይበልጥ ስር እንዲሰዱ ሊያደርግ ይችላል፡፡