ሊያነቡት የሚገባ-የከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ምድብ ችሎት ውሎ /ጌታቸው ሽፈራው/

ሊያነቡት የሚገባ-የከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ምድብ ችሎት ውሎ /ጌታቸው ሽፈራው/

” ለእኔ ይህ ችሎት መፍትሄ አይሰጠኝም። መፍትሄ የማገኘው የስርዓት ለውጥ ሲመጣ ብቻ ነው። ከእስር ቤት ስወጣም እታገላለሁ!” ጌታሁን በየነ

“የምንበላው የተፈጨ አሸዋ ነው!” ባንተወሰን አበበ

የዛሬው የፈደራልከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ምድብ ችሎት ውሎ

(ህዳር 26/2010 ዓ.ም)

~በእነ አዱኛ ኬቲሳ የክስ መዝገብ የተከሰሱ 10 ወጣቶች እያንዳንዳቸው አምስት አመት ተፈርዶባቸዋል። አብዱ፣ ሽመልስ፣ ካሳሁን፣ ጳውሎስ፣ ኬኖ፣ ቶማስ፣ ኢሳያስ፣ ምትኩ እና ፈይሳ አንከላከልብ ብለው የተፈረደባቸው ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ እከላከላለሁ በማለቱ ቀጠሮ ተሰጥቶታል።

~ በግንቦት ሰባት ክስ የተመሰረተባቸው 7 የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተከላከሉ የሚል ብይን ተሰጥቶባቸዋል። በእነ ምስጋናው ደምሴ የክስ መዝገብ የተከሰሱት መካከል ምስጋናው ደምሴ፣ አሸናፊ ሞገስ፣ ሙሉቀን ባዘዘው፣ ታዴ ብርሃኑ፣ ጌትነት አዛናው፣ ዳንኤል ዮሃንስና ሌሎች ሁለት ተከሳሾች ናቸው። ሁሉም ተከሳሾች በማንኛውም መንገድ በ”ሽብርተኛ” ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ፣ ከ1ኛ ተከሳሽ ውጭ ያሉት በኩብለላ እና 4ኛ ተከሳሽ ከመከላከያ ሰራዊት የተረከበውን እቃ አላስረከበም የሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል። በሁሉም ክሶች እንዲከላከሉ ተበይኖባቸዋል። ተከሳሾቹ መዝገቡ በደንብ ሳይመረመር እንደተበደየነባቸው ለፍርድ ቤቱ ቅሬታቸውን ገልፀዋል።

~ በእነ ጌታሁን በየነ ክስ መዝገብ የተከሰሱ 14 ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን መሰጠቱ ይታወሳል። 1ኛ ተከሳሽ ጌታሁን በየንን ጨምሮ አንከላከልም ያሉ ተከሳሾች በመኖራቸው የቅጣት አስተያየት ለማቅረብ ተቀጥረው ነበር። ተከሳሾቹ የቅጣት አስተያየታቸውን በፅሑፍ እንዲያቀርቡ ሲጠየቁ ጌታሁን በየነ በቃል እንደሚያቀርብ ገልፆ ነበር። በዛሬው ችሎትም ” ለእኔ ይህ ችሎት መፍትሄ አይሰጠኝም። እኔ መፍትሄ የማገኘው ስር ነቀል ለውጥ ሲመጣ ነው፣ መፍትሄው የስርዓት ለውጥ ብቻ ነው። መፍትሄ የማገኘው ዴሞክራሲና ፍትህ ሲሰፍን ነው። ከእስር ቤት ስወጣም እታገላለሁ” ብሏል። ፍርድ ቤቱ 1ኛ ተከሳሽ አስተያየት በሚሰጥበት ወቅት “ይህን አንሰማህም! በስነ ስርዓት ሕጉ መሰረት አቅርብ!” እያለ በተደጋጋሚ አቋርጦታል። 1ኛ ተከሳሽ ጌታሁን በየነ የተከሰሰበት ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠቱን በመግለፅ አስተያየቱን ሰጥቷል።

~በእነ ጌታሁን በየነ የክስ መዝገብ አንከላከልም ያሉት ተከሳሾች የቅጣት ውሳኔውን ለማንበብ ለታህሳስ 9/ 2010 ተቀጥረዋል። ተከሳሾቹ ቂሊንጦ እስር ቤት ውስጥ የሚገጥማቸውን ችግር በመግለፅ ቀጠሮ እንዲያጥርላቸው ጠይቀዋል። 13ኛ ተከሳሽ ባንተወሰን አበበ “የምንበላው የተፈጨ አሸዋ ነው” ሲል ለፍርድ ቤቱ በምሬት ተናግሯል።

~ በእነ አወል አባጊዳ የክስ መዝገብ 4ኛ ተከሳሽ ሰሚራ አማን 2 የመከላከያ ምስክሮችን አሰምቻለች። ከምስክሮቹ መካከል ንግስት ይርጋ ማዕከላዊ እስር ቤት በሰሚራ ላይ የተፈፀመውን በደል ለፍርድ ቤቱ አስረድታለች። የማዕከላዊ መርማሪዎች የተፃፈና የሰሚራ ያልሆነን ቃል በግድ ፈርሚ በማለት ድብደባ እንደፈፀሙባት፣ በተደጋጋሚ በተፈፀመባት ድበደባ በግድ የእሷ ባልሆነ ቃል ላይ መፈረሟን፣ በግድ ለማስፈረም በተፈፀመባት ድብደባም እራሷ፣ እግሯ ላይ ጉዳት ደርሶባት ክሊኒክ ሄዳ እንደታከመች ንግስት ይርጋ የምስክርነት ቃሏን ሰጥታለች።

LEAVE A REPLY