ማዕከላዊ እስር ቤትን መዝጋቱን ትንሽ ብታቆዩት /ክንፉ አሰፋ/

ማዕከላዊ እስር ቤትን መዝጋቱን ትንሽ ብታቆዩት /ክንፉ አሰፋ/

የደርግ ባለስልጣናት በአስራ አንደኛው ሰዓት ላይ ከርቸሌን ማሰማመር ጀምረው ነበር። በወቅቱ ምን እንደታያቸው ግልጽ ባይሆንም፤የኋላ ኋላ ግን ያንን ማድረጋቸው እንደጠቀማቸው አይተናል።

በጅምር ላይ ከነበሩ የልማት ተቋማት ይልቅ ይህ የእስር ቤት ግንባታ ቅድሚያ ተሰጠውና፣ ከርቸሌ ቅጥር ግቢ ውስጥ “አለም በቃኝ” የተሰነውን ክፍል እንዲገነባ አደረጉ። በመጨረሻም “አለም በቃኝ” የደርጎች ማረፍያ ስፍራ ሆነች። ግንቦት 1983 ወያኔ ቀን ወጥቶለት የእስር ቤቱን ቁልፍ ሲረከብ ሁሉንም እዚያ አጎራቸው። አብዛኞቹ የደርግ ባለስልጣናት ይህችን አለም ከዚያው ተሰናበቷት።

ለምስክር የቀሩት ጥቂቶቹ የሰው ልጅን መግደል፣ ማሰቃየት እና ማሰር ምን እንደሆነ የገባቸው በሰፈሩት ቁና ሲሰፈርባቸው ነበር። እነ ፍቅረ-ስላሴ ወግደረስና እነ ፍሰሃ ደስታ በህይወት ዘልቀው የይቅርታ ግዜ አግኝተዋል።

ዛሬ ኃይለማርያም ደሳለኝ ማዕከላዊ እስር ቤትን ህወሃት ሊዘጋው እንደሆነ ነግረውናል። በአስራ አንደኛው ሰዓት ያባነናቸው ነገር ምናልባት እንደ ደርግ ዞሮ መግቢያችን ይህ ስፍራ ይሆናል ብለው ይሆን?

ግራም ነፈሰ ቀኝ – ይህ ያልተጠበቀና ከበድ ያለ ውሳኔ ነው። ምክንያቱ ግልጽ ባይሆንም ከውሳኔው በስተጀርባ ምን እንዳለ ግን መገመት አያደግትም። ህወሃት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ድብደባ እና ስቃይ ሲፈጽምበት የነበረው ስፍራ፣ የሺዎች ህይወት እያለፈበት ያለ የቶርቸር ቻምበር፣ አካላዊና ብቻ ሳይሆን ስነ-ልቦናዊ ስብራት ሲፈጸምበት የነበረ የምድር ሲዖል በመዘጋቱ የተቀላቀለ ስሜት መፍጠሩ አይቀርም።

መዘጋቱ መልከም ነገር ነው። ግን ይህ የምድር ሲዖል ከጅምሩ በዚያች ምድር መኖር አልነበረበትም። እኔም በዚያ አልፍያለሁና የትግራይ ተወላጆች መብቱን ያወቀ ዜጋ ላይ ይፈጽሙት የነበረውን ሁሉ ጠንቅቄ አውቀዋለሁ። ከኤሌክትሪክ ገመድ ግርፋት እስከ፣ለረጅም ጊዜያት እጅና እግር የህዋሊት መታሰር፣ የወንዶች ብልት ላይ እስከ አንድ ሊትር የሚደርስ የጠርሙስ ውሃ ማንጠልጠልና ብልቱ ላይ የበቀለውን ፀጉር በክብሪት ማቃጠል፣… ወዘተ በወገን ላይ የሚደርሱ የስቃይ አይነቶች ናቸው። በተለይ ደግሞ ሳይቤሪያ ተብሎ የሚጠራው የ“ጨለማ ቤት” ስቃይ ባእዳን እንኳን ይፈጽሙታል ብሎ ማሰብ ይከብዳል።

ህገ ወጥ ተግባራትን የሚፈጽም ማዕከል መዝጋቱ እና የፖለቲካ እስረኞችን መፍታቱ ከበጎ ፈቃድ የመጣ ቢሆን መልካም ነበር። ህወሃት በህዝባዊ እንቢተኝነት እጁ ሲጠመዘዝ ይህንን መናገሩ፣ ጥቂት ትንፋሽ ለመውሰድ መሆኑን ልንዘነጋው አይገባም።

በአስር ሺዎች የሚገመቱ የህሊና እስረኞች እንዳሉ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሲዘግቡ፣ እስከዛሬዋ የሃይለማርያም መግለጫ ድረስ ወያኔ የሚነግረን በፖለቲካ አመለካከታቸው የታሰሩ ወገኖች እንደሌሉ ነበር። ይህችን መሪር ሃቅ አምነዋል። ዜጋን በፖለቲካ አመለካከቱ መሰር እና ማሰቃየት በአለም አቀፍ ህግ እንደሚያስጠይቅም ግንዛቤ መውሰዳቸው የግድ ነው። እነዚህ የፓለቲካ እስረኞች የታሰሩት ፍትሃዊ ስርዓት በሃገሪትዋ እንዲሰፍን መሆኑንም በነካ እጃቸው ሊናገሩት ይገባል። ማእከላዊ እስር ቤት ከመፍረሱ ወይንም የህሊና እስረኞች ከመፍታት ባሻገር ፍትሃዊ ስርዓት ሲኖር ብቻ ነው ሃገሪቱ ከገባችበት ማጥ ልትወጣ የምትችለው።

የሕግ የበላይነት ሳይሆን የህወሓት የበላይነት አሁንም የሚቀጥል ከሆነ ወያኔ በሰላም ሊኖር አይችልም።

እንፈታለን! እንዘጋለን ብለዋል። ስንቱን የስቃይ እስር ቤት እንደሚዘጉ እና ስንቱን የህሊና እስረኛ እንደሚፈቱ ደግሞ የምናየው ነገር ነው።

LEAVE A REPLY