/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፦ የሰላሳዎቹ አጋማሽ የሆነው ወጣት ገብረመስቀል ጌታቸው በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ታላቅ ቦታ የሚሰጠውን የጥምቅት በአል ለማክበርና ታቦተ ህጉ ወደ ማረፊያው ለማንገስ ተሰናድቶ ነበር ከቤቱ የወጣው፡፡ የቢቢ ሲ ዘገባ እንዲህ አሰናድቶታል…
መንግሥት የሟቾች ቁጥር ሰባት ነው ቢልም ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ግን የሟቾችን እና የቁስለኞችን ቁጥር ከፍ ያደርጉታል።
ከከተማዋ ነዋሪዎች እንደሰማነው ከሟቾቹ መካከል አዛውንቶች እና እድሚያቸው በአስራዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኙ ሁለት ታዳጊዎች ይገኙበታል።
ከዚህ በተጨማሪ በጥምቀት በዓል ማግስት ከተገደሉት መካከል በወልዲያ ከተማ በብረታ ብረት ሥራው የሚታወቀው ገብረመስቀል ጌታቸው ይገኝበታል።
ገብረመስቀል እድሜው ወደ 35 የሚጠጋ ሲሆን ባለትዳር እና የ5 ዓመት ሴት ልጅ አባት ነበር። ገብረመስቀልን በቅርብ የሚያውቁት ጠንካራ ሰራተኛ ስለመሆኑ ይመስክሩለታል። ብረመስቀል የብረታ ብረት ድርጅት የነበረው ሲሆን በወልዲያ ከተማም የንግድ ህንጻ እየገነባ ነበር።
ገብረመስቀል በተገደለበት ቀን እና አሁን ቤተሰቡ ስለሚገኘበት ሁኔታ ወንድሙን ኪዳኔ ጌታቸውን አነጋግረነው ነበር። ገብረመስቀል ጥር 12 የሚካኤል ታቦትን ሽኘቶ ሲመለስ መብራት ኃይል የሚባል ቦታ ላይ በጸጥታ ኃይሎች በተተኮሱ ጥይቶች እንደተገደለ ከቤተሰቡ ሰምተናል። ወንድሙ ኪዳኔ ”ወንድሜን አምስት ቦታ ነው በሳስተው የገደሉት። እንዳይተርፍ ነው 5 ጊዜ በጥይት የመቱት” ሲል በምሬት ይናገራል።
ኪዳኔ ዕለቱን ሲያስታውስ ”ግርግር እንደተነሳ ደጋግሜ ስልክ ደወልኩለት፤ አያነሳም። ብጠብቀውም መልሶ አይደውልም። በጣም ስለተጨነኩኝ ወደ ሆስፒታል ልፈልገው ሄድኩኝ።
”አንገቱ ላይ፣ ደረቱ ላይ፣ ሆዱ ላይ እና ብልቱ ላይ አምስት ጊዜ በጥይት የተመታ እና በደም የተሸፈነውን የወንድሜን አስከሬን ሆስፒታል ውስጥ አገኘሁ” ይላል ሁኔታውን ሲያስታውስ።
”ማመን ነው ያቀተኝ። ወንድሜ ላይ ግፍ ነው የተፈጸመው። ገብረመስቀል አንድ ጥይት የሚበቃው ልጅ ነበር። የቤተሰቡን አንጀት ነው የቆረጡት። እናቱን ወዳጅ፤ አባቱን አክባሪ ነበር። እሱን ብቻ ሳይሆን ቤተሰቡን ነው የገደሉት። የአምስት ዓመት ሴት ልጅ አለችው አሁን የተፈጠረውን ነገር መቀበል አልቻለችም” ሲል ኪዳኔ በቁጭት ይናገራል።
ኪዳኔ እንደሚለው ገብረመስቀል ታቦት ሸኝቶ ሲመለስ መብራት ኃይል አካባቢ በነበረበት ወቅት ምንም አይነተ ረብሻ አልነበረም። ”ለምን መግደል እንዳስፈለጋቸው አላውቅም። ይህን ስላደረገ ነው የተገደለው የሚለን እንኳ አላገኘንም” ይላል።
ከአንድ ወር በፊት ሌላ ታናሽ ወንድማቸውን በህመም እንዳጡ የሚናገረው ኪዳኔ ”በሃዘን ላይ መሪር ሃዘን ነው የጨመሩብን” ሲል ይናገራል። ”የታናሽ ወንድማችንን 40 ቀን እንኳን ሳናወጣ ነው ሃዘን ላይ እያለን ሃዘን የተጨመረብን” ብሏል።
እሁድ ዕለትም ጸጥታ አስከባሪዎች የቀብር በሥርዓቱ እንዳንፈጽም እክል ሲፈጥሩብን ነበር የሚለው ኪዳኔ ”አስክሬኑ ቅዳሜ ምሽት ወልዲያ ኪዳነምህረት ቤተ-ክርስቲያን ፍትሃት ሲደረግበት አደረ፤ ከዚያም ከኪዳነምህረት አውጥተን ለቀብር ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን ስናመራ፤ መከላከያዎች እና አድማ በታኞች ጥይት እና አስለቃሽ ጪስ በመተኮስ ለቀብር የመጣን ህዝብ ሲበትኑ ነበር” በማለት ኪዳኔ ያስረዳል።
የክልሉን ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ባለስልጣናት መኖሪያ ቤታቸው በመምጣት እንዳነጋገሯቸው የሚናገረው ኪዳኔ ”እኛም የወንድማችን ገዳይ ተለይቶ ለፍርድ ይቅረብልን። የወንድማችን ደም ፈሶ መቅረት የለበትም ስንል ነግረናቸዋል” ይላል።
የክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር ወልዲያ ላይ ከተፈጸመው ግድያ በኋላ በሰጡት መግለጫ ጉዳዩ በጥንቃቄ ተጣርቶ ውጤቱ ለህዝብ ይፍ ይሆናል ማለታቸው ይታወሳል።
ትናንት አመሻሽ ላይ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ራቪና ሻምዳሳኒ በጄኔቫ ላይ ባወጡት መግለጫ ”በኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች የሚወስዱት የኃይል እርምጃዎች እጅጉን አሳስቦናል” ብለዋል።
ኮሚሽኑ ገለልተኛ እና አድልዎ በሌለው አካል አስቸኳይ ምርመራ ተካሂዶ ጥፋተኞች ከህግ ፊት እንዲቀርቡ በማለት ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።