የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ( ኢንሳ) ሃላፊ ሜ/ር ጄኔራል ተክለብርሃን ወልዳረጋይ ወራይና ከተባለ መጽሄት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ስለትግራይ እና ስለ ህዝቡ ብዙ ነገሮችን ተናግረዋል። ህወሃት የትግራይን ፖሊሲ የቀረጸው “የሰው አስተሳሰብን መሰረት አድርጎ ነው” የሚሉት ጄኔራሉ፣ የትግራይ ህዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሲነጻጸር የራሱ የሆነ አንጸራዊ ብልጫ (comparative advantage) የሚያስገኙለት እሴቶች አሉት ይላሉ። እነዚህን አንጻራዊ ብልጫ የሚያስገኙ እሴቶች ሲዘረዝሩም፦
1ኛ የትግራይ ህዝብ ጽናት አለው አሉ። ( ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጽናት የለውም ማለታቸው ነው)
2ኛ የትግራይ ህዝብ ዲሲፕሊን አለው አሉ። ( ሌለው ኢትዮጵያዊ ዲሲፕሊን የለውም ማለታቸው ነው)
3ኛ የትግራይ ህዝብ ለሰው ልጅ የሚሰጠው ክብር ከፍተኛ ነው አሉ ። ( ሌላው ኢትዮጵያዊ ለሰው ልጅ ክብር አይሰጥም ማለታቸው ነው)
4ኛ የትግራይ ህዝብ በእውቀት ላይ የተመሰረተ (አስተሳሰብ) ነው ያለው አሉ። ( ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ መሃይም ነው ማለታቸው ነው)
5ኛ የትግራይ ህዝብ በረጅም ታሪክ ያፈራቸው ቅርሶች አሉት አሉ። ( ሌሎች ቅርሶች የላቸውም ወይም ቅርሶቹ የትግራይ ብቻ ናቸው ማለታቸው ነው)።
ባለስልጣኑ በዚህ ብቻ አያበቁም። የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያኖች የተሻለ “ሰውን መሰረት ያደረገ” አንጻራዊ ብልጫ ስላለው፣ ይህንን ብልጫውን በአገር አመራር ደረጃ ሊጠቀምበት ይገባል አሉ። የትግራይ ወጣቶችም በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በተለይም በዘመናዊ ቴክኖሎጂው ዘርፍ ተምረው አመራሩን መያዝ አለባቸው ሲሉ ይመክራሉ። የድርጅታቸው ፖሊሲም ይህ መሆኑን ይነግሩናል። ህወሃት ከሌለው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለዬ የትግራይ ተወላጆችን ብቻ በብዛት ወደ ውጭ ልኮ የሚያስተምረው በአገሪቱ አመራር ውስጥ አንጻራዊ ብልጫ ( comparative advantage) ለማግኘት መሆኑን ባለስልጣኑ ይነግሩናል። አንጻራዊ ብልጫ የሚገኘው ደግሞ የሌሎች ብሄር ተወላጆች የትምህርት እድሉ እንዳይኖራቸው በመከልከል እና የተሻለ የትምህርት እድል እንዳያገኙ መንገዶችን ሁሉ በመዝጋት ነው። ይህ ፖሊሲ ነጮች በአፍሪካ ላይ ሲተገብሩት የነበረው የቅኝ ግዛት ፖሊሲ ተቀጥላ ነው። ቅኝ ገዢዎች፣ ቅኝ ተገዢዎች ከተወሰኑ ትምህርቶች በላይ እንዳይማሩ የከለክሉ ነበር። “ማሃይምን በቀላሉ መግዛት ይቻላል” ከሚል አስተሳሰብ የሚመጣ እጅግ አደገኛ አስተሳሰብ ነው።
ጄኔራሉ ይቀጥላሉ። “የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያ ተፈላጊ መሆን ካለበት አሁንና ለወደፊቱ በሚፈጥረው ሃብት ነው” አሉ። ትግራይ ሃብት ካላፈራ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደማይፈልገው ይናገራሉ። በገደምዳሜም ህወሃት ዝርፊያውን የሚያጡዋጡፈው ለዚህ እንደሆነ ይነግሩናል። ዜግነት በደም፣ በባህል፣ በታሪክ፣ በመረዳዳት ወዘተ መሆኑ ቀርቶ በብሄሮች የሃብት መጠን ላይ የተመሰረተ መሆኑንም አሳውቀውናል።
ትግራይ የተፈጥሮ ሃብት ስለሌላት ብቻ የትግራይ ልጆችን የተለዬ ትምህርት በማስተማር በኢትዮጵያ አንጻራዊ አብላጫ እንዲኖራቸው የማድረጉ ፖሊሲ፣ የተፈጥሮ ሃብት ያላቸው አካባቢ ልጆች “ሃብታቸው ይበቃቸዋል” በሚል እሳቤ በትምህርት እንዳይገፉ የሚያደርግና ዜግነትን የሚያጠፋ እጅግ አደገኛ አስተሳሰብ በመሆኑ ከእንግዲህ ሊቀጥል አይገባውም። የአማራ፣ የኦሮሞ ፣ የደቡብ፣ የጋምቤላ ወዘተ ወጣቶች ትምህርት በበቂ ሁኔታ የማታገኙበትን ሚስጢር ጄኔራሉ ነግረዋችሁዋል። ለምን በቂ ትምህርት አላገኛችሁም ተብሎ እንደወደቃችሁ፣ ስራ አጥ እንደሆናችሁ፣ ተመርቃችሁ በስራው አለም ተወዳዳሪ መሆን እንዳልቻላችሁ፣ ለምን ሃብት ማፍራት እንደተሳናችሁ ሁሉ ጄኔራሉ ሚስጢሩን ዘክዝከው ነግረዋችሁዋል:: ይህን መቀየር ከእንግዲህ የእናንተ ፋንታ ነው።
( ማ.ሻ. የሰውዬውን ቃለ ምልልስ አይጋ ፎረም ላይ በአማርኛ ማንበብ ይቻላል)