የካንጋሮው ፍርድ ቤት ወንጀለኞች ሲጋለጡ፣ አንደኛው ዳኛ የህወሃት አባል ነበሩ

የካንጋሮው ፍርድ ቤት ወንጀለኞች ሲጋለጡ፣ አንደኛው ዳኛ የህወሃት አባል ነበሩ

/ሳዲቅ አህመድ/

የህዝብን ዉክልና ተቀብለው ህዝብና መንግስትን ለማስታረቅ የጣሩት የሙስሊም የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ለመልካም ተግባራቸው ወሮታ እንዲሆን ህወሃት መራሹ ቡድን አስሮ አሰቃያቸው። የደረሰባቸው አካላዊ ስቃይ ተነግሮ አያልቅም። መንፈሳቸውን ሰብሮ ሽንፈትን ፈልቅቆ ለማዉጣት ህወሃት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

የጨቋኙን፣የአፋኙንና የገዳዩን ህወሃት መራሽ ቡድን ሴራ የተቋቋሙት የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች የህወሃት ደህንነቶች በሚሾፍሩት የካንጋሮ ፍርድ ቤት ላይ በዳኞች፣በዓቃቤ ህጎች፣በሐሰት መስካሪዎች ብዙ ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል።

የሐሰት ፍርድ ተፈርዶባቸዋል።ንጹህነታቸው በታሪክ መዛግብት ላይ ሰፍሮ ሲታወስ የሚኖር መሆኑ ሰቆቃዉን የሚያስረሳ ሐቅ ነው። የካንጋሮው ፖለቲካዊ ፍርድ ቤት ወንጀለኞች እነማን ናቸው? ዛሬ የህወሃትን ፖለቲካዊ ጉዳይ አስፈጻሚ ከሆኑት ዳኛ ሙሉጌታ ኪዳኔ ሚና ምን ነበር? የማጋለጽ ስራችንን ይቀጥላል።

ፍርድ ቤቱን የሚሾፍሩት ወንጀለኛው ዳኛ አቶ ሙሉጌታ ኪዳኔ ይባላሉ።በብቃት ሳይሆን ለህወሃት ባላቸው ፖለቲካዊ ጠቀሜታ በተከበረው የዳኝነት ወንበር ላይ የተሰየሙ ናቸው። ህወሃትና የሚቆጣጠረው የደህንነት መስሪያ ቤት በተለያዩ ክልሎች እያዟዟረ ፖለቲካዊ ብያኔን እንዲያሳልፉ የሚጠቀምባቸው ናቸው። ጠበቆችን «የኔን ችሎት ካልፈለጋቹ ተዉት» በማለት እስረኞች እስር ቤት ዉስጥ ተወርዉረው እንዲቀሩ የሚያደርጉ ሰብዓዊነት የጎደላቸው ናቸው። በዘራቸው ከህወሃት ጋር የቆራኙ በመሆናቸውና የህወሃት ታማኝ ፖለቲካዊ አገልጋይነታቸው በግልጽ በችሎት ላይ የሚንጸባረቅ በመሆኑ «ህግ» ለሚለው ለተከበረው ቃል ደንታ የላቸውም።ዳኛ ሙሉጌታ ኪዳኔ ሰብዓዊነትን የሚጠየፉ በመሆናቸው በብዙ ንጹሗን ዜጎች ላይ ጭካኔ የተሞላበትን ፍርድ ፈርደዋል፣ብዙ ቤተሰብን አለያይተዋል፣ እስረኞች በእስርቤት ዉስጥ እንዲሞቱ መንስኤ ሆነዋል። ዳኛ ሙሉጌታ ኪዳኔ ወንጀለኛ መሆናቸውን ይፋ ማድረጉ ተገቢ ነው።

በካንጋሮው ፍርድ ቤት የወንጀል ተግባር ላይ የተሰማሩ የዓቃቤ ህጎች፣ ወንጀል መርማሪዎች፣ የሐሰት መስካሪዎች፣ ስልጠና የሚሰጡ የደህንነት አባልት፣ ድራማዉን ከበስተጀርባ ሆኖ በማቀነባበር ለህወሃት ሎሌ ሆነው ያገለግሉ የነበሩት የፍትሕ ሚኒስቴር ድኤታው ዶ/ር ሃሺም በደም ያደፈ እጅና መርዛማ ተግባር የሙስሊም የመፍትሔ አፈላላጊ ብቻ ሳይሆን መላዉ የፍትህ ስርዓትና የኢትዮጵያ ህዝብ የተጎዳበት በመሆኑ ወንጀለኞች እርቃን የማስቀረቱ ተግባር የዜጎች ሁሉ ሐላፊነት ነው።

የሙስሊም የመፍትሔ እፈላላጊ ኮሚቴዎችና አብረዋቸው የታሰሩት ሌሎች ባልደረቦቻቸው በማእከላዊ ዉስጥ አያሌ ስቃይና መከራን አሳልፈው በጥቅምት 19 ቀን 2005 በልደታ ከፍተኛ ፍ/ቤት ቀረቡ፡፡ በዕለቱም ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል የመናድ ሙከራ እና የሽብርተኝነት ወንጀል መፈጸም የሚል ሁለት ክሶች ተመሰረቱባቸው።

በሁለቱም ክሶች ላይ ተከሳሾች «ኢስላማዊ መንግሥትን ለመመሥረት እና ሕገ–መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ በማሰብ ከ2001 ጀምሮ ሲዘጋጁ ቆይተው በ2004 ግምቱ 160 ሺህ ብር ገደማ የሆነ ንብረት እንዲወድምና ኮማንደር ግርማይ ወ/ሚካኤል የተባሉ ፖሊስ ላይ መጠነኛ ጉዳት እንዲደርስ አነሳሱ» የሚል የሐስት ዉንጀላ ታክሎበት ነበር፡፡

የሐስት ክሱን ተዓማኒነት ለማጉላት በህወሃት የሚመራው ቡድን በሚቆጣጠራቸው የመገናኛ ብዙሗን ብዙ የፕሮፓጋንዳ ስራ ሰርቷል።ይህንኑ ፕሮፓጋንዳ ለማመን የበቁ ሰዎች ቢኖሩም የኮሚቴዎቹ ንጹህነት ከሐስት ዉንጀላዉ የላቀና የገዘፈ ሆኖ በታሪክ ድርሳናት ላይ ሰፍሯል።ሌላው ቀርቶ ‹‹የአካል ጉዳት ደረሰባቸው›› የተባሉት ኮማንደር ግርማይ በፍ/ቤቱ ለምስክርነት ቀርበው ተከሳሾቹን እንደማያውቁ ጠቅሰዋል።

በዓይናቸውም ላይ መጠነኛ ጉዳት ያደረሱባቸው ሰዎች ታስረው፣ በጳውሎስ ፍ/ቤት መስክረውባቸው በቀላል እሥራት መቀጣታቸው ይታወቃል። በፈጠራ ግጭቱን ‹‹አነሳሳችሁ›› የተባሉት የኮሚቴ አባላት ክስ ግን «ሕገ–መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማፍረስ እና ሽብርተኝነት» የዘለገ መሆኑ የማይታበልና ህወሃት የፈጸመው ፖለቲካዊ ወንጀል ነው፡፡

LEAVE A REPLY