ኢሕአዴጎች የጀርመናዊውን የካርል ሽሚትን “ፖለቲካ በጓደኛሞች መካከል ያለ ልዩነት ነው”የሚለውን መርህ ተቀብለዋል...

ኢሕአዴጎች የጀርመናዊውን የካርል ሽሚትን “ፖለቲካ በጓደኛሞች መካከል ያለ ልዩነት ነው”የሚለውን መርህ ተቀብለዋል /ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ/

ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ለረዥም ዓመታት ፍልስፍናን አስተምረዋል፡፡ ለሦስት አሥርት ዓመታት ገደማ ከኖሩበት አሜሪካ መጥተው ኢትዮጵያ መኖር ከጀመሩ ዘጠኝ ዓመታት አልፏቸዋል፡፡ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ በመስጠትም ይታወቃሉ፡፡ ሰለሞን ጎሹ አበክረው በሚጽፉባቸው ርዕሶችና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡– ከ2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫ በኋላ ባሉት ሦስት ዓመታት የሚስተዋሉት የፖለቲካ ሁኔታዎች ለየት ያሉ ናቸው፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በገዥው ፓርቲና በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ተቃውሞና አመፅ ተስተውሏል፡፡ የገዥው ፓርቲ አባል ፓርቲዎችና ልሂቃንም ይፋ የወጣና ውስጥ ለውስጥ የሚከናወን የፖለቲካ ትግል ውስጥ መሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡ ክልላዊና አካባቢያዊ አስተዳደሮችም የተለያዩ ጥያቄዎችን እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ፖለቲካዊ ተቃርኖዎችና አለመግባባቶች ጠቅለል ያለ መነሻ ምንድነው?

ዶ/ር ዳኛቸው፡- የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝምና ዴሞክራሲ እያዘገሙ ለበርካታ ዓመታት ተጉዘዋል፡፡ ነገር ግን በአራት ነጥቦች ዙሪያ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ አንደኛው የፖለቲካ ግንኙነት ላይ ነው፡፡ ሁለተኛ የነፃነት ግንኙነት ላይ ነው፡፡ ሦስተኛው የኃይል ግንኙነት ላይ ነው፡፡ አራተኛ የንዋይ ግንኙነት ላይ ነው፡፡ በሒደት እነዚህ የግጭት ካስማዎች ተፈጥረዋል፡፡ በተጨማሪም በፍትሕ ላይ ጥያቄዎች እየመጡ ነው፡፡ ክልሎችን የሚመሩ ኃይሎች በእነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያ አንዳንድ ነገሮች ይደረግልን እያሉ ይመስለኛል፡፡ እስካሁን የተዘረጋው የፌዴራሊዝም ሥርዓት አድሎአዊና አንድን ፓርቲ ብቻ የሚደግፍ በመሆኑ እንደገና መዋቀር አለበት የሚል ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ይኼ የኃይል ጥያቄ ነው፡፡ ዴሞክራሲው ደግሞ በአግባቡ እየሠራ አይደለም፡፡ ፌዴራሊዝሙ ዴሞክራቲክ ሊሆን አልቻለም፡፡ የኢኮኖሚ አደረጃጀቱና ግንኙነቱም ላይ ጥያቄ እየተነሳ ነው፡፡ በሀብት ክፍፍል ዙሪያም የአንድ ወገን ተጠቃሚነት በገሃድ እየታየ ነው የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ እየቀረበ ነው፡፡

ሪፖርተር፡– አውራ ፓርቲና ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችን እንደ ጠላት መፈረጅን ጨምሮ የአገሪቱ መሠረታዊ ችግሮች ምንጭ የኢሕአዴግ ርዕዮተ ዓለም ነው በማለት የሚከራከሩ ተንታኞች አሉ፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች የሊበራል ፍልስፍናን ወዳቀፈው ሕገ መንግሥት መመለስ እንዳለበት እየገለጹ ነው፡፡ ሊበራል ዕርምጃዎችን መውሰድ በአገሪቱ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ምን ያህል ጠቃሚ ነው?

ዶ/ር ዳኛቸው፡- ኢሕአዴጎች ሲጀምሩ ሶሻሊስቶች ነን ነበር የሚሉት፡፡ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ አዲስ ነገር የመቀበልና ተግባር ተኮር የመሆን አዝማሚያ አሳይተዋል፡፡ ሆኖም ግን አንዳንድ ያልተላቀቋቸው ብሂሎች አሉ፡፡ ኢሕአዴጎች የጀርመናዊውን የካርል ሽሚትን “The Concept of the Political” ጽሑፍና አስተምህሮ አንብበውትም ይሁን ሳያነቡት፣ “Politics is the Discrimination Between Friends and Foes” የሚለውን መርህ ተቀብለዋል፡፡ እንግዲህ ለሽሚት ፖለቲካ ማለት ወዳጅን ከጠላት የመለየት ተግባር ነው፡፡ ለኢሕዴጎች ሌላው ቀርቶ ድህነት እንኳን በጠላትነት ነው የተፈረጀው፡፡ ጠላት እንደ ሞተር ነው የሚታየው፡፡ ሁሉንም ነገር ከወዳጅና ጠላት አንፃር ነው የሚመለከቱት፡፡ በአገሪቱ ያለው ጠላት ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚቀያየር ነው፡፡ ዛሬ ጠላት የሆነ ነገ ደግሞ ወዳጅ ሊሆን ይችላል፡፡ ወዳጅና ጠላት ብለህ ከለየህ በኋላ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመከተል በጣም ያስቸግራል፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌላውም ታዳጊ አገር እ.ኤ.አ. ከ1980ዎቹ መጨረሻ በኋላ ወደ ሥልጣን የመጡት መንግሥታት ስለዴሞክራሲ ያወራሉ፡፡ እንዲያውም ሦስተኛው የዴሞክራሲ ንፋስ/ማዕበል የመጣበት ወቅት እንደሆነ የሚወስዱትም አሉ፡፡ ከወታደራዊ መንግሥታት በተቃራኒ ኢሕአዴጎችም ስለዴሞክራሲ ያወራሉ፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማትንም አቋቁመዋል፡፡ ነገር ግን የእነዚህን ተቋማት ዓላማ አስተው ለራሳቸው ጥቅም ብቻ ነው የሚጠቀሙባቸው፡፡ ዴሞክራሲ በ‹ቶታሊቴሪያን› መንግሥት ሕዝቦችንና ዜጎችን ያገለግላሉ የሚባሉትን እንደ መገናኛ ብዙኃን፣ ሲቪል ማኅበራት፣ ምርጫ አስፈጻሚና ፍርድ ቤት ያሉ ተቋማት ለሕዝብ የቆሙ ናቸው፡፡ ኢሕአዴጎች እነዚህ ተቋማት የነፃነት መሣሪያ እንደሆኑ ካወጁ በኋላ በተግባር ግን ለራሳቸው ፖለቲካዊ ጥቅም ብቻ ይጠቀሙባቸዋል፡፡

መንግሥት ሁለት የጭቆና መሣሪያዎች አሉት፡፡ አንደኛው ከፖሊስ፣ ከወታደርና የፀጥታ ኃይል የተውጣጣ ነው፡፡ ሁለተኛውን የሚያቋቁሙት እንደ ሲቪል ማኅበር ያሉ ተቋማትን በመጠቀም ለጭቆናው ማስፈጸሚያ እንዲመቻቸው የራሳቸውን ሰዎች በማደራጀትና በማስረግ ውስጥ ገብተው ዓላማቸውን እንዲስቱ በማድረግ ነው፡፡ ከአፈጻጸም አንፃር በመጀመርያ መንግሥት ጭቆናውን በእነዚህ የዴሞክራሲ ተቋማት አማካይነት ይፈጽማል፡፡ በእነዚህ ተቋማት አማካይነት መፈጸም ሲያቅተው ግን ፖሊሶችን፣ ወታደሮችንና የፀጥታ ኃይሎችን መጠቀም ይጀምራል፡፡ ሌላው በአገራችን ስለዴሞክራሲና ሊበራሊዝም ያለው አረዳድ የተጣረሰ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ስለሥልጣን አወቃቀር፣ ሥልጣን ስለሚገኝበት ሥርዓት፣ እንዲሁም የተቋማት ሚናን ነው የሚያስረዳው፡፡ ዴሞክራሲ በዋናነት አንድን ሕዝብ ከአምባገነናዊ ኃይል የሚጠብቅ ነው፡፡ ሊበራሊዝም ደግሞ ስለነፃነትና ስለሰብዓዊ መብት ነው የሚያወራው፡፡ እነዚህ ዘግይተው ወደ ዴሞክራሲ የመጡ አገሮች ሊበራሊዝም ላይ ብዙ አልሠሩም፡፡ የሕግ የበላይነት፣ ሰብዓዊ መብትና ነፃነት ላይ በጣም ችግር አለባቸው፡፡

ፋሪድ ዘካርያ የተባለ አሜሪካዊ ጸሐፊና የሚዲያ ባለሙያም ዴሞክራሲ ያለ ሊበራሊዝም መሠረታዊ ችግር እንዳለበት ጽፏል፡፡ ዴሞክራሲ ለወሬ ይመቻል፡፡ በተለይም በሦስተኛው የዴሞክራሲ ማዕበል ተብሎ ከሚጠራው ወቅት በኋላ ዴሞክራሲን መተግበር የጀመሩ በርካታ አገሮች ዴሞክራሲን እያሳደግን ነው ቢሉም ሊበራሊዝም ግን እያደገ አይደለም፡፡ እንዲያውም ገና ጀማሪ ዴሞክራሲ ስለሆነ ስህተት ቢኖር ምናለበት? ይላሉ፡፡ ነገር ግን ትልቁ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ጂዮቫኒ ሳርቶሪ በትክክል እንዳሉት፣ ሰብዓዊ መብትን ለማክበር ጀማሪና ጨራሽ መሆን አስፈላጊ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ጋዜጠኛን አለማሰር፣ ሰውን ስታስር ያለመግረፍ፣ ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ጥይት አለመተኮስ፣ ሰው መግደል ትክክል አለመሆኑን ለምን ያህል ጊዜ ነው የምትማረው? ይህች አገር እኮ ጥንታዊና ብዙ የሚያውቅ ሕዝብ ያለባት ነች፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ጅምር ዴሞክራሲ ሦስት ዓበይት የሆኑ መሰናክሎች አሉበት፡፡

አንደኛ ወደ ዴሞክራሲ መንገድ ለመግባት የመሪዎች ፍላጎት ያስፈልጋል፡፡ ባዶ ልፈፋ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ዴሞክራሲን ለማስፈን ሥልጣን ላይ ገደብ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ በተግባር ግን በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲባል እየተገደበ ያለው ዴሞክራሲያዊ ውሳኔ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓቱ ነው፡፡ ሁለተኛ የዴሞክራሲ ባህል ወሳኝ ነው፡፡ የመብትና የነፃነት ረገጣው ከመንግሥት ተቋማት ብቻ የሚነሳ አይደለም፡፡ በሕዝቡ፣ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በግል ተቋማትና በመሳሰሉትም የሚስተዋል ነው፡፡ ሦስተኛ ተቋማት በጣም አስፈላጊ ናቸው፡፡ ነፃና ገለልተኛ የሆኑ ተቋማትን ገና አልገነባንም፡፡ የራሳቸውን ልዕልና ያላከበሩ ተቋማት የዜጎችን ነፃነት ሊያስከብሩ አይችሉም፡፡ በአገራችን አስፈጻሚው የመንግሥት አካል በሕግ አውጭውና በሕግ ተርጓሚው ሥራ ውስጥ ጣልቃ ሲገባ ታየዋለህ፡፡ አንድ ትልቅ ዝሆን በመሆን ራሱ እየፋፋና እያደገ ሌሎቹን ተቋማት ሁሉ እያቀጨጨና እየዋጠ ነው፡፡ ለስሙ ብዝኃነት ይባላል እንጂ አንድ ወጥ የሆነ አሠራር ነው ያለው፡፡ ኢሕአዴግ ካለፈው አስከፊ ሥርዓት ቢያላቅቀንም የራሱን አዲስ ቀንበር ግን ጭኖብናል፡፡ ዜጎች ምሉዕ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ፍትሐዊ ነፃነት ይጎናፀፉ ዘንድ የዴሞክራሲና የሊበራሊዝም መስተጋብር የግድ ይላል፡፡ የአገራችንን ፖለቲካ ዴሞክራሲ ከሚጠይቀው ሕዝባዊ ተሳትፎና ሊበራሊዝም ከሚሻው መንግሥታዊ ተጠያቂነት አንፃር ስንመለከተው ትልቅ ጉድለት አለበት፡፡ ለኢሕአዴግ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማለት አስቀድሞ የወሰነውን ነገር ባለድርሻ አካላት የሚላቸውን የራሱን ወኪሎች መርጦ ውሳኔዎች በተሳትፎ የተገኙ ማስመሰል ነው፡፡

ሪፖርተር፡– ከ1993 ዓ.ም. የሕወሓት ወይም የኢሕአዴግ ክፍፍል በኋላ በመንግሥት ወይም በገዥው ፓርቲ በተግባር እየዋለ የሚገኘው የልማታዊ መንግሥት የዕድገት ሞዴል ወይም ርዕዮተ ዓለምን ተፅዕኖ እንዴት ይገመግሙታል?

ዶ/ር ዳኛቸው፡- ኢሕአዴግ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያስገኙልኛል ብሎ ቀደም ብሎ አስቀምጧቸው የነበሩ ነገሮችን በሒደት ለውጧል፡፡ መጀመርያ አካባቢ ሕገ መንግሥቱን በመጠቀም ዴሞክራሲን በመገንባት፣ ሰብዓዊ መብትን በማክበርና በማስከበር፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ በማካሄድ የሕዝቡን ድጋፍ ማግኘት እችላለሁ ብሎ ያስብ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን ይህ እንደማያዋጣው ገባው፡፡ አሁን አንድ ደጀን ይዞ ነው የተቀመጠው፡፡ ይኼውም የተሻለ አፈጻጸም ወይም ልማት ማሳየት ነው፡፡ ብዙ ድልድይ፣ ግድብና መንገድ እንገነባለን ነው የሚሉት፡፡ ልማት ስላመጣን፣ ዕድገት ስላስመዘገብን ቅቡልነት ይኖረናል ብለውም ያስባሉ፡፡ ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ ስለዕድገትና ልማት አብዝተው ያወራሉ፡፡ ከልማት አንፃር አገሪቱ ካለፈው ጊዜ የተሻለ ደረጃ ላይ ናት፡፡ ነገር ግን የሕዝቡን ታታሪነትና ሥራ ወዳድነት ወደ ጎን በመተው ሁሉን ነገር በራሱ ብቻ እንዳስገኘው አድርጎ ለማሳየት ይጣጣራል፡፡

ሪፖርተር፡– በሥራ ላይ ያለው ብሔር ተኮር የፌዴራል ሥርዓት አሁን አገሪቱ ለገባችበት ችግር ተጠያቂ ነው በማለት የሚከራከሩ አሉ፡፡ አንዳንዶች ግን ሥርዓቱ ችግር ውስጥ የገባው የዴሞክራሲ ዕጦት ስላለበት ነው እንጂ በራሱ የሚነቀፍ አይደለም በማለት ይከራከራሉ፡፡ የብሔርተኝነትን ስሜት ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ይቻላል?

ዶ/ር ዳኛቸው፡- የብሔሮች እኩልነት መስፈን አለበት የሚለው መርህ ተገቢ ነው፡፡ አንዱ ብሔር የበላይ ሌላው የበታች መሆን የለበትም፡፡ ነገር ግን ዝም ብሎ እኩልነት ተብሎም መተው አልነበረበትም፡፡ እኩል ስለሆንክ አብረህ ትኖራለህ ማለት አይደለም፡፡ በአንድ በኩል እኩል ነህ ይባላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይኼ ብሔር ሲበድልህ ነው የኖረው ተብሎ የበደል ወሬ ይወራል፡፡ እንደ የወንድማማችነትና የጋራነት እሴቶች (Fraternity and Communality) ያሉ አብሮ ለመኖር የሚያስችሉ ግብዓቶች አልተሠራባቸውም፡፡ ከ25 ዓመታት በኋላ አሁንም ስለመቻቻል ነው የምናወራው፡፡ መቻቻል ብዙ አሉታዊ አንድምታዎች አሉት፡፡ ትንሽ ብንሠራ ኖሮ አንድ ደረጃ ከፍ ብለን ስለመገናዘብ እናወራ ነበር፡፡ መገናዘብ ከመቻቻል ይልቃል፡፡ ከዚያ ደግሞ አንዱ ሌላውን መቀበል ይመጣል፡፡ ዋናው ችግር ግን የሥልጣን መዋቅሩ ላይ ነው ያለው፡፡ ለመጫወት የተስማማህበትን ሕግ ሳይስማማህ ሲቀር በመሀል መቀየርና ማጠፍ አትችልም፡፡ የምትጫወትበትን ሕግ በመሀል ካፈረስከው ጨዋታውም አብሮ ይፈርሳል፡፡ ሥልጣንን ለማስቀጠል የሚደረገው ትግል ዴሞክራሲውንና ፌዴራሊዝሙን እየጨፈለቀው ነው፡፡

ሪፖርተር፡– በሕገ መንግሥቱ የተቋቋመው ፌዴራላዊ አወቃቀር በአገሪቱ የቡድንና የግለሰብ መብቶች አንዳቸው በሌላኛው ላይ ያልተፈለገ ተፅዕኖ ሳያሳርፉ ጎን ለጎን እንዲተገበሩ ያለመ ነው፡፡ በተግባር ግን መንግሥት ለግለሰቦች መብት ትኩረት አይሰጥም ተብሎ ይወቀሳል፡፡ ለዚህ እንደ አብነት የሚጠቀሰው የዜጎችን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትና የሚዲያ ነፃነትን የሚገድቡ ዕርምጃዎችን በተደጋጋሚ መውሰዱ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?

ዶ/ር ዳኛቸው፡- ቀደም ብሎ የቡድንና የግለሰብ መብቶችን ጎን ለጎን ማስኬድ አይቻልም የሚል ክርክር ነበር፡፡ አሁን ግን ሊቀራረቡ ይችላሉ የሚል አስተሳሰብ እየመጣ ነው፡፡ ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ መብት አንፃር የቡድንና የግለሰብ መብቶች በአገራችን እየተከበሩ ነው ማለት አልችልም፡፡ ነፃነትን በተመለከተ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት እየተገበረ ነው ከተባለም መንግሥት መርዳት፣ ማገዝና ማሟላት የሚገባው ነፃነት እንጂ ራሱን ማቀብና ጣልቃ ከመግባት ሊቆጠብ የሚገባውን ነፃነት አይደለም፡፡ ይኼ ልዩነት ላይ በሰፊው የጻፈው ሰር አይዛያ በርሊን ነው፡፡ የመጀመርያው ዓይነት ነፃነት የሚያተኩረው መሆን ላይ ነው፡፡ አይዛያ በርሊን ‹‹ፖዘቲቭ ሊበርቲ›› ይለዋል፡፡ ኦሮሞ መሆን፣ ሙስሊም መሆን እንደማለት፡፡ ሁለተኛው ዓይነት ነፃነት ማለት ደግሞ ከሆነ አካልና ጉዳይ ነፃ መሆን ወይም መጠበቅ ማለት ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ከሚወድቁት መካከል በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ የመሰብሰብና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ‹‹ነጌቲቭ ሊበርቲ›› ይላቸዋል አይዛያ በርሊን፡፡ እነዚህ መብቶች በሰፊው የተገደቡ ናቸው፡፡ ዜጎች እንዲህ ዓይነት ነፃነትና መብቶች እንዲተገበሩ መንግሥት ጣልቃ ያለመግባትና መታቀብ ያለበት ሲሆን፣ እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ እናገራለሁ ስትል ስለማንና ስለምንድን ነው የምትናገረው? ትባላለህ፡፡ በአደባባይ መንግሥት ላይ ተቃውሞ ማቅረብ ከባድ ነው፡፡

የዶ/ር መረራ ጉዲና መጽሐፍ እንዳይገመገም ለ35 ዓመታት ያስተማሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ከልክለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ከሌለ ሌላ የት ቦታ እንዲኖር እጠብቃለሁ፡፡ ሚዲያው የኢሕአዴግን ሐሳብ ለማስተጋባት የተደራጀ ነው የሚመስለው፡፡ ለኢሕአዴግ ግለሰቡ ያለ አይመስለውም፡፡ እንደ ብሔርና ጎሳ ያለው የቡድን መብት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ባልተረጋገጠበት አገር የግለሰቡ መብት የቡድን መብትን ሊገዳደርና ሁለቱን መብቶች ለማመጣጠን የምንችልበት ምኅዳር ለመፍጠር በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ማክበር ከብዶታል፡፡ ይኼ መብት የግለሰቡ ብቻ ሳይሆን እንደ ሲቪል ማኅበራት ያሉ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትም መብት ነው፡፡ ለመናገር አዳራሽ የማታገኝ ከሆነ ይህን መብት ተግባራዊ ልታደርግ አትችልም፡፡ ኢሕአዴግ እኮ በአገሪቱ ተገቢ የሆኑ ጥያቄዎችና መልሶችን ሁሉ ይነግርሃል፡፡ በአገሪቱ ብዙ ትክክለኛ የሆኑ ጥያቄዎችና መልሶች አሉ፡፡ መንግሥትን ተጠያቂ ለማድረግ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ የሆነ ሚዲያ መኖሩ የግድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡– የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ከምርጫ 97 በፊትና በኋላ ምን ዓይነት የተለየ ገጽታ አለው?

ዶ/ር ዳኛቸው፡- ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙ ችግር ነው ያለባቸው፡፡ አንዳንዶቹ ተቃዋሚም አይመስሉኝም፡፡ ዓላማቸውን ስተው የገዥው ፓርቲ መሣሪያ የሆኑ አሉ፡፡ ኢሕአዴግ ጠንካራ ተቃዋሚ እንዲወጣ አይፈልግም፡፡ እኔ ራሴ ለዚህ ምስክር ነኝ፡፡ ሁለት ፓርቲዎችን ለማስታረቅ ጫፍ ላይ ከደረስን በኋላ በሚፈራረሙበት ቀን የደረሰብንን ችግር በደንብ ነው ያየሁት፡፡ ከኢሕአዴግ የሚመጣ ጫና አለባቸው፡፡ የራሳቸውም ድክመት አለ፡፡ ሕዝባዊ ተቀባይነት ማግኘት አልቻሉም፡፡ ብዙ አማራጭ ሐሳብም ይዘው ሊቀርቡ አልቻሉም፡፡ ፓርቲ አቋቁሞ ለመንቀሳቀስ የሚመች የፖለቲካ ምኅዳርም የለም፡፡ በወረቀት ላይ ያለው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት በተግባር እየታየ አይደለም፡፡ መንግሥት ላይ ጠንከር ያለ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች ሲፈርሱ በተደጋጋሚ ዓይተናል፡፡ በእኔ እምነት ምርጫ ቦርድ አንድነት ፓርቲን አፍርሶ ለማይገባው ሰው ነው የሰጠው፡፡ ፓርቲው ጠንካራ ተገዳዳሪ የመሆን አቅም የነበረው ቢሆንም፣ አሁን ሰውየው ኢሕአዴጋዊ መስመሩን እየገፋ ነው ያለው፡፡ ይኼ መንግሥትን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ሊያሳስብ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡– ከኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ በአብዛኛው ከወጣቶች የተውጣጣ መሆኑ አገሪቱን የለውጥ ኃይሎች ባለፀጋ እንዳደረጋት ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ይህን ኃይል በአግባቡ ለመጠቀም ግን የትምህርት ሥርዓቱ በተገቢው መንገድ መዋቀርና መሥራት እንዳለበት ያመለክታሉ፡፡ በአገሪቱ የተመሠረተው የትምህርት ሥርዓት የተለያዩ ችግሮች እንዳሉበት የእርስዎ ሥራዎች ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ምንድን ናቸው? ከምንስ የመጡ ናቸው?

ዶ/ር ዳኛቸው፡- ገዥው ፓርቲ ቁጥር ላይ ነው ትኩረት ያደረገው፡፡ ከተደራሽነት አንፃር ብዙ ሺሕ ትምህርት ቤቶች መከፈታቸው በጎ ነገር ነው፡፡ አንድ አሜሪካዊ ፈላስፋ ‹‹ፍርድ ቤት ሄደህ ዳኝነት አታገኝ ይሆናል፣ ያለ ፍርድ ቤት ግን ዳኝነት የለም፤›› ይላል፡፡ በተመሳሳይ ትምህርት ቤት ሄደህ ጥራት ያለው ትምህርት ላታገኝ ትችላለህ፡፡ ያለ ትምህርት ቤት ግን ትምህርት የለም የሚል የግል አቋም አለኝ፡፡ እኔ ትምህርትን የምተረጉምበት መንገድና መንግሥት ወይም ገዥው ፓርቲ ትምህርትን የሚተረጉሙበት መንገድ ይለያያል፡፡ እነሱ አንድ ሰው ተማረ የሚሉት ሰውዬው በሆነ ሙያ ሠልጥኖ ወይም ቴክኒክ ተምሮ ማኅበረሰብ ውስጥ ገብቶ የተወሰነ ሥራ ሲሠራ ነው፡፡ የሙያ ትምህርትና ትምህርት ቤት በቅጡ የተለዩ አልመሰለኝም፡፡ ትምህርት ግን አንድን ሰው ሰው ለማድረግና ለመቅረጽ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው መታወቅ አለበት፡፡ የፍልስፍናና የነገረ መለኮት ምሁር ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስ የትምህርት ተቀዳሚ ሥራ የሰውን ልጅ አዕምሮ ለዕውቀት ማብቃት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ መንግሥት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይልቅ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ኢንቨስት ቢያደርግ ይሻላል፡፡ አስተማሪዎችና የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻል ኢንቨስት ማድረግ አለበት፡፡

የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች ልዩነት በየጊዜው እየሰፋ መጥቶ አሁን የመሬትና የሰማይ ያህል ተራርቀዋል፡፡ የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከሥር በደንብ ይማራሉ፡፡ ድሮ ግን ተፈሪ መኮንንና ዊንጌት ከሴንት ጆሴፍና ከእንግሊዝ ስኩል ቢበልጡ እንጂ አያንሱም ነበር፡፡ ያለ ትምህርት አገር ፎቀቅ አትልም፡፡ የትምህርት ሥርዓቱን በተመለከተ በርካታ ውይይቶችና ስብሰባዎች የሚካሄዱ ቢሆኑም፣ የፖለቲካ ካድሬዎችን እንጂ ገለልተኛ ባለሙያዎችን አያሳትፉም፡፡ ቢያሳትፉም ለይስሙላ እንጂ ሐሳባቸውን ለመቀበል አይደለም፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችንን እስካሁን እየመሩ ያሉ ግለሰቦች ፒኤችዲ ይኑራቸው እንጂ የአመራር ብቃትና ዝግጁነት የላቸውም፡፡ ለትምህርት ተቋማት አንፃራዊ ነፃነት ሊሰጥ ይገባል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ዓለም አቀፋዊነትና ብዝኃነትን ይዘው መገኘት አለባቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ከተለያየ ባህል፣ ወግና ታሪክ የሚመጡ ተማሪዎች ከሚማሩት መደበኛ ትምህርት ባሻገር እርስ በርሳቸው ልምድና ተሞክሮ ሊለዋወጡና ሊቀስሙበት የሚያስችል ማዕከልም ነው፡፡ በአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ይዘዋቸው የሚመጡትን አንዳንድ አሉታዊ ዕይታዎች ወይም ግንዛቤዎች አፍርሰው፣ አዎንታዊ በሆኑ ነገሮች መተካት የሚችሉባቸው ማዕከላት መሆን ሲገባቸው ተሸክመዋቸው የመጡትን ነገሮች እያጠናከሩ የሚመረቁባቸው ተቋማት ሆነዋል፡፡

ወጣቱ ወሳኝ የሆነ የማኅበረሰብ አካል ነው፡፡ ወጣቱ አዲስ ሐሳብ ለመቀበል የተዘጋጀ ኃይል ነው፡፡ ነገር ግን መማር አለበት፡፡ ወጣቶች ሲማሩ ግን የራሳቸውን መንገድ ቢከተሉ ጥሩ ነው፡፡ አሁን አንዳንድ የቀድሞውን ትውልድ አባላትን እየተኩ ያሉ ወጣቶች የእነሱኑ መንገድ ሲከተሉ እያየሁ ነው፡፡ ወጣቶችን በጥቅም እያማለሉ ካድሬ የማድረግ የኢሕአዴግ አካሄድም የሚያዋጣ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው ባለፉት ጥቂት ዓመታት በነበሩ አመፆችና ተቃውሞዎች መንግሥት ላይ በዋነኛነት ተቃውሞ

LEAVE A REPLY