/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፦ ፈቃድ ሳያወጡ በሳተላይት አማካይነት በሀገር ውስጥ ቋንቋ ፕሮግራማቸውን በሚያሰራጩ አራት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የህዝብንና የፓርላማውን እገዛ እንደሚያስፈልገው የብሮድ ካስት ባለሥልጣን መናገሩን ሸገር ራዲዮ ዘገበ፡፡
ቃና፣ ኢቢኤስ፣ ኤል ቲቪና ናሁ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፈቃድ ተሰጥቷቸው ስርጭታቸውን የጀመሩት በውጭ ሀገር የተቋቋሙና በተቋቋሙበት ሀገርም ፈቃድ ያላቸው ናቸው በሚል ኃሣብ እንደነበርም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ተናግሯል፡፡
የብሮድካስት ባለስልጣን ከባህል ቱሪዝምና መገናኛ ብዙሃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በ2010ዓ.ም በጀት ዓመት እቅድ ላይ ሲመክር እንደገለጸው “አራቱም የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚሰሩትም ሆነ ገቢ የሚያገኙት በኢትዮጵያ መሆኑን ደርሼበታለሁ” ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ቋንቋ የሚሰራጭ የቴሌቪዥን ጣቢያ የውጭ ሀገር ዜጋም ሆነ ትውልደ ኢትዮጵያዊ በባለቤትነት ሊያስተዳድረው እንደማይችል የብሮድካስት አዋጅ እንደሚደነግግም ተገልጿል፡፡
የአራቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ባለቤቶች ግን ትውልደ ኢትዮጵያዊና የውጭ ሀገር ዜጎች እንደሚገኙባቸው ማወቁን ባለስልጣኑ ገልጿል። የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርአይ አስገዶም እንዳሉት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ቃና፣ ኢቢኤስ፣ ኤል ቲቪና ናሁ የተሰኙ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሕጋዊ ፈቃድ እንዲያወጡ ማነጋገራቸውን እስረድተዋል። የቴሌቭዥን ጣቢያዎቹ ፈቃድ የማያወጡ ከሆነ ህጉ በሚፈቅደው መልኩ እርምጃ እንደሚወስዱና ለዚህም ህዝብና ፓርላማው ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡
ኢ.ቢ.ኤስ እና ቃና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በመዝናኛው ዘርፍ የማይናቅ ተመልካች ያላቸው ሲሆን ከተመሰረተ ሁለት ዓመታት ያልሞላው ቃና ቴሌቪዥን በትርጉም በሚያቀርባቸው የተለያዩ የውጭ ሀገር ፊልሞች የ“ሀገር ባልህ”ን በመመረዝና ተማሪዎችን ከትምህር ገበታ ላይ እንዳይገኙ በማዘናጋትና በማዘናጋት ከፍተኛ ትችት ሲቀርብበት መቆየቱ ይታወቃል።