/በሥዩም ወርቅነህ/
አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኘው አንባገነን፣ አፓርታይድና ዘረኛው የወያኔ/ህወሃት-ኢህአዴግ ሥርዓት ህዝብ የሚፈልገውን ይቅርና የሥርዓቱ ጀሌዎች የለፈፉትን እንደማያሥፈፅም እሙን ነው። ይህ ደግሞ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ግልፅ የሆነ ጉዳይ ነው። ድፍን ኢትዮጵያዊ በሚባል ደረጃ ወያኔ/ህወሃት-ኢህአዴግ የሙሰኛ፣ የፀረ-ኢትዮጵያዊና የዘረኞች ሥብሥብ መሆኑን ይሥማማል። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ተሥማምተውና ተፈቃቅደው እንዳይቀጥሉ ሌት-ከቀን እየሰሩ መሆኑ ግልፅ ነው። ሥርዓቱ በሥልጣን ላይ እሥካለ ድረሥ ሃገራችንና ህዝባችን ለችጋር እንደሚጋለጡና ሥርዓቱ ካልተወገደ የመበታተን አደጋም እንደሚገጥመን ሳንወድ በግድ የምንቀበለው አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል።
ወያኔ/ህወሃት-ኢህአዴግ ምርጫ በመጣ ቁጥር ህዝብን ለማጭበርበር በሁሉም የህብረተሰባችን ክፍል እየዞረ አሥቧቸው የማያውቃቸው የልማት ተግባሮችን እሰራለሁ በማለት የመሰረት ድንጋይ እንደሚያሥቀመጥ የተለመደ ጉዳይ ነው። ህዝባችንም ይህን የማጭበርበሪያ ተግባር በአግባቡ ሥለሚረዳ ሥርዓቱን እንደማይመርጥ የሚታወቅ ነው። ወያኔ/ህወሃት-ኢህአዴግ ምርጫን ለማሸነፍ የሚጠቀምበት ምርኩዝ ምርጫ ቦርድ ሲሆን ለተቃውሞ የወጡትን ለመቀልበሥ የሚገድልበት፣ የሚያሥርበት፣ የሚደበድብበት፣ የሚያሥርበትና የሚያሥፈራራበት ምርኩዝ ደግሞ የሥርዓቱ መከላከያ ሰራዊት ነው።
የወያኔ/ህወሃት-ኢህአዴግ ሥርዓትን አንቅረው ከተፉት የአገራችን ማህበረሰብ ውሥጥ የጉራጌ ማህበረሰብ አንዱ ነው። በተከታታይ በተደረጉ አገራዊ ምርጫዎች ድምፁን በመንፈግ በተግባር አሳይቷል። በዚህም ምክንያት የማህብረሰቡ ተወላጆች ሰርፈ ብዙ መሥዋዕትነት ከፍለዋል። ይህን ደግሞ የሚቀለበሥ ጉዳይ አይደለም። “ሚሥማር ሲመቱት ነው የሚጠብቀው” እንደሚባለው ሁሉ፤ የጉራጌ ማህበረሰብም ሥርዓቱን ላይመለሥ ለማሥወገድ ታጥቆ ተነሥቷል። ይህን የተገነዘበው የወያኔ/ህወሃት-ኢህአዴግ ሥርዓት፤ ከ7 ዓመት በፊት ህዝቡ ከ220 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ሊገነባው ያሰበውን የጤና የትምህርትና የግብርና ማዕከል፤ ብሩን በመዝረፍ በቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊሥ የተጣለውን መሰረተ ድንጋይ በማፍረሥ፣ ሊሰራ የታሰበው መሰረተ ልማት እንደተሰረዘ ገልጿል። ይህ በጣም አሳዛኝና አሳፋሪ ተግባር ነው።
በመጀመሪያ ማዕከሉ የሚገነባው የጉራጌ ማህበረሰብ ባዋጣው ገንዘብ እንጂ ከሥርዓቱ ከሚደጎም በጀት አልነበረም። ሲቀጥል በጉራጌ ዞን የጤና የትምህርትና የግብርና ማዕከል ባለመኖሩ ሥርዓቱ ማህበረሰቡን እያሥገደደ እየገዛና ግብር እያሥከፈለ ሥለሆነ መሰረታዊ ተቋማትን የመገንባት ግዴታ አለበት። የጉራጌ ማህበረሰብ ለፍቶ ያመጣውን ገንዘብ ከመመዝበር አልፎ ህዝብን እያሥጨፈሩ የተጣለውን መሰረተ ድንጋይ በአንድ ግንበኛ አፍርሶ “ተቋሙ አይገነባም ወደ ትግራይ ክልል ተቀልብሷል” ማለት ሥርዓቱ ለጉራጌ ማህበረሰብ ያለውን ከልክ ያለፈ ንቀትና ጥላቻ በግልፅ ያመለክታል። ይህ ደግሞ የጉራጌ ማህበረሰብ ቢያበረታው እንጂ የሚያሰንፈው ጉዳይ አይደለም።
ይህ ሥርዓት ወደ ሥልጣን ከመጣ 27 ዓመት ቢሞላውም ለጉራጌ ህዝብ ነቀርሳ ከመሆን ውጪ አንድ ልማት ያመጣው ነገር የለም። የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የተገነባው በማህብረሰቡ ጉልበትና ሃብት ነው። ለመላው የጉራጌ ማህበረሰብ ያለው አንድ ሆሥፒታል ብቻ ነው። ህዝብ ሲታመም የሚታከምበት ሆሥፒታል ሳይገነቡ፣ በራሱ ተነሳሽነት ሃብትና ንብረቱን አሟጦ ሊገነባው ያሰበውን ማዕከል ጭምር እየቀለበሱ ለህዝብ የቆምኩ ነኝ ብሎ መለፈፍ ከቀልድም ያለፈ ጅልነት ነው።
ጉራጌ ንቃ!
ትግላችን ይቀጥላል!