የተባበሩት መንግስታት በወልድያ ወጣቶች ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ እጅግ እንዳሳዘነው አስታወቀ

የተባበሩት መንግስታት በወልድያ ወጣቶች ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ እጅግ እንዳሳዘነው አስታወቀ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፦ በወልዲያ የጥምቀትን በዓል ሲያከብሩ በነበሩ ንጹሃን ሰዎች ላይ የጸጥታ ሀይሎች የፈጸሙት የጅምላ ጭፍጨፋ በእጅጉ እንደሚያወግዘው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።በወልዲያ ከተማ ለንጹሃን ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውም በጥምቀት በዓል ላይ ህዝቡ “መንግስትን” የሚቃወሙ መዝሙሮች ሲዘመሩ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ለማስቆም መሞከራቸው ለግጭቱ መነሳት ምክንያት መሆኑን የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ገልጿል።የጸጥታ ሀይሎች አሰቃቂውን ግድያ ከፈጸሙ በሗላም የከተማው ህዝብ መንገዶችን በመዝጋትና በርካታ ንብረቶችን በማቃጠል ተቃውሞውን እንደገለጸ መግለጫው ጨምሮ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ገዥው ቡድን ኢህአዴግ ስህተቱን በማረም “ለመለወጥ” ቃል ከገባ ከሁለት ሳምንታት በሗላ ይህ ክስተት መፈጠሩ ከመቸውም ጊዜ በላይ የሚፀፅት መሆኑን ገልጿል።የሰብአዊ መበት ኮሚሽኑ የመንግስት ታጣቂዎች ስራቸውን በሚሰሩበት ጊዜ ከሀይል ርምጃ እንዲቆጠቡና ሙያዊ ስልጠና እንዲሰጣቸው ጠይቋል።የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሞቱና የተጎዱ ሰዎች እንዳሉ ማረጋገጣቸውንና ምርመራም እንደሚደረግ ቢገልጹም ግን በገለልተኛ አካል ጉዳዩ ሊጣራ ይገባል ብሏል።ንጹሃንን የገደሉ ታጣቂዎችም ተገቢው ማጣራት ተደርጎ ለፍርድ እንዲቀርቡም ኮሚሽኑ ጠይቋል።

ማክሰኞ እለት በወልዲያ ቃና ዘገሊላ በሚያከብሩ ሰላማዊ ወጣቶች ላይ በህወሓት ወታደሮች በተከፈተ ተኩስ ከ20 ሰዎች በላይ በግፍ እንደተገደሉ የተለያዩ መረጃዎች ቢጠቁሙም እስካሁን በሚዲያ እየተገለጸ ያሉው ግን የሰባት ሰዎች ብቻ ነው።

LEAVE A REPLY