መፍትሄው! በህዝባዊ ማዕበል የቀውሱን ፈጣሪ ማስወገድ!! ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ት.ዴ.ት./TAND)

መፍትሄው! በህዝባዊ ማዕበል የቀውሱን ፈጣሪ ማስወገድ!! ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ት.ዴ.ት./TAND)

ታሕሳስ 2017
ቀውሱ ከባድ ነው፣ ሃገርን ሊያፈራርስ፥ ህዝቦችን እርስበርስ ሊያዳም የሚችል ኣደገኛ ቀውስ ለመሆኑ በየቀኑ ከምንሰማቸው ዘግናኝና ኣሳዛኝ ድርጊቶች መገንዘብ ይቻላል። ይህ ኣስጨናቂ ክስተት በኣንድ ወቅት ብቅ ያለና በቀላሉ የሚያባራም ኣይደለም። ሲከማች የቆየና ስር ያለው ነው፣ ቢሆንም በዘመነ ህወሓት/ኢህኣዴግ ጭራሽ እንዲያንሰራራ በመቻሉ ኣምባገነኖቹ ከሚያደርሱት ኣረመንያዊ ግድያ ሌላ ህዝቡ ለእርስበርስ እልቂት እንዲዳረግ ኣድርገውታል። ስለዚህም የቀውሱ ነባር እና ጊዚያዊ መንሰኤዎች በውል ታውቀው፥ ተመጣጣኝ መፍትሄው ተነድፎለት፥ ተግባር ላይ ካልዋለ የፈራነው ሊደርስ ይችላልና ሳንቀደም በጋራው መፍትቴ ላይ እናተኩራለን።

እነሆ ት.ዴ.ት. ከተመሰረተ 1995 ዓ/ም/ፈ. ጀምሮ (ከ22 ዓመታት በፊት መሆኑ ነው)፣ ይህ በጉልበት ስልጣን ላይ የወጣው የህወሓት/ኢህኣዴግ ገዢ ቡድን የኢትዮጵያን ህዝብ ኣመኔታ ስለሌለውና ለህዝቡ ጥቅም ስላልቆመ በጉልበት ብቻ ሳይሆን መሰሪ ስልቶችም በማከል፣ ህዝቡን ኣፍኖ እንደሚገዛ ደጋግመን ስንገልጽ፥ ከነመፍትሄው ጭምር ነበር። ይህ ገዢ ቡድን በስታሊናዊ ኣምባገነንነት የተለከፈ ስለሆነ ማንኛውም ገንቢ ጥያቄ ይሁን ትችት፣ ኣስተያየት ይሁን ተቃውሞ፥ ባጠቃላይ መብት ነክ ጉዳይ የማይቀበል ብቻ ሳይሆን፣ ለየት ያለ ሓሳብ ኣቅራቢውን እንደጠላት ፈርጆ የሚያሳድድ፥ የሚያፍን፥ የሚያስር፥ ኣሰቃይቶ የሚገድል ለመሆኑ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍለ-ሃገራት ኣብነቶች እያጣቀስን ኣስረድተናል፣ ጽፈናል፣ በየመድረኩ ጮሆናል። የዚህ ሁሉ በደል ቤተ-ተመኩሮ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ለመሆኑ ካሉት የዋሻ ድብቅ እስር ቤቶችና እየታፈነ ከሚገደለው ወጣት፥ በየኣመቱ ከሚያንሰራራው ድርቅና ከሚያልቀው ወገን፥ ለስደትና ለልመና ከሚሰማራው ሴትና ወንድ፥ ወዘተ. መገንዘብ እንደሚቻል ኣስረድተናል። ኣሁንም በተለያየ ምክንያት የትግራይ ህዝብ መከራ ያልገባቸው ካሉ ሓቁ ይኸው መሆኑ በኣጽንኦት እንገልጻለን።

ወደ መፍትሄው ስንመጣ ደግሞ፣ ይህ ኣምባገነን ሃይል የሃገሪቱን ሃብትና ጉልበት በመቆጣጠር፣ እንዲሁም ከውጭ ኣጋሮቹ ዙርያ-መለሽ ድጋፍ በማሰባሰብ ተደራጅቶ እንደሚገዛን ሁሉ፥ እኛም በዛው መጠን ተደራጅተንና ኣንድ ማእከል ፈጥረን ይህን ኣምባገነን ቡድን በማስወገድ ለጋራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መፈጠር ስንታገል ነው የሚል ነበር። ለዚህም ነው ህብረት እንዲፈጠር ያላሰለሰ ጥረት ስናደርግ የቆየነው። ኣሁንም ከዚሁ የመፍትሄ መርህ ስለማንወጣ፥ ሸንጎ የተሰኘው የጋራ ድርጅት በጋራ መስርተን በህብረት መታገል ላይ የምንገኘው። ሸንጎው ያሰባሰበው ዓቅም እፊታችን ከተደቀነው ውስብስብ ትግል ኣንጻር ሲመዘን ግን በቂ ጉልበት ስላይደል፣ ሰፊ ኣድማስ ያለው ህብረት ተፈጥሮ ውጤታማ እንዲሆን የሁሉንም ግብኣት ኣስፈላጊ መሆኑ እንገነዘባለን፣ በተያያዘ መልኩም ሌላውን ለማስገንዘብ እንወዳለን።

ስለ መፍትሄ ከተነሳ ላይቀር፥ ገዢው ቡድን እንደሆነ ኣንዴ መቀሌ ሌላ ጊዜ ኣዲስ ኣበባ በመኮፈስ፥ “በስብሰናል እንታደስ” እያለ የማያልቅ ስብሰባ በማካሄድ፥ ኣዳዲስ መሰሪ ስልቶችም በመቀመር ኣገዛዙን ለማጥበቅ ይጨነቃል እንጂ የህዝቡን ብሶት ተሰምቶት የመፍትሄ ፖሊሲ ይዞ ይወጣል ማለት ‘’ከእባብ-እንቁላል እርግብ’’ የመጠበቅ ያህል የማይሆን ነገር ነውና የመከራችን መፍትሄ ከህዝባዊ ማዕበል እንደሚፈልቅ በመተማመን ተደራጅቶ መስራት ይጠይቃል።

በጣም የሚያሳዝነው፥ መሰሪነቱ ወደ ሰፊው ህዝቡ ሰርጾ እንዲገባ በማስደረግ፣ በደጉም በክፉውም ቀን ተባብሮ የኖረውን ህዝብ ኣሁን እርስበርሱ እንዲተላልቅ ማቀነባበሩ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፥ ለዚህ መሰሪ ቅንብሩ ተባባሪዎች የሆኑ፥ በስሜት የሚነዱ “ኣክቲቪስቶች” “ፖለቲከኞች” “የሚዲያ ተቋሞች” መኖራቸው ኣውዳሚ ሁኔታው እንዲጋጋልና የመሰሪዎቹ ውጥን እንዲሳካ ማገዛቸው እጅግ ያሳስባል። ቀደም ሲል በበደኖ፥ በጋምቤላ፥ በጉራፈርዳ፥ . . . ወዘተ፣ ኣሁን ደግሞ በኣምቦ፥ በጨለንቆ፥ በዓዲግራት፥ በወልዲያ፥ . . . ወዘተ፣ የምናያችው እርባና-ቢስ መተላለቅ የገዢው ቡድን ሰንካላ ፖሊሲና መሰሪ ቅንብር ድምር ውጤት መሆናቸው እየታወቀ፥ በሰበብ-ኣስባቡ ሃላፊነት ከማይሰማው ዜጋ በኩል የሚረጩት ኣፍራሽ ድምጾች ማንኛውንም ህዝቡን ሰለባ እስካደረጉ ድረስ ከመሰሪዎቹ ጎን መፈረጃቸው የማይቀር ለመሆኑ ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል።
የሃገራችንን ኣንድነት በታኝ፥ ህዝቦቻችንን እርስበርስ ኣጨፋጫፊ ዋናው ስራኣስኪያጅ የህወሓት/ኢህኣዴግ ማፍያዊ ቡድን ሆኖ እያለና ይህንን መዥገርት ለመንቀስ የጭቁኑ ህዝብ ማዕበል ፈጥሮ መንቀሳቀስ ሲገባ፣ በቁንጽል ኣስተሳሰብ ተነሳስተው ያ መፍትሄ የሚሆነው ህዝባዊ ማዕበል እንዳይፈጠር የሚያሰናክሉ ወገኖችን እርማትም ማስጠንቀቂያም እንዲደርሳቸው ያስፈልጋል። ተወደደም ተጠላ፥ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ፥ ማዕበሉ እንዳይፈጠር ምክንያት እየሆኑ የኣገዛዙን ዕድሜ ያስቀጥላሉና!!!

ከምንገኝበት ከባድ ቀውስ መውጫው ኣንድ በር ብቻ ነው ያለው። ይኸውም ተባብሮና ተቀናጅቶ፣ የጋራ ምእኩል ግንባር ፈጥሮ፥ ህዝባዊ ማዕበል ቀስቅሶ ኣምባገንኑ ኣገዛዝ ማስወግድና በቦታው መጀመርያ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚያስተናግድ የጋራ መንግስታዊ ስርዓተ-ህዝብ (መንስህ) መመስረት ነው። ቀዋሚ መሰረት የሆነው፥ ይህ ስርዓት ተዋቅሮ ከቦታው ስለሌለ ነው፥ ማንም ቡድን እንደምንም ስልጣን ላይ እየወጣ እንዳሻው ረግጦ የሚገዛን። ማፍያዊው ቡድን ከተወገደ በኋላም ያንኑ ዓይነት ቡድን ተመልሶ እንዳይወጣብን ኣስቀድመን ስርዓቱን በጠንካራ መሰረት ላይ ማኖር ያስፈልገናል።
ይህን ዘላቂ የጋር መፍትሄ እግቡ ለማድረስ፥ ት.ዴ.ት. በሸንጎ በኩል ተደራጅቶ እንደሚታገለው ሁሉ ሌሎቻችንም በሰፊ ህብረት ተቀናጅተን መድሃኒታችን የሆነውን ህዝባዊ ማዕበሉ እንድንፈጥር መተባበር ይጠበቅብናል። ይህ ካልሆነ መከራችን እንደሚንዛዛና ካሁኑ የባሰ ኣደጋም መጋበዝ መሆኑን ልናስገነዝብ እንወዳለን።

በመጨረሻም ለትግራይ ህዝብና ልጆቹ ኣጭር መልእክት ማስተላለፍ እንፈልጋለን።
የትግራይ ህዝብ ሆይ! ቀደም ሲል ያካሄድከው ትግል ከጎስቋላው ኑሮ ተላቀህ በእኩልነት፥ በኣንድነት፥ በሰላም ለመኖር ነበር። ሆኖም ትክሻህን ረግጦ ስልጣን ላይ የተቆናጠጠው ማፍያዊ ቡድን፥ በስምህ እየነገደ መላው የኢትዮጵያ ህዝብን የመከራ ኣረንቋ ውስጥ መክተቱ ብቻ ሳይሆን እርስበርሱም እንዲተላለቅ እያደረገ ነው። ይህ መተላለቅ በራስህ ላይም እየደረሰ ለመሆኑ ነጋሪ ኣያስፈልግህም። ምንጩ ባንተ ላይ የሚዝተው የዋህ ወይም ግልብ ዜጋ ሳይሆን እነዛ ለብዝበዛ የተሰማሩ ጨካኝ ገዢዎቹ ናቸው።

ክፋታቸው በዚህ ኣያቆምም፣ ይህን እነሱ ሆን ብለው የፈጠሩት ግጭት ምክንያት በማድረግ የመገንጠል መፍትሄ እንድታቀነቅን እያሴሩብህ ነው። ዓላማው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ እየበዘበዙ ሲያላገጡበት ከነበረው ስልጣን ሲባረሩ፣ ኣንተውኑ ምሽግ በማድረግ የለመዱት ማላገጥ እንዲቀጥሉብት በመፈለግ ነው። ስለዚህ ይህን ኣደገኛ ሴራ ለማክሸፍና ኣፈና የሌለበት ሰላማዊ የጋራ ኑሮ ለመኖር፣ ብዙ ሰው ያልገባው ድርብርብ ኣፈና ቢጫንብህም ቅሉ፥ እንደምንም ተጋፍጠህ፥ ከታሪካዊው ወገንህ ከኣብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ተሰልፈህ ማዕበሉ ውስጥ ግባ። በውትድርና የተሰለፉት ልጆችህንም ኣስረዳቸው።የዘላቂው መፍትሄ ኣቅጣጫ ይህ ብቻ ነው። ከሸንጎ ጀምሮ ያሉት ኢትዮጵያውያን ዴሞክራቶችና ምንጊዜም ኣጋርህ ሰፊውና ጭቁኑ ህዝብ ከጎንህ እንደሚሰለፉ እርግጠኞች ነን፣ እኛም ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ኣብረን ተባብረን እየሰራን ነው።

በጋራ ትግል ኢትዮጵያ ታብባለች፣ ህዝቧም ተፋቅሮ ባንድነት ይኖራል!!!
ት.ዴ.ት. / TAND

LEAVE A REPLY