“ብታምኑም ባታምኑም ቀለበት ውስጥ ከተውናል” /ኤፍሬም እንዳለ/

“ብታምኑም ባታምኑም ቀለበት ውስጥ ከተውናል” /ኤፍሬም እንዳለ/

“ንቀውናል፣ ደፍረውናል – ብታምኑም ባታምኑም በቁማችን ሞተናል” ተብሎ ነበር ያኔ፡፡ ዘንድሮም ደግሞ ‘ብታምኑም፣ ባታምኑም’ የሚባል ነገር አይመጣም አይባልም፡፡

“ንቀውናል፣ ከበውናል፣ ብታምኑም ባታምኑም ቀለበት ውስጥ ከተውናል” የሚያስብል ነገር አይመጣም አይባልም፡፡ ታንኩ በቅርብ እየሰፈረ ነው፣ ከባድ መሳሪያው በቅርብ እየሰፈረ ነው፣ የጦር መርከብና ጀልባው ከማዶ እያጓሩ ነው፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ጦር ሰፈሮች ለማቋቋም የሚደረገው ሽሚያ የሚመስል ጥድፊያ ጦፏል … አፍንጫችን ስር ማለት ነው፡፡

ያኔ ምድረ ቅኝ ገዥ “ከዚህ እስከዚህ የእኛ”፣ “ከዚህ እስከዚህ ደግሞ የእኛ” እያሉ አህጉሪቷን ይቀራመቷት በነበረበት ዘመን ‘ዘ ስከራምብል ፎር አፍሪካ’ የሚባል ነገር ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ‘ዘ ስክራምብል ፎር ዘ ሆርን ኦፍ አፍሪካ’ የሚል ነገር እየተፈጠረ ይመስላል፡፡

ቀደም ባሉት ዘመናት እኮ ጣጣ አልነበረውም…ወይ ሶቪየት ህብረት ነች፣ አለበለዚያም አሜሪካ ነች፡፡ አሁን ግን በተለምዶ ጦራቸውን ከድንበራቸው አስወጥተው የማያውቁና ‘ሀያላን’ የሚል ቅጽል ገና ያልተሰፋላቸው ሀገራት በአካባቢያችን ጦር ሰፈሮች እየመሰረቱ ነው … ዙሪያችንን ለመባል ምንም በማይቀረው ሁኔታ፡፡

በተለይ ነሀሴ ላይ ቻይና በጅቡቲ የጦር ሰፈር ስትመሰርት ታላላቆቹ የዓለም መገናኛ በዙሀን ሁሉ “ይሄ ነገር እንዴት ነው?” ማለት ጀመሩ፡፡ ቻይኖቹ ማብራሪያ ነበራቸው፡፡ “ይሄ የጦር ሰፈር ሳይሆን በአካባቢው ላለን የሰላም ማስከበርና ሰብአዊ ተግባሮቻችን የአቅርቦት ጣቢያ ነው፣” አሉ፡፡ ማንም “እንዳላችሁ” አላላቸውም፡፡ እንደውም ቻይና በአፍሪካ ቀንድ፣ በመላው አፍሪካም ላላት የመስፋፋት ፖሊሲዋ እንዲመቻት ያደረገችው ነው ተባለ፡፡

የቅርብ ማስረጃ ሲባል… የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የበቀደሙ ኮንግርስ ላይ ፕሬዝደንቱ “ቻይና ዓለም ላይ የመሪነት ሚና መጫወት አለባት፣” ያሉትን ይጠቅሳሉ፡፡ ሆኖም አሁን የቻይና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በተለይ የባህረ ሰላጤው ሀገራት በአፍሪካ ቀንድ መሰባሰብ ጥያቄዎችም፣ መላ ምቶችም እያስከተለ ነው፡፡

የባህረ ሰላጤውን ፍጥጫ ወደ አፍሪካ ቀንድ እያስፋፉት ነው ተብሏል፡፡ እንዳጋጣሚ አካባቢው ያሉት ሀገራት በሁሉም መለኪያዎች ኋላ ቀር መሆናቸው በገንዝብ ለማማባልም አያስቸግሩም ነው የሚባለው፡፡

በተለይ ደግሞ ሚጢጢዋ ጅቡቲ ለሌሎች ሀገራት ጦር ሰፈሮች ተመራጭ የመሆኗ ነገር “ለምን?” “እንዴት?” “በምን ምክንያት?” አይነት ጥያቄዎች እያስከተለ ነው፡፡ ሀገሪቷ የአውሮፓ፣ የአሜሪካና የእስያ ጦር ሀይሎች መስፈሪያ እየሆነች ነው፡፡ የቀድሞ ቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ በጅቡቲ ከፍተኛ የጦር ሀይል ክምችት አላት፡፡

ምንም እንኳን የራሳቸው ጦር ሰፈር ባይኖራቸውም የጀርመንና የስፔይን ወታደሮች ከፈረንሳዮቹ ጋር አብረው አሉ ነው የሚባለው፡፡ ከመስከረሙ 2001ዱ የአሜሪካ የሽብር ጥቃት በኋላ አሜሪካ ተቀላቀለች፡፡ ከየመንና ከአፍሪካ ቀንድ የአሸባሪዎችን ጥቃቶች ለመከላከል በሚል የትረምፕ ሀገር በጅቡቲ ወታደራዊ ተቋሟን መሰረተች፡፡

አንድ ገራሚ ነገር ደግሞ አለ … የጃፓን ነገር፡፡ ይቺ ሀገር አይደለም ጦር ሰፈሮች መመስረት ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር አይነት ወታደራዊ እንስቃሴዎች ውስጥ ስሟ ይህን ያህል የሚጠቀስ አይደለም፡፡ እሷም በጅቡቲ ወታደራዊ ሰፈር አላት – ከአገር ውጪ ያላት ብቸኛ ወታደራዊ ሰፈር !!! ለምን ቢባል ቻይና በአካባቢው መጠናከሯ ምቾት አልሰጣትም ነው የሚባለው፡፡ እንደ ፈርንሳዮቹ ግዙፍ ባይሆንም ጣልያንም የራሷ ሰፈር አላት፡፡

“የጅቡቲ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥና በተተራመሰ አካባቢ የተረጋጋ ሰላም ስላላት የታላላቆቹ ሀገራትን ቀለብ ስባለች” ይላሉ ተንታኞች፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ አብዛኛው የባህር የገቢና የውጪ ንግድ የሚካሄደው በጅቡቲ ወደብ በኩል በመሆኑ እዛ ኮሽ ያለው ነገር ሁሉ ስሜታችንን ቢይዝ አይገርምም፡፡

ለነገሩ ጅቡቲ ድሀ ሀገር ነች፡፡ ከፍተኛ የሥራ አጥነት ችግር አለባት፣ ለተደጋጋሚም የምግብና የነዳጅ ዋጋ መናር የተጋለጠች ነች፡ ሰለዚሀ ገንዘብ ያስፈልጋታል፣ ከፍተኛ ገንዘብ፡፡ እኛ በምንከፍለው የወደብ አገልግሎት ሂሳብ ደግሞ የትም አይደረስም፡፡

ስለሆነም ወታደራዊ ሰፈሮችን በማከራየት የምታገኘው ገቢ ለኤኮኖሚ እድገቷ ወሳኝ ነው፡፡ ለምን ብላ እምቢ ትበል ! በተጨማሪም በምድሯ ያሉት የሌሎች ሀገራት ሀይሎች ምናልባት የውጪ ወረራ ቢገጥማት ይከላከሉላታል የሚል ትንተና ቢጤም አለ፡፡

ኤርትራም በዚህ በኩል አልሰነፈችም፡፡ የተባባሩት አረብ ኤሚሬትስ በአሰብ ወደብ ወታደራዊ ተቋማት መስርታለች፡፡ አሁን ኤሚሬትስ ከዛ ላይ ተንደድራ ታንክና መድፏን አፍሪካ ቀንድ የምትተክልበት ምን አሳማኝ ምክንያት አላት ?

አሳማኝ ምክንያት አለኝ ትላለች፡፡ በየመን የሁቲ አማጺዎች ላይ ጦር ከሰበቁ ሀገራት አንዷ በመሆኗ ይህንን ዘመቻ ለማገዝ ጠጋ ማለቷ ነው ተብሏል፡፡ “ይቺ ሰበብ ትሁን እንጂ፣” ይላሉ ታዛቢዎች፣ “ይቺ ሰበብ ትሁን እንጂ ነገሩ የአፍሪካ ቀንድን ለመቆጣጠር የሚደረገው ርብርብር አካል ነው” ይላሉ፡፡

ሳውዲ አረቢያም በኤርትራ እግሯን ተክላለች፡፡

ኤርትራ ከእኛ ጋር ካለችበት ‘ኖ ፒስ፣ ኖ ዋር’ ሁኔታ ሌላ ከጅቡቲ ጋር ወታደሮቻቸውን ያፋጠጠ ቅራኔ ውስጥ ነች … በዱሜራ ደሴት የተነሳ፡፡ ኳታር 400 ያህል ወታደሮቿን በሰላም አስከባሪነት ደሴቲቷ ላይ አስፍራ ነበር፡፡

በቀደም ግን አኮረፈች … ኤርትራና ጅቡቲ ኳታር ላይ ላበሩባት ለሳውዲና ተከታዮቿ ስለወገኑ አኮረፈች !! አኩርፋም ወታደሯችን አስወጣች… ጠባቂ የሌለው ቤት፡፡ የአስመራ ሰዎች ግን ጊዜ አላጠፉም፣ ወዲያውኑ ወታደሮቻቸውን ደሴቲቷ ላይ አሰፈሩ ነው የተባለው፡፡ ይህ ደግሞ የአካባቢውን ፍጥጫ አባብሶታል ነው የሚባለው፡፡

ነገሩ እየተካረረ ከሄደ ሁለቱ ሀገራት መካከል “መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ” የማይባባሉበት ምክንያት የለም ነው የሚባለው፡፡ እንደሚፈራው በጀቡቲና በኤርትራ መሀል ከበድ ያለ ወታደራዊ ግጭት ቢፈጠር የጅቡቲ ስትራቴጂያዊ ወዳጅ የምትባለው ኢትዮጵያ እጇን አጣምራ መቀመጥ ሊያቅታት ይችላል፡፡ እንደውም አንዳንድ ምንጮች የኤርትራን ወታደሮች ከዱሜራ ለማስወጣት ኢትዮጵያ ሃይሏን እያጠናከረች ነው ብለው ነበር፡፡

ከሌሎች ምንጮች የተገኘ ምንም ማስተማመኛ የለም እንጂ፡፡ ይልቁንም ይህንን መላምት የሚያጣጥሉ አሉ፡፡ አንድ ዘገባ፣ “የአፍሪካ ቀንድ ትልቅ የዲፕሎማሲና ወታደራዊ ሀይል የሆነችው ኢትዮጵያ በሁለቱ ሀገራት እሰጥ አገባ ላይ የያዘችው አቋም ገለልተኛ ነው” ብሏል፡፡ በዚህም ሆነ በዛም ግን የዱሜራ ጉዳይ በጊዜ ካልተቋጨና ሁኔታዎች ከተባባሱ በኢትዮጵያና በኤርትራ እንዲሁም በኤርትራና በጅቡቲ ድንበሮች ላይ ከፍተኛ ግጭቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ የሚሉ ስጋቶችም አሉ፡፡

በሌላ በኩል ሁለቱ ሀገራት ለይቶላቸው የምር ቢታኮሱ በእነሱ መሬት ያሉት የውጪ ሀይላት ወገን ይይዛሉ ወይስ ዝም ብለው ይቀመጣሉ ? አስቸጋሪ አዙሪት ይመስላል፡፡ በተለይ የጅቡቲ የቀድሞ ቅኝ ገዥ ፈረንሳይ “አፍንጫን ሲመቱት…” አይነት ነገር ልትል ትችላለች፡፡ ጥሩ ስእል አይደለም ያለው፡፡ አፍሪካ ህብረትና የተባባሩት መንግሥታት ድርድር እንዲጀመር ያደረጓቸው ጥረቶች ፍሬ አላፈሩም፡፡

ጅቡቲ የአፍሪካ ህብረት ገለልተኛ ታዛቢዎች ጭቅጭቅ ባሉባቸው ስፍራዎች እንዲያሰፍር ጠይቃለች፡፡ ሆኖም ቀደም ሲል የአፍሪካ ህብረት የታዛቢ ቡድንን ያገደችው ኤርትራ ይሄን ሀሳብ አትቀበልም ነው የሚባለው፡፡ ቻይና “ወታደሮቼን ማስፈር እችላለሁ፣” ብላ ነበር፡፡ ከሁለቱም ሀገራት ጋር መልካም ግንኙነቶች ቢኖሯትም ሀሳቡን አገሮቹ ይቀበሉት፣ አይቀበሉት ግልጽ ነገር የለም ነው የሚባለው፡፡

በነገራችን ላይ ኤርትራ ላይ የሚደረገው ዓለም አቀፍ ጫና እንደ በፊቱ አይደለም ይባላል፡፡ ለአስርት ዓመታት ተቆልፋ የቆየችው አገር ከ1998 አሰከ 2000 ከኢትዮጵያ ጋር ካደረገችው ጦርነት በኋላ ለተጣለባት ማእቀብ ያለው ዓለም አቀፍ ድጋፍ ቀስ በቀስ እየቀነሰ፣ እንደውም እየተመናመነ ነው ተብሏል፡፡

‘ፎሪን ፖሊሲ’ የተባለው መጽሔት ይህ የሆነው “ኤርትራ ለአልሸባብ እርዳታ ለመስጠቷ እስካሁንም ተጨባጭ ማስረጃ ስለሌለ ነው፣” ብሏል፡፡ የአውሮፓ ህብረት ኤርትራ ውስጥ ዳኞችንና የጸጥታ አካላትን ለማሰልጠን እገዛ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል፡፡ ብሪታንያ በአስመራ ዓለም አቀፍ የልማት ቢሮ ለመክፈት አቅዳለች ተብሏል፡፡

በዚህ በበታቻችን በኩል ደግሞ በሶማሊላንድ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ በርበራ ላይ ወታደራዊ ሰፈር አቋቁማለች – 25 ዓመታት ልትጠቀምበት ተፈራርማ፡፡ ኤሚሬትስም በርበራ ላይ የባህር ላይ ሰፈር ለመገንባት ከሶማሊላንድ ጋር ተፈራርማለች፡፡

ሶማሊያ የአረብ ሊግ አባል ነች፡፡ የአረብ ሀገራትም በዛች ሀገር የበላይነታቸውን ለማስረጽ ፉክክር ውስጥ ናቸው፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በሶማሊያ ሰፋ ባለ ሁኔታ ተንሰራፍተው የነበሩት እነሳውዲ አረቢያ ነበሩ፡፡ አሁን ግን ኳታርና የተባባሩት አረብ ኤሚሬትስ ገብተዋል፡፡ የአረብ ሀገራቱ የሶማሊያ የተለያዩ ታጣቂ አንጃዎችን በመደገፍ የአገሪቷን መከራ አብሰውታል ነው የሚባለው፡፡

የአገሪቱ ፕሬዝደንት ለጸረ ኳታር የአረብ ሀገራት ቡድን ወግነው ከኳታር ጋር ሰማኒያቸውን እንዲቀዱ ጫናና የገንዘብ ማባባል ሁሉ ተሞክሮባቸው ነበር፣ አልተቀበሉትም እንጂ፡፡

ከወራት በፊት የሳውዲ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ከሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት ውጥረት የበዛበት ውይይት የሳውዲው ባለስልጣን ሞቃዲሾን ካብጠለጠሉ በኋላ ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ካላቋረጡ ከባድ ችግር ላይ እንደሚወድቁ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩን አስጠንቅቀዋቸው ነበር – እሳቸው ግን በእጄ አላሉም፡፡

በዚህ የተነሳ የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ከሳውዲና ከኤምሬትስ የሚያገኘውን ወታደራዊና የመዋዕለ ነዋይ እርዳታ ሊያጣ የሚችልበት ፍርሀት ነበር፡፡

ኤሚሬትስ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሶማሊያ ኮማንዶዎችን ያሰለጠነች ስትሆን ለሶማሊያ መንግሥት ወታደራዊ እርዳታዋን ስታሳድግ ቆይታለች፡፡ ለዚህም ሦስት ግቦች አሏት ነው የሚባለው፡፡ በሶማሊያ ጸረ—የባህር ወንበዴዎች ጥረቶችን ለማሳደግ፣ በአካባቢው እያደገ የመጣውን የቱርክን ወታደራዊ ሃይል መገዳዳር፣ እና ለየመን ዘመቻዋ፡፡ በነገራችን ላይ ቱርክ ሞቀዲሾ ውስጥ ወታደራዊ ሰፈር አላት፡፡ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በሚታየው ‘ስክራምብል ፎር ዘ ሆርን’ የአታቱርክ ሀገርም ገብታበታለች ነው የሚባለው፡፡

ሳውዲና ኤሚሬትስ ከኤርትራ ጋር በ2015 የአሰብን ወደብ፣ ወደቡ አጠገብ ያለን የአይር ሀይል ሰፈርን፣ በቀይ ባህር የኤርትራ ይዞታዎች የሆኑ ደሴቶች ላይ ያሉ ተቋሟትን ለመጠቀም የ30 ዓመት ሊዝ ተፈራርመዋል፡፡ ኤሚሬትስ ከእነኚህ ቦታዎች እየተነሳች የመን ላይ የባህርና የአየር ጥቃት ለማካሄድ ተፈቅዶታል፡፡

ሁለቱ ሀገራት በተጨማሪ ከጅቡቲ፣ ሶማሊላንድና ሶማሊያ ወታደራዊ ሀይላቸውን ለማደርጀትና ዘርፈ ብዙ ለማድረግ የወታደራዊ ትብብር ስምምነቶችን ከየሀገራቱ ጋር ተፈራራመዋል፡፡ ለዚህ ሁሉ ዋናዋ ሰበብ የመን ነች፡፡

“የየመን ችግር ቢፈታ ምን ይፈጠራል፣ ሁሉም ጓዙን እየሸከፈ ወደመጣበት ይመለሳል?” የሚለው እስከዚህ ግራ አያጋባም፡፡ የትኛውም ሀገር ቢሆን ከእንግዲሀ ጦር ሰፈሩን ያጠናክራል እንጂ አይነቅልም ነው የሚባለው፡፡ በነገራችን ላይ አሁን፣ አሁን ደግሞ ሩስያ ሱዳን ውስጥ ጦር ሰፈር ልታቋቁም ትችላላች የሚሉ ወሬዎች እየተናፈሱ ነው፡፡

ተንታኞች እንደሚሉት ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ጦር ሰፈር እያቋቋሙ ካሉት ሀገራት ጋር አደባባይ የወጣ ቁርሾ ባይኖራትም የወታደራዊ ሰፈሮች መብዛት ሊያሳስባት ይችላል ይባላል፡፡ ምክንያቱም በዚህ የተነሳ ኤርትራ የልብ ልብ አግኝታ ወታደራዊ ሀይሏን ለማጠናከር ልትጠቀምበት ትችላለች በሚል ነው፡፡

ኤርትራ ለሪያድም፣ ለአቡዳቢም አካባቢያዊ ትራቴጂ ትልቅ ወሳኝ ናት ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም የተባበሩት መንግሥታት ማእቀብ እየተጣሰ የጦር መሳሪያ ይቀርብላታል የሚል ወሬ ነበር፡፡

እንግዲህ በዚህ ሁሉ መሀል ግብጽ አለች፡፡ ተወደደም ተጠላም የፈርኦኖቹ ሀገር በአካባቢያችን የምታደርገውን አይደለም ወታደራዊ፣ ሌላም እንቅስቃሴ በዓይነ ቁራኛ መከታተል ግድ ይላል፡፡ ግብጽ ከኤርትራ ጋር ያላትን ወታደራዊ ጥምረቷን እየጠናከረች ነው ተብሏል፡፡ እንደውም የረጅም ርቀት ሚሳይሎችን ማስወንጨፍ የሚችል ፈጣን የጦር መርከብን ጨምሮ ተዋጊ ጀልባዎችን በቀይ ባህር አካባቢም አሰማርታለች፡፡

ለምን ? ከዛ ላይ እዚህ ታች ድረስ ጦር መርከብ መቅዘፍ ለምን አስፈለገ ? የኤርትራና የግብጽ ባለስልጣናት መርከቦቹ እዛ መኖራቸው የባህር ላይ ውንብድናን ለመከላከል ነው ይላሉ፡፡ የሚሳይል ሀይል የሚያስፈልጋቸው የባህር ላይ ወንበዴዎች መፈጠራቸውን ብዙም አልሰማንም፡፡ ለዚህ ነው አንዳንድ ተንታኞች ይህን ምክንያት የማይቀበሉት፡፡ “ግብጽ ‘ስትራቴጂያዊ ከበባ’ በሚባለው ስልት ኢትዮዽያን ከአካባቢው ነጥላ ብቻዋን ልታስቀራት ነው የምትፈልገው፣” ይላሉ ተንታኞቹ፡፡

እዛ ማዶ ሆኖ ክፉ ሰው ተጣራ

እዚህ ማዶ ሆኖ ክፉ ሰው ወይ አለው

ጎበዝ ጠንቀቅ በል ይሀ ነገር ለእኛ ነው…

ማለት ደረጃ እንደማንደርስ ምኞታችን ነው፡፡ “ንቀውናል፣ ከበውናል፣ ብታምኑም ባታምኑም ቀለበት ውስጥ ከተውናል፣” ማለት ደረጃ እንደማንደርስ ምኞታችን ነው፡፡

LEAVE A REPLY