/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፦ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአማራና ትግራይ ክለቦች መካከል የሚደረጉ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲካሄዱ ተወሰነ
መቀሌና ውልዋሎ ዩ. የእግር ኳስ ክለቦች ከፋሲልና ወልድያ ጋር የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲደረጉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ትናንት ወሰነ።በኢትዮጵያ ፕሪሜርሊግ ውስጥ የሚሳተፉት መቀሌና ውልዋሎ ዩኒቨርሲቲ የእግር ኳስ ክለቦች ከፋሲልና ወልድያ ጋር የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲደረጉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ወስኗል።
ወልድያ ከነማ ከወልዋሎ ዩ. የፊታችን ሰኞ ታህሳስ 30/2010ዓ.ም ከቀኑ 10:00 ሰዓት አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ የሚካሄድ ሲሆን ፋሲል ከነማ ከመቀሌ ድግሞ ቅዳሜ ጥር 5/2010ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰአት አዲስ አአበባ ስታዲየም ላይ ይካሄዳል። እንዲሁም ወልድያ ከመቀሌ ረቡዕ ጥር 9/2010ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ እንደሚካሄድ ፌዴሬሽኑ ያወጣው መርሀ-ግብር ያመለክታል።
በአማራና ትግራይ የእግር ኳስ ክለቦች መካከል ከአምና ጀምሮ በደጋፊዎቻቸው መካከል ከፍተኛ ግጭቶች ሲደረጉ መቆየታቸው የሚታወቅ ሲሆን ፌዴሬሽኑ የመርሀ ግብር ለውጥ ያደረገውም ባለፈው ወር በወልዲያ ከተማ ህይወት የጠፋበት ግጭት መፈጠሩን ተከትሎ እንደሆነ ይታመናል።
በ10ኛው የፕሪሜርጉ ጨዋታዎች ወልዋሎ ዩ. ከወልድያ ከነማ እሁድ አዲግራት ላይ እንዲሁም ፋሲል ከመቀሌ ጎንደር ላይ ሊያካሂዱት የነበረው ጨዋታ ነው ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም እንዲዘዋወር የተደረገው።