የሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ በወልዲያ ከተማ በጥምቀት እና በቃና ዘገሊላ በዓል አከባበር ወቅት የተቀሰቀሰው ግጭትና የተፈጸመው ግድያ በጸጥታ ኃይሉ ስሕተት የደረሰ ነው ማለታቸውን ሐራ ተዋሕዶ ድረ-ገጽ ዘገበ
*****
የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ: በወልድያ የበዓለ ጥምቀት ግጭትና ግድያ የጸጥታ ኃይሉን ወቀሱ፤ “የእነርሱ መዘዝ ነው፤ ወጣቱ አበላሸ የምንለው ነገር የለም፤”
• “መከላከያዎቹ እንዳይመጡ ቀድመን አሳስበናል፤ከዞኑም ጋር ተናበን እየሠራን ነበር፤”
• “በሰላም ሊጠናቀቅ ባለበት ሰዓት መጥተው ግጥም አሉ፤ ይኸው ወጣቱን አሳበዱት፤”
• “ወጣቱን ሌላ የፖሊቲካ አካል ቀሰቀሰው አሉ፤ ወታደሮቹን ማን ነው የቀሰቀሳቸው?”
• “የበቀል ነው የሚመስለው፤እንደው ከራሳቸው መካከልም የሚያጠፋ ያለ ይመስለኛል፤”
• “ታቦቱን ያከበሩት ካህናት፣በጎናቸው ባሉት ካህናት ተገድፈው ነው እንጅ ወድቀዋል፤”
• “ተዉ ብሎ ይህን ማስተካከል እና መሥመር ማስያዝ ያለበት መንፈሳዊ አባት ነው፤”
• “ቤተ ክርስቲያኗን ወጣቱ ሰምቶልናል፤ታቦቱ ከገባ በኋላ ሁሉም እንሙት እያለ ነበረ፤”
†††
• “ተረጋግቶ እያለ ድኻ የሚረዳ ልጅ ገድለው ዳግም በእነርሱ ስሕተት ግጭቱ ቀጠለ፤”
• “ሕንፃ እግዚአብሔር እያፈረሳችሁ ፎቅ ትጠብቃላችሁ፤”ብሎ ሕዝቡ በጣም ተቆጨ፤
• “ስንቱስ ንብረት ወደመ? የእነርሱ መዘዝ ነው፤ ወጣቱ አበላሸ የምንለው ነገር የለም፤”
• “መከላከያ ይውጣ፤ ወጣቱ ከከተማው ፖሊስ ጋር ይጠብቀዋል፤” በሚል ተስማማን፤
• ርእሰ መስተዳድሩም፣ “ሠራዊቱን አስወጣለሁ፤ አጣሪ እልካለሁ፤ አጥፊው ለሕግ ይቀርባል፤ ይፋም አደርጋለሁ፤” ብለዋል፤ ልቅሶ ቤትም ገብተው አብረው እያለቀሱ አጽናንተዋል፤
• “ከሁለት ዙር ውይይት በኋላ፣ ወጣቱን በየአቅጣጫው የሚመሩ ካህናት መድበን ወደየቤቱ እንዲገባ አድርገናል፤ በሰላም እየዘመረም ወደየቤቱ ተመልሷል፤”
• “እኛም በየሐዘን ቤቱ እየዞርን ስናጽናና ውለናል፤ ርእሰ መስተዳድሩ ከተመለሱ በኋላ ከላኳቸው ልኡካን ጋራ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተካትተን እየመከርን ነው፤”
†††
በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ፣ በጥምቀት እና በቃና ዘገሊላ በዓል አከባበር ወቅት የተቀሰቀሰው ግጭትና የተፈጸመው ግድያ፣ በጸጥታ ኃይሉ ስሕተት የደረሰ ነው፤ ያሉት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ረዳት፣ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፣ ለጠፋው የዜጎች ሕይወት እና ለወደመው ንብረት ወቀሱት፡፡
የቃና ዘገሊላ በዓል እንደ በዓለ ጥምቀት ኹሉ በሥርዐቱ እየተከበረ በሰላም ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ሰዓት የመጣው የጸጥታ ኃይል “ያልተጠራ” እንደነበር የጠቀሱት ብፁዕነታቸው፣ ከመጣ ችግር እንደሚፈጠር ስለታመነ እንዳይመጣ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ቀድመው አሳስበው እንደነበር አውስተዋል፡፡
ለበዓሉ አከባበር፣ ሀገረ ስብከቱ ከዞኑ ሓላፊዎች ጋራ እየተናበበ በመሥራቱ የተጠየቀ ተጨማሪ ኃይል እንዳልነበርና “እነርሱ አይምጡ፤ እኛው በእኛው ፕሮግራማችንን እንመራለን፤” በማለት ቀድሞ እንዳሳወቀ ብፁዕነታቸው ጠቁመዋል፡፡ ይኹንና በመምጣታቸው ወጣቱ ለተቃውሞ እንደተነሣሣ ተናግረዋል፤ “ወጣቱን አሳበዱት፤ የተሳደበም ይመስለኛል፤ ድንጋይም ሳይወረውር አይቀርም፤ በጥይት ለቀሙት፤” በማለት የርምጃውን ኢፍትሐዊነት አስረድተዋል፡፡ በማግሥቱም ቀጥሎ የነበረው ግጭትና የንብረት ውድመት መንሥኤ የጸጥታ ኃይሉ እንደኾነ የተናገሩት ብፁዕነታቸው፣ “የእነርሱ መዘዝ ነው፤ እኛ ወጣቱ አበላሸ የምንለው ምንም ነገር የለም፤” ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል፡፡
በሞትና መቁሰል ስለደረሰው ጉዳትም፣ “ብዙ ሰው ነው የተጎዳብን፤ ያላወቅነውም ይኖራል፤” ብለዋል ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፡፡ ግጭቱ በተከሠተበት ወቅት ከመርሳ ከተማ ወደ ወልዲያ ተመልሰው በዚያው አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ለማስተማር በዝግጅት ላይ እንደነበሩ ገልጸው፣ የጸጥታ ኃይሎቹ ለብተና በተጠቀሙበት አስለቃሽ ጢስ ታቦቱን ያከበሩት ካህናት፣ “በጎናቸው ባሉ ካህናት ተገድፈው ነው እንጅ ወድቀዋል፤” ብለዋል ጥልቅ ቅሬታ በሚደመጥበት አነጋገር፡፡
የጸጥታ ኃይሉን ለምን ማሠማራት እንዳስፈለገ እንደማያውቁ ብፁዕነታቸው ጠቅሰው፣ ኾነ ተብሎ የታቀደ እንደሚመስላቸው ሳይገልጹ አላለፉም – “ለምን እንደመጡ አናውቅም፤ ኾን ብለው ለመምታት ይመስላል፤ ከራሳቸው መካከልም የሚያጠፋ ያለ ይመስለኛል፤” ብለዋል፡፡ አያይዘውም፣ “ወጣቱን ሌላ የፖሊቲካ አካል ቀሰቀሰው ይባል፤ እነርሱን ወታደሮቹን ማን ነው የቀሰቀሳቸው? ሰላም እንዳይኾን!” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ከክልሉ ርእሰ መስተዳድር ጋራ በኹለት ዙሮች በተካሔደው ውይይት፣ ወጣቱ በአጠፌታ ተሠማርቶበት ከነበረው የንብረት ማቃጠልና ማውደም አረጋግተው ወደ አዳራሽ እንዲገባ በማድረግ ከሌሎች የሃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ጋራ የተሳካ ሥራ እንደሠሩ ብፁዕነታቸው ይገልጻሉ፡፡ ቀደም ሲል ከእግር ኳስ ጨዋታ ጋራ ተያይዞ ተከሥቶ በነበረው የከተማዋ ግጭት በተለይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የማረጋጋት አባታዊ ሚና እንደነበራቸው በማውሳት፣ “ቤተ ክርስቲያኗን ወጣቱ ሰምቶልናል፤” ሲሉ አመስግነዋል፡፡
ባለፈው ሰኞ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር በተገኙበት በተደረገው ውይይት፣ የመንግሥት ጥፋት በግልጽና በዝርዝር መቅረቡን፤ ለከተማው ሰላምና ጸጥታ በሚረዱ አጠቃላይ መፍትሔዎች ላይም ስምምነት እንደተደረሰ አስታውቀዋል፡፡ ሠራዊቱን ከከተማው እንደሚያስወጡ ርእሰ መስተዳድሩ የገለጹ ሲኾን፣ ለሰላሙና ጸጥታው ወጣቱ ከፖሊስ ተባብሮ እንደሚሠራም አረጋግጧል፡፡ ርእሰ መስተዳድሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ “ስለተፈጸመው ነገር የሚያጣራ አካል እልካለሁ፤ አጥፊው ለሕግ ይቀርባል፤ ለእናንተም ይፋ አደርጋለሁ፤” ማለታቸው ታውቋል፡፡
ከውይይቱ በኋላ አቶ ገዱ፣ ሐዘንተኞችን በየቤታቸው ተገኝተው በማጽናናታቸው ያመሰገኑት ብፁዕነታቸው፣ በቤተ ክርስቲያንም በኩል ካህናትን መድቦ ወጣቱ በሰላም ወደየቤቱ እንዲገባ ከማድረግ ባሻገር፣ እስከ ትላንት ድረስ ሐዘንተኞችን ሲያጽናኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ በአኹኑ ወቅትም በክልሉ መንግሥት ተሠይሞ ከተላከው ልኡካን ቡድን ጋራ፣ እርሳቸውን ጨምሮ የከተማው የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች የተካተቱበት ምክክር እየተካሔደ እንዳለ አስታውቀዋል፡፡
እየተከሠተ ያለው የግፍና ጥፋት ድርጊት፣ ሕዝብን ከሕዝብ እያለያየ መኾኑ በእጅጉ እንደሚያሳዝናቸው ብፁዕነታቸው ተናግረዋል፡፡ “ተዉ ማለት ያለበት፣ ይህን ማስተካከልና መሥመር ማስያዝ ያለበት መንፈሳዊ አባት ነው፤” ሲሉ ቤተ ክርስቲያን ጥፋትን የመከላከል፣ አጥፊውን የማውገዝና የመገሠጽ፣ የተበደለው እንዲካስና እንዲጽናና የማድረግ በአጠቃላይ የአገርን ሰላምና የሕዝብን አንድነት የማስጠበቅ ከባድ መንፈሳዊና ታሪካዊ ሓላፊነት እንዳለባት አመልክተዋል፡፡
አባቶችና መንበረ ፓትርያርኩ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር በመዳፈርና ሥርዐቷን በመጣስ ጭምር ስለተፈጸመው የወልዲያው ግፍ፣ አቋማቸውን እንዲያሳውቁና ኖላዊነታቸውን እንዲያረጋግጡ በብዙኃን መገናኛዎችና በመግለጫዎች የሚሰነዘሩት ጥያቄዎችና ወቀሳዎች እንደቀጠሉ ናቸው፡፡
መኢአድ እና ሰማያዊ ፓርቲዎች፣ ከትላንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የጥምቀት እና የቃና ዘገሊላ በዓልን ለማክበር በወጡ የወልዲያ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ የተመለከተችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ድርጊቱን አለማውገዟ ያስተዛዝበናል፤ ብለዋል፡፡
ለተነሣው ግጭትና ለተወሰደው የግድያ ርምጃ የቀረበው ምክንያት፣ “መንግሥትን የሚቃወም ዜማ አሰማችሁ፤” የሚል እንደኾነ በመግለጫቸው የጠቀሱት ፓርቲዎቹ፣ “ይህ ደግሞ መብትን መጣስ ነው፤” ብለዋል፡፡
አክለውም፣ “የጸጥታ ኃይሎች ቅዱስ ታቦትን ባከበሩ ቀሳውስት ላይ አስለቃሽ ጭስ መተኮሳቸው ሃይማኖቱን መዳፈር በመኾኑ መንግሥት ድርጊቱን በማውገዝ የእምነቱን ተከታዮች በዐደባባይ ይቅርታ ይጠይቅ፤ ለሟች ቤተ ሰዎች የደም ካሳ እንዲከፍል፤ ግድያው እንዲፈጸም ትእዛዝ የሰጡም ኾነ ጉዳዩን በቸልተኝነት የተመለከቱ የዞኑ ባለሥልጣናት በሕግ እንዲጠየቁ፤ ግድያውን የፈጸሙ የመንግሥት ታጣቂዎች ለሕግ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን፤” ሲሉ አቋማቸውን አስታውቀዋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤን በመወከል በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ርእሰ መንበርነት አመራር የሚሰጠው ቋሚ ሲኖዶስ፣ ከልደት ጀምሮ በነበሩት ዐበይት ክብረ በዓላት ሳቢያ የተመደቡት ተለዋጭ አባላቱ ብፁዓን አባቶች በየአህጉረ ስብከታቸው በመኾናቸው አለመሰብሰቡ ተጠቁሟል፡፡ ሰሞኑን፣ እስከ ግንቦቱ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ድረስ በተለዋጭነት በተመደቡት አራት ብፁዓን አባቶች አባላቱ በሚቀጥለው ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባው፣ ጉዳዩን ይመለከተው እንደኾነም ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡