አነጋጋሪው የኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ጉዳይ /በጌታቸው ሺፈራው/

አነጋጋሪው የኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ጉዳይ /በጌታቸው ሺፈራው/

~ የኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ጠበቆች የቀረበው ሰነድ ሀሰተኛ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል

~ የልደታ ፍርድ ቤትና የደህንነት መስርያ ቤቱ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አላከበሩም

~በእነ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ስም ተከፍቷል የተባለው መዝገብ ሌላ ሰው የተከሰሰበት እና በ2004 ዓም ውሳኔ ያገኘ ነው ሲሉ ጠበቆች ገልፀዋል

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የኮሎኔል ደመቀ ክስ ላይ ኮሎኔሉ ከሌሎች ግለሰቦች ጋር በስልክ ተለዋውጠዋል ያለውን ሪፖርት አቅርቧል። የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ኮሎኔሉ ከሌሎች ግለሰቦች ጋር ተገናግረዋል በሚል በፅሑፍ ያቀረበው ሪፖርት የድምፅ ቅጅ እንዲያመጣ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

በሌላ በኩል የኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጠበቆች የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በኮሎኔሉ ላይ ስልክ ጠልፌ አቀረብኩት ያለውን ማስረጃ ተቃውመው ነበር። የመቃወሚያው መነሻም የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ስልክ ለመጥለፍ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አልነበረውም የሚል ነው። ሆኖም ለዚህ መቃወሚያ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት የኮሎኔሉን ስልክ እንደጠለፈ ገልፆ ነበር። ስልክ ንግግሩን የጠለፈውም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ በወጣ መዝገብ ቁጥር 104025 መሰረት እንደሆነ መልስ ሰጥቷል። ትዕዛዙ የተሰጠውም በወቅቱ የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ዳኛ በነበሩት አቶ ሀብቴ ፍቻለ ነው ተብሏል።

አቶ ሀብቴ ፍቻለ ትዕዛዝ መስጠት ይችላሉን?

……………………………………

በወቅቱ ትዕዛዝ ሰጥተዋል የተባሉት ዳኛ ከሕግ አንፃር ትዕዛዝ መስጠት ይችላሉ አይችሉም የሚለውን እንዲያብራሩልኝ የኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጠበቃ የሆኑትን አቶ አለልኝ ምህረቱን ጠይቄያቸው ነበር። አቶ አለልኝ ምህረቱም ዳኛው በወቅቱ በስራ ላይ ነበሩ ወይ የሚለው በራሱ የሚጣራ ሆኖ አንድ ዳኛ ብቻውን በመሰል ጉዳይ ላይ ትዕዛዝ እንደማይሰጥ ገልፀውልኛል። በጉዳዩ ለአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረቡትን መቃወሚያ መልስም አግኝቼ አይቸዋለሁ። በመቃወሚያቸውም “የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ 23 አዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀፅ 23(3) (ሀ) መሰረት ……ከ15 አመት በላይ የሚያስቀጡ ወንጀሎች በ3 ዳኞች እንደሚታይ ተደንግጓል። በተጨማሪም የፌደራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዝደንቶች እና ምክትል ፕሬዝደንቶች በ3 ዳኞች በሚታዩ ጉዳዮች በሰብሳቢነት ከሚሰሩ ውጭ በመደበኛ ዳኝነት እንዲሰሩ አልተፈቀደላቸውም።” ሲሉ ትዕዛዝ ሰጡ የተባሉት ዳኛ በወቅቱ ትዕዛዝ ሰጥተዋል ቢባሉ እንኳ ሕጋዊነት እንደሌለው ይገልፃሉ።

መዝገብ ቁጥር 104025 የማን መዝገብ ነው?

……………………………………

የኮሎኔል ደመቀ ጠበቆች ከፍርድ ቤቶች አረጋግጠው እንደገለፁልኝ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶችም ሆነ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች በወንጀል ሆነ በፍትሕብሔር መዝገብ ቁጥሮች ተከታታይ ናቸው። የፍትሕብሔርና የወንጀል ቁጥሮች ከተራ ቁጥር 1 ጀምሮ የወንጀል ከፍትሕብሔር ጋር ሳይደባለቅ፣ ወይንም ሳይደረብ የሚሰጣቸው ስለሆኑ መዝገቦች ተመሳሳይ ቁጥር የላቸውም። ይህን በመቃወሚያቸውም ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል።

ሆኖም ግን እነ ኮሎኔል ደመቀ ላይ ተከፈተ የተባለው 104025 መዝገብ ቁጥር ሲፈለግ በከሳሽ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 07/17 እና በእነ አስረስ ተካልኝ መካከል የነበረ የፍትሕብሔር ክርክር ሆኖ መገኘቱን ጠበቆቹ ገልፀዋል። ይህ መዝገብ በልደታ ምድብ 10ኛ ፍትሕብሔር ችሎት ለረዥም ጊዜ ሲታይ ቆይቶ ሚያዚያ 25/2007 ዓም ውሳኔ አግኝቶ የተዘጋ መዝገብ ነው ብለዋል ጠበቆቹ። እነ ኮሎኔል ደመቀ ላይ መዝገቡ ተከፈተ የተባለው ይህ መዝገብ ከተዘጋ ከ3 አመት በኋላ ነሃሴ 25/2007 ዓም ነው። እነ ኮሎኔል ደመቀ ላይ መዝገብ ተከፈተ ከተባለበት 8 ወር በፊት እንኳ የልደታ ፍርድ ቤት የመዝገብ ቁጥር 161802 ደርሶ እንደነበር ጠበቆቹ በወቅቱ ይዘውት ከነበር መዝገብ ማረጋገጥ ተችሏል። እነ ኮሎኔል ላይ ተከፈተ የተባለው መዝገብ ከዚህ ጋር ሲነፃፃር በ57,777 መዝገብ ቀድሞ ይገኛል።

ይህ በእነ ኮሎኔል ደመቀ ላይ ተከፈተ የተባለው መዝገብ በ2003 ዓም የተከፈተ የፍትሕብሔር መዝገብ እንደሆነም ጠበቆቹ ማረጋገጣቸውን ገልፀዋል። በዚህም መሰረት የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የእነ ኮሎኔል ደመቀን የስልክ ንግግር በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደጠለፈ የገለፀው ከእውነት የራቀ እንደሆነና፣ እውነት ለማስመሰልም በእነ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ላይ በልደታ ፍርድ ቤት ስም ሀሰተኛ ሰነድ እንደተዘጋጀባቸው፣ በዚህ ሰነድ ላይም ምክትል ፕሬዝደንት የነበሩት ዳኛ ትዕዛዝ ሰጡበት የተባለው እውነት እንዳልሆነ ጠበቆቹ ተከራክረዋል።

የልደታ ፍርድ ቤት አጣብቂኝ

………………………………………

በእነ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ላይ የተከፈተ መዝገብ የልደታ ፍርድ ቤት መዝገብ መሆኑን፣ በዚህ መዝገብ ላይም ትዕዛዝ የሰጡት በወቅቱ የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዝደንት የነበሩት አቶ ሀብቴ ፍቻለ እንደሆኑ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሰነድ ላይ ተጠቅሷል። የኮሎኔል ደመቀ ጠበቆች ባቀረቡት መቃወሚያ መሰረትም የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የስልክ ልውውጥ ነው የተባለው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ስለመፈፀሙ ለማረጋገጥ ተከፍቷል የተባለው መዝገብ እንዲመጣለት ትዕዛዝ ልኳ ነበር።

ጥር 14/2010 ዓም በዋለው ችሎት ግን የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መዝገቡን አልክም የሚል መልስ ሰጥቷል። በምክንያትነት ያስቀመጠውም መዝገቡ ውስጥ የሌሎች 45 ሰዎች ስም ስለሰፈረ የሚል ነው። የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣን ያለው ፍርድ ቤት ነው። መዝገብ እንዲልክ የተጠየቀው ደግሞ ከአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር ተመሳሳይ ስልጣን ያለው ተቋም ነው። መዝገቡም የሚላከው ለፍርድ ቤት እንጅ ለሌላ አካል አይደለም። መዝገቡ ትክክለኛ መዝገብ ቢሆን በሕጉ መሰረት እንደ አንድ ተቋም ለሚታይ አካል (ሁለቱም የከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣን ነው ያላቸው) መዝገብ አልክም ብሎ መልስ መስጠቱ አነጋጋሪ ሆኗል።

የደህንነት ተቋሙ አጣብቂኝ

……………………………………

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሚታዩ ጉዳዮች ላይ ፍርድ ቤቶች ተከሳሾች በጠየቁት መሰረት ገፍተው የስልክ ልውውጥ ተደርጓል ስለመባሉ የሚያሳየውን የድምፅ ቅጅ ከደህንነት መስርያ ቤቱ አይጠይቁም። የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግን የደህንነት መስርያ ቤቱ እውነትም በኮሎኔሉ ላይ ያቀረበውን የፅሑፍ ማስረጃ ከስልክ ልውውጥ ነው ያገኘሁት ካለ የድምፅ ቅጅውን እንዲያቀርብ ብይን ሰጥቷል። የኮሎኔል ደመቀ ቤተሰቦችም የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ የፕሬዝደንቱ ቤተ መንግስት ፊት ለፊት ለሚገኘው ዋናው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መስርያ ቤት በአካል አድርሰዋል።

ሆኖም የደሕንነት መስርያ ቤት ጥር 14/2010 ዓም በዋለው ችሎት የድምፅ ቅጅውን እንደማይልክ ለፍርድ ቤቱ ገልፆአል። ምክንያት ብሎ ያቀረበውም ከኮሎኔል ደመቀ ጋር የስልክ ልውውጥ ያደረጉና ያልተያዙ ግለሰቦች ስላሉና የድምፅ ቅጅውን ቢልክ ሊይዛቸው የሚፈልጋቸውን ግለሰቦች ለመያዝ እንደሚያዳግተው የሚገልፅ ነው። ይሁንና ከስልክ ንግግር የተገኘ ነው በተባለውና በፅሑፍ የኮሎኔል ደመቀ ክስ ላይ ማስረጃ ተብሎ የቀረበው ላይ ያልተያዙ ግለሰቦች ከኮሎኔሉ ጋር አድርገውታል የተባለው የስልክ ምልልስ ሰፍሮ ይገኛል። የእነዚህ ግለሰቦች የስልክ ልውውጥ ነው የተባለው ክስ ላይ ሰፍሮ በሚገኝበት ሁኔታ ድምፃቸው ያውም ይህን የስልክ ጠለፋ አዝዞ አስጠልፏል ለሚባል ፍርድ ቤት አልክም ማለት የደሕንነት መስርያ ቤቱም አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን የሚያመለክት ነው።

“የሀሰት ማስረጃ ነው!”

……………………………

የኮሌኔል ደመቀ ዘውዱ ጠበቆች ሕዳር 25/2010 ዓም ለአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት “የማስረጃ ሀሠተኝነት እንዲረጋገጥልን” የሚል ርዕስ ሰጥተው ባቀረቡት አቤቱታ “የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሕዳር 15/2007 ዓም ከተፃፈ ማመልከቻ ጋር በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 104025 ነሃሴ 25 ቀን 2007 ዓም ተሰጠ የተባለ የምርመራ ፈቃድ ትዕዛዝ ግልባጭ አቅርቧል። ሆኖም ይህ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነው የተባለው ሕጉን ያልተከተለ ከመሆኑም በተጨማሪ ሀሰተኛ ሰረድ መሆኑን አረጋግጠናል” ብለዋል።

ጠበቆቹ አክለውም በክርክር ሂደት ከሚመጡት አዲስ ጭብጦች የሚፈለጉ ማስረጃዎች ካልሆነ በስተቀር ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ማናቸውም የወንጀል ማስረጃዎች በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነስርዓት ቁጥር 98 መሰረት አስቀድመው መያዝ እንደነበረባቸው አስገንዝበዋል። ማስረጃው ያልተያዘው አስቀድሞ ስላልነበረ ነው ሲሉ በመቃወሚያቸው ላይ ተከራክረዋል። “የተከሳሽ ስልክ እንዲጠለፍ ትዕዛዝ ተሰጠ የተባለበት መዝገብ በ2004 ዓም ውሳኔ ያገኘ የፍትሕብሔር መዝገብ ስለሆነ ይህ ማስረጃ ሀሰተኛ መሆኑ ደግሞ ሌሎች ማስረጃዎችም ተመሳሳይ እንደሆኑ ሙሉ ግምት ሊያስወስድ የሚችል በመሆኑ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ሬጅስትራል ፅ/ቤት የተጠቀሰው መዝገብ ቁጥር በማን ስም እንደሆነ እንዲረጋገጥልን……” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት፣ ፍርድ ቤቱ ለልደታ የላከው ትዕዛዝ ተፈፃሚ ሳይሆን ቀርቷል።

ጠበቆቹ ሀሰተኛ ያሉት መዝገብም ሆነ የደህንነት መስርያ ቤቱ ማስረጃዎች የሀሰት ናቸው ብለው ላቀረቡት አቤቱታ፣ የአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የልደታ ፍርድ ቤት መዝገቡን፣ ደህንነት መስርያ ቤቱም ድምፁን እንዲልኩ የሰጠው ትዕዛዝ ተግባራዊ አልሆነም። የአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም መዝገቡ የሀሰት መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም እውን የደህንነት መስርያ ቤት ማስረጃውን ከስልክ ጠልፎ ስለማምጣቱ ከድምፅ ቅጅው ከማረጋገጥ የሰጠው ትዕዛዝ ተግባራዊ ባልሆነበት የካቲት 9/2010 በኮሎኔሉ ክስ ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ይዟል።

LEAVE A REPLY