ኦሮሞና አማራ ቢጠላሉ ኖሮ ለምን ይጋቡ ነበር?

ኦሮሞና አማራ ቢጠላሉ ኖሮ ለምን ይጋቡ ነበር?

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ሸገር ታይምስ ከተባለ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለ አማራና ኦሮሞ በርካታ ምስክሮችን ሰጥተዋል።እንዲያነቡት ተጋብዘዋል።

*****

ሸገር ታይምስ፡- ኢትዮጵያዊነት ደብዝዟል እያሉኝ ነው ማነው ከዚህ ድብዘዛው የሚያድነው?

አቶ ቡልቻ፡- በአብዛኛው ትግራይ ነጻ ለመሆን ፈልጎ ነበር፡፡ እንዲያውም ከነፃነት ውጭ ሌላ ነገርም አያስቡም ነበር። ይሄ ከብዙ ወዳጆቼ ጠላቶቼም ጋር የምነጋገረው ነው። እነሱ ነጻነት ፈልገዋል። ኦሮሞ ነጻነት አልፈለገም፣ ከአገር ለመገንጠልም አልፈለገም፣ ኦነግ ተቸገረ፣ መገንጠል አንዳንድ ጥቅም አንዳለው አየ፣ ግን ኦሮሞን ማስረዳት አቃተው፣ ተገንጥሎ ሌላ አገር መሆን ወይም መሄድን አብዛኛው ኦሮሞ ተቃወመው እና እኔ ያነተ ነኝ ብሎ ማነቃነቅ አቃተው፣ አሮሞ ልገንጠል ብሎ አልተነሳም፣ ኦሮሞ ነው ተጨቆንኩ ያለው አማራ ብሎ አያውቅም። አማራ እንደ ህዝብ ተበደልኩ ብሎ አያውቅም።

ሸገር ታይምስ፡- ቀደም ባሉት ጊዜያት አማራ ተበድሏል ወይስ አልተበደለም?

ሸገር ታይምስ፡- አቶ መለስ አገራቸውን ይወዱ ነበር ወይስ አይወዱም ቢባሉ ምን ይላሉ?

አቶ ቡልቻ፡- በቂ መልስ እኮ ነው አይወድም። አንድ ህጻን ልጅ እኮ እናትና አባቱን ቀስ ቀስ እያለ ሲያውቃቸው ነው የሚወዳቸው። እሱ ኢትዮጵያን ይወዳል ብዬ አላስብም፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ሲዋጋ ነበር፣ የኢትዮጵያ ሰው እሱ ላይ እየተኮሰ እሱ ኢትዮጵያ ላይ እየተኮሰ ነው ያደገው ታዲያ እንዴት ኢትዮጵያን ይወዳል ብዬ ልናገር?

ሸገር ታይምስ፡- ሰሞኑን ዩኒቨርሲቲዎቻችን አከባቢ የሚሰማ ነገር አለ። በተለይ ዘር ተኮር የሆነ ነገር መነሻው ምንድን ነው የምን ችግርስ ነው?

አቶ ቡልቻ፤ ይህ ያለውና የተጀመረው ችግር ስርዓቱን ባለመፈለግ ነው። ዜጎች ስርዓቱን አልፈለጉትም፣ ግን የሚያደርጉት ነገር የላቸውም። ተማሪ መከራከር ይችላል፣ እዚህ አዲስ አበባ ወንበር ላይ ተቀምጦ እነ ገሌን ግደል እነገሌን አትግደል ማለት አይችልም። ስለዚህ አዘንኩ ያለ ሰው ለሃዘኑ መልስ የለውም። ማድረግ ያለበትን ያደርጋል፡፡ ይህንን የሚያፋፍመውና የሚያስፋፋው እገሌ ነው አልልም ግን ያመጣው ግን የህወሃት መንግስት ነው። ይህንን ያመጡት የህወሃት መሪዎች ናቸው። እሳቱን እፍፍ ብለው እንዲነድ ያደረጉት እነሱ ናቸው። ነገር ግን በተደረገው ጥፋት ሁሉ እነሱ ሃላፊ ናቸው ማለት አልችልም። ከተጀመረማ ሁሉም ይጣላል። ግን የጀመሩት እነሱ መሆናቸው ግልጽ ነው።

ሸገር ታይምስ፡- ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚስተዋሉትን ችግሮች ለማስወገድ ምን ቢደረግ ይሻላል?

አቶ ቡልቻ፡- ኢትዮጵያዊነት እኮ አሁን ደብዝዟል፡፡ ከዚህ በፊት የአገሪቷ ሁኔታ ሲለወጥ አቶ ክፍሌ ሃላፊያችን ቢሆንም እኔም ነበርኩበት፡፡ አንዳንዱ ሃሳብ ሳንወድ ሳንቀበለው ነው የመጣው፡፡ ለምሳሌ አሰብን ተመልከት የኦሮሞ ወጣት የኤርትራን ወጣት ጠልቶት አይደለም ሊጠላውም አይችልም፡፡ ግን እነሱ በዙ ስልጣን ፈለጉ፣ መቆየት ፈለጉ በሃይል ከሁሉም በላይ መሆን ፈለጉ ያ ሃሳባቸው አልሳካ አላቸው፡፡ ሲጀመር በዚህ ዓላማ ላይ የተነሳ ሰው ሊሳካለት አይችልም። ሁሉም ተነሳባቸው፣ አልሆነላቸውም ምክንያቱም አላማቸው መጥፎ ስለነበር። ወደ እኛ ስንመጣ አሁን ማድረግ የሚገባን የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የደቡብና የትግራይ ህዝብ መሪዎች ተመራረጠው እንደ ዛሬ 27 ዓመት ቁጭ ብለው መነጋገር እና ሰዎች ተጠርተው እና ተመርጠው እነዚህን ሰዎች በሉ ተቀመጡ ብሎ ምን ይሻላል? ምን ማድረግ አለብን? በማለት ይምከሩ ነው የምለው። ከዚህ ውጭ ምንም አማራጭ የለንም። ይህ ደግሞ በአስቸኳይ ነው መሆን ያለበት፡፡

ሸገር ታይምስ፡- ኢትዮጵያዊነት ደብዝዟል እያሉ ነው ማነው ያደበዘዘው?

አቶ ቡልቻ፡- እኔ እንደሚመስለኝ የዛሬ 26 ዓመት የኢትዮጵያን ጦር አሸንፎ እና ተስፋ አስቆርጦ ስልጣን የያዘውና የኢትዮጵያን ንብረትና ሀብት በጣም የሚበላው ወገን ነው ።

ሸገር ታይምስ፡- በኦሮሚያና በሱማሌ ክልሎች የተፈጠረውን ግጭት ማን ነው የጀመረው ማነውስ ያነሳሳው ይላሉ?

አቶ ቡልቻ፡- እሱ ችግር እኔ እንደሚመስለኝ ኦሮሞን ለማዳከም የሚፈልግ ቡድን ወይም ግለሰብ ይኖራል። ለምንድነው ኦሮሞዎች በቁጥራቸው በዙ፣ ዴሞክራሲ ጋር ስንመጣ እንግዲህ እነሱ አብዛኛውን ሹመት ከላይ ጀምሮ ቀስ በቀስ ወደታች ቢቻል እንደ አሜሪካ ወይንም አንደ እንግሊዝ ማድረግ ነው። በዴሞክራሲ ስንመጣ ኦሮሞዎች ቁጥራቸው በዙ ስለሆነ እና ስለሚጠነክሩ እንምታቸው የሚል ያለ ይመስለኛል።

አቶ ቡልቻ፡- ተበድሏል እሱ የታወቀ ነገር ነው።

ሸገር ታይምስ፡- ኦነግ ግን መገንጠልን ይደግፋል እኮ?

አቶ ቡልቻ፡- ይላል ግን ኦሮሞ እምቢ አለ፡፡ እንዴት አሁን እኛ ከእናት አገራችን፣ ከተወለድንበት፣እትብታችን ከተቀበረበት ቦታ ተገንጥለን ሌላ አገር እንሆናለን? እድል የለንም እንቸገራለን ብለው አልደገፉትም፣ አይሆንምም ብለዋል። እኔም ድሮ እኮ ከኦነግ ጋር ትንሽ ዳር ዳር ብያለሁ።

ሸገር ታይምስ፡- እርስዎ ስለ መገንጠል ያስባሉ እንዴ?

አቶ ቡልቻ በፍፁም አላስብም።

ሸገር ታይምስ፡- ኦሮሞና አማራ አንድ ነን፣ ማንም አይለየንም የሚሉ መድረኮችን ሰሞኑን ሲዘጋጁ አስተውለናል። በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች ደግሞ ሁለቱ ህዝብ እንዳይጠናከርና ወዳጅ እንዳይሆን የማይፈልጉም አሉ ይባላል ። እርስዎ ስለሁለቱ ህዝብ ምን ይላሉ?

አቶ ቡልቻ፡- አጼ ምኒልክና ራስ ጎበና አብረው ነው ያደጉት። አብረው ነበሩ፣ ይነጋገሩ ነበር አሁን እኔና አንተ እንደምንነጋገረው። አጼ ምኒልክ ራስ ጎበናን ማንም የለም ከጎኔ መጥተህ እርዳኝ ባሏቸው ግዜ እኔ ኦሮሞ ነኝ ካንተ ጋር መስራት አልችልም ብለዋል ራስ ጎበና? አላሉም፡፡ ራስ ጎበና ጋር ጉግስ ይጫወቱ ነበር፣ የአጼ ምኒልክን ችግር አዩ፣ ገባቸው። እሽ እከተልሃለሁ አሏቸው። ምን ስራ ትሰጠኛለህ አላሉም፣ እሽ እከተልሃለሁ ነው ያሉት፡፡ እሳቸው እንግዲህ አጼ ምኒልክ ሸዋን ይዘዋል፣ ወለጋ፣ ሃረር ከእርሳቸው ኮማንድ ውጭ ነው።

ኦሮሞ ግን እንደተበታተነ በየአገሩ ቀረ፣ ይህንን ለማሰባሰብ አጼ ምኒልክ ጎበናን መረጡ ።ተስማሙ አብረው መጡ ወደ አዲስ አበባ አሁን ከምንነጋገርበት አንጻር አንደት እንዳልተፈራሩ አልገባኝም። እኔ ኦሮሞ ነኝ እርሱ አማራ ነው ብለው እንደት አልተፈራሩም? ይገለኛል፣ ይጠላኛል ለምን አልተባባሉም። እንደዛሬው ልዩነት አለን ብለው አላሰቡም አንድ አገር ነን ብለው ነው ያሰቡት፣ ልዩ ልዩ አገርም አለን ብለው አላሰቡም። ጎበናም ምንም ሳይጠይቁ ከእርሳቸው ጋር ገቡ አብረው በሉ ጠጡ ተጋቡ፣ ይህንን ነው የማውቀው። ሁለቱም አይፈራሩም አብረው ነው ለዘመናት የኖሩት ተጋብተው ተዋደው።

ሸገር ታይምስ፡- አጼ ምኒልክን ለኦሮሞ የተለየ ጥላቻ አንዳላቸው አድርገው የሚያነሱ ሰዎች አሉ ይህ ነገር እንደት ያዩታል?

አቶ ቡልቻ፡- በፍጹም ጥላቻ የላቸውም። አሮሞ የሚባል ስም አልወድም እገላቸዋለሁ፣ ወላይታን አልወድም እፈጃቸዋለሁ፣ አደሬን አልወድም ብለው አንድን ህዝብ መርጠው ጠላቴ ነው ብለው አያውቁም፣አስበውም አያውቁም። አገር እንዲሰለጥን ነው፣ ህዝብ ሁሉ እንዲሰለጥን ነው የተቻላቸውን ሁሉ ያደረጉት። ለአንድ ህዝብ የተለየ ጥላቻ ኖሯቸው ይህንን ህዝብ እንውጋው ብለው ይነጋገራሉ ብዬ መገመት እንኳን አልችልም፡፡ እሳቸው ለአገራቸው ስልጣኔ ነው የለፉት ማንንም አይጠሉም ነበር ። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ሌሎች ናቸው፡፡

ሸገር ታይምስ፡- ታዲያ ሁለቱ ህዝብ እንዳይግባቡ አደረገ የሚሉት ማንን ማነው?

አቶ ቡልቻ፡- እነሱ ናቸው ቅድም የነገርኩህ፣ አለቃ ለመሆን ሁሉም ሰው እንዲቀበላቸው አማራና ኦሮሞ አብረው በልተው እና ተጋብተው ነው የኖሩት ስለዚህ ይጣላሉ ብዬ አልገምትም። ኦሮሞና አማራ ቢጠላሉ ኖሮ ለምን ይጋቡ ነበር? ለምን አማራ ለኦሮሞ ልጁን ይድራል፣ አማራስ ለምን ለኦሮሞ ልጁን ይድራል?

LEAVE A REPLY