“ወንድሞች ሆይ እንመክራችኋለን ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገስጹዋቸው፣ ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው፤ ለደካሞች ትጉላቸው፣ ሰውን ሁሉ ታገሱ፣ማንም ለሌላው በክፉ ፋንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፣ ነገር ግን ሁል ግዜ እርስ በእርሳችሁ መልካሙን ነገር ለማድረግ ትጉ፡” 1ኛ ተሰሎንቄ 5፣14-1
ከማእከላዊ በፊት የደደቢት እምነት በሚለው ጽሁፌ የኢህአዴግም በሉት የወያኔ ግምገማም በሉት ጥልቅ ተሀድሶ ዋናውን መሰረታዊ ምክንያት የደደቢቱን እምነት አመለካከት እስካልነካ ድረስ ለውጥ ማየት እንደማንችል፣ የደደቢቱ እምነት አመለካከት ሊወገድ የሚችለው ደግሞ ከወያኔ ጋር አብሮ እንጂ ለብቻ ሊሆን እንደማይችል የታየኝን ለማሳየት ሞክሬ ነበር፡፡
ለማ እንዲህ አለ፣ ደጉ ይህን ቃል ገባ፣ መንግሥት ጥፋቱን አመነ፣ የሚሉ የሞኟ ቀበሮ (የበሬው እንትን ይወድቅልኛል ብላ አንጋጣ ስትከተል እንደምትውለው ማለት ነው ) አይነት ሰዎች በአንድ በኩል፤ ወያኔ በርግጥ ማንነቱን በገሀድ የሚያሳይበትን አረመኔያዊ ተግባር ሲፈጽም ከጓዳ መግለጫ፤ ከአንድ ሰሞን ጫጫታ ወዘተ የዘለለ ተግባር መፈጸም የተሳነን ከንቱዎች በሌላ በኩል ተበራከትንና ወያኔ እህት በሚላቸው ድርጅቶች እያላጋጠ በህዝቡ ላይ ቁማር እየተጫወተ እንዳለ አለ፡፡ እንዲህም ሆነና ንቀቱ፣ ማን አለብኝነት እብሪቱ ጣራ ነካና በታቦት ላይ እስከመተኮስ ደረሰ፡፡ ይህንንም ነገ እንረሳዋለን፡
ሞት እስራት እነርሱም እኛም ተለማምደነው ከአንድ ሰሞን ጉድ ጉድ የማያልፍ ተግባር ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ የሩቁን ትተን የቅርቡን የእሬቻውን እልቂት ፤የባህር ዳሩን ፍጅት፤ የሞቶ ሺህ ኦሮሞዎችን የሀገር ውስጥ ስደት ወዘተ ረስተነዋል፡፡የአብዛኞቹ ፖለቲከኞች ሥራ በእለት በእለቱ ነገር እየጮሁ አንድም ደጋፊ ማበራከት ሁለትም ገንዘብ መሰብሰብ እንጂ ምሬቱ አስመርሮአቸው ከማማረር ወደ ማምረር ሊሸጋገሩ አልቻሉም፡፡
ወትሮም በፍርፋሪ ለቃሚነት እንጂ በተቀዋሚነት የማንፈርጃቸው ፖለቲከኛ ተብዬዎችም የቱንም ያህል ህሊናቸውና ሆዳቸው ቦታ ቢለዋወጥ በኢትዮጵያ በማናቸውም ቦታና ምክንያት ዜጎች በየእለቱ እየተገደሉ ድርድር እያሉ ማላጋጥ አልነበረባቸውም፡፡
ደራሲ ሲሳይ ንጉሱ ትንሳኤ በተሰኘው መጽሀፉ ውስጥ # ለሥጋችን ባደርን ግዜ ደግሞ ህሊናችንና አእምሮአችን ጭራሹኑ እየበደነ ይሄድና ሙሉ በሙሉ ጭራውን የሚቆላ እንስሳ ወይንም ተናካሽ አውሬ ያደርገናል፡፡ በሰውነታችን ወስጥ የተሰጣቸው ቦታ የተለያየ ስለሆነ አቀርቅረን ሆዳችንን ስናይ ቀና ብለን አዕምሮአችንንና ህሊናችንን የማየቱን ነገር እንረሳዋለን፡፡ ሳናውቀው እንደድባለን፡፡አዕምሮና ህሊና በሆድና በስጋ እንዲታዘዙ እናደርጋለን፡፡ እንግዲህ ሰው የሆነ ሁሉ በአዕምሮው፣ በህሊናው መተማመን ሆድና ሥጋውን ለእነዚህ ተገዢ ማድረግ አለበት $ ነበር ያለው ፡፡ ይህ አባባል ስንቶቻችንን እንደሚመለከት ራሳችንን እንጠይቅ፡፡
የኃይማኖት አባት ተብለው የክርስቶስን መንገድ ሊያስተምሩ ቀሚስ ለብሰሰው መሰቀል አጥልቀው የምናያቸው ሰዎች ከአለማዊያኑ ብሰው ህሊናቸውን ለሆዳቸው ሲያስገዙ፣ አንደበታቸው በጎሳ ልጓም ሲሸበብ፣ አይናቸው እውነቱን አላይ ብሎ ሲንሸዋረር መመልከት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አማኞች የተለመደ የተለማመድነው ጉዳይ ቢሆንም እንዲህ ታቦት ተደፍሮ በአለ- ጥምቀት ወጣት የሚረሸንበት ቀን ሆኖ ሲያልፍ ዝም ጭጭ ያሉ የሀይማኖቱ መሪዎች ተብለው የተቀመጡ ሰዎችን ግን ከዚህ በላይ ልንታገሳቸው የሚገባ አይመስለኝም፡፡
ከክርሰቶስ ደጅ መቅረት ባይገባንም እጃችን ለእነርሱ መዘርጋት ለመስቀላቸው ግንባራችንን መስጠት ግን ልክ እየሰራችሁ ነው የአባትነት ተግባራችሁን እየከወናችሁ ነው ወዘተ ብሎ የማደፋፈር ያህል ይሆናል፡፡ ይህን ስል ሁሉንም አለማለቴ ይታወቅልኝ፡፡
መጽሀፍ ቀዱስም ይላል “በትልቅም ቤት የእንጨትና የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፡፡እኩሌቶቹም ለክብር እኩሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፡፡እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ ለክብርም የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎ ስራ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል፡፡” (ጢሞቲዎስ 2፣2፣20) ስለሆነም በእርግጥም የክርስቶስ ተከታይ ክርስቲያኖች ከሆንን ታቦት ካስደፈሩ ለክብር ሳይሆን ለውርደት ከቆሙ ጋር አብሮነት ሊኖረን አያሰፈልግም፡፡
የሀይማኖት አባቶች አይደለም እነርሱ በአባትነት በተሰየሙበት እምነት፤ የእምነቱ ታከታዮችና ስርኣተ ንግስ ላይ ለተፈጸመ ወንጀል ቀርቶ በማናቸውም የሰው ልጅ ላይ በየትኛውም ቦታ በማንም የሚፈጸሙ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን ሁሉ የመኮነንና የማውገዝ ተግባር ይጠበቅባቸው ነበር፡፡
ከላይ በመነሻየ የገለጽኩት የመጽሀፍ ቅዱስ ሀይለ ቃልም የሚለው ይህንኑ ነው፡፡ “ያለ ሥርዐት የሚሄዱትን ገስጹዋቸው”(1ኛ ተሰሎንቄ 5፣14-1) የእኛዎቹ ግን አንድም በፖለቲካው ተሸንፈው ሁለትም በጎሳ ልጓም ተሸብበው በታቦት ላይ አስለቃሽ ጥይት ተተኩሱ ታቦት ለማንገስ በወጣው ህዝብ ላይ የጥይት አረር ዘንቦ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ጭጭ አሉ፡፡ለዘመናት ራሱም ተከብሮ ሀገርንና ምዕምናኑንም አስከብሮ የኖረው የኦርቶዶክስ እምነት ትናንት በጳውሎስ ዛሬ በማትያስ ተዋረደ፡፡ታዲያ እንዲህ እምነታችንን ያዋረዱትን ሰዎች እናከብር ዘንድ ግድ የሚለን መንፈሳዊም ሆነ ዓላማዊ ህግ ይኖር ይሆን?
የክርስቶስ የሆኑ የእምነቱ አባቶችን ወደ መንበሩ ለማውጣት ሹዋሚ ሻሪ የሆነው ጠብ መንጃ ባያስችለንም የፖለቲካ ተሸዋሚ ለሆኑ በተለይም ሀይማኖታችንን አዋራጅ የሆነ ተግባር በሚፈጽሙ ስመ የሀይማኖት አባቶች አንመራም አንተዳደርም ለማለት የሚገደንና መስዋዕትነት የሚጠይቀን አይሆንም፡፡
ገጠር አብያተ ክርስቲያናት ሌላ ሌላው ሁሉ ቀርቶ ለእለት መቀደሻ ጧፍ እጣን በማያገኙበት ሁኔታ ተሹዋሚዎቹ ከተማ ተቀምጠው ከአለማዊያኑ ጋር እየተፎካከሩ መኖር ደረጃ የደረሱት ከምዕምናኑ በሚሰበስቡት ገንዘብ መሆኑ መጤን ያለበት ይመስለኛል፡፡ ድሀ እናት መቀነቷን ፈታ ድሀ አባት ኪሱን ዳብሶ የሚሰጡት ሙዳይ ምጽዋት እምነት ለሚያረክሱና ታቦት ለሚያስደፍሩ ሰዎች መንደላቀቂያ መዋል የለበትም፡፡ ስለሆነም ይህ አታድርጉ ማለቱ የሚቻለን ባይሆንም ለድርጊት የሚጠቀሙበትን ገንዘብ መንሳት ግን ተገቢና ሊቸግረን የማይችል ቀላል፤ ነገር ግን ትልቅ ውጤት ሊያመጣ የሚችል እርምጃ ነው፡፡
በየግዜው የታዩ ችግሮችን በለዘብታ እያለፍን ወይንም እኛ ከእምነታችን እንጂ ከእነርሱ ምን ጉዳይ አለን በሚል ንቀን እያለፍን ነው ዛሬ ታቦት ለማስደፈር አስደፍረውም ዝም ጭጭ ለማለት ደረጃ የተደረሰው፡፡ ጥቂቱን እንኳን ብናስታውስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከለላ ትሆነናለች ከአምባገነነን ዱላ ታስጥለናለች ብለው ተማምነው ከተጠለሉባት ከአምስት ኪሎ ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን ቅጽር ግቢ ታጣቂዎች ዘልቀው እያፈኑ ሲወስዱዋቸው የእምነቱ አባቶች የተባሉት በተባባሪነት ከመሰለፍ ባለፈ ሊከላከሉ ቀርቶ ድርጊቱን በቃላት እንኳን ሊያወግዙ አልቻሉም፤ እኛ ምዕምናኑም ከአንድ ሰሞን ጩኸት ያለፈ ያልነውም ያደረግነውም ነገር አልነበረም፡፡
እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ከታቦት ፊት አውደ ምህረት ላይ ባህታዊ ሲገደሉ እንዲሁ፤ ዋልድባ ገዳም ሲደፈር አናስደፍርም ያሉት በእምነታቸው የጸኑት ታፋነው ሲወሰዱና ታስረውም ሲሰቃዩ እንዲሁ፣ ሌላም ሌላም፡፡ እናም የናቁትን ሀገር በአህያ ይወሩታል እንዲሉ ሆነና ይኼው ዛሬ ታቦት ላይ አስለቃሽ ጭስ መተኮስ ደረጃ ተደረሰ፡፡
በ1990 ዓ. ም ነው፣ አንድ መጽሄት ለቤተ እምነቱ ቅርበት የነበራቸውን ፕ/ር ታደሰ ታምራትን የሀይማኖት አባቶች ትክክለኛ ተግባራቸውን ለመወጣት ስላልቻሉበት ምክንያት ጠይቋቸው ሲመልሱ “የዚህን አይነት እንቅሰቃሴ ለማድረግ እኮ በራስ መተማመንን የሕዝብም የፖለቲካ ፓርቲዎችም የመንግሥትም እውነተኛ ከበሬታና አመኔታ አለኝ ድምጼ ሙሉ ተሰሚነት ያገኛል ብሎ ርግጠኛ መሆንን ይጠይቃል፡፡እንደዚህ ለማድረግ የሚችሉ መንፈሳዊ አባቶች ራሳቸው የሚከተሉት የጽድቅ ኑሮ ከነሱ አልፎ በምዕምናኑም መካከል እያንጸበረቀ በሚከተላቸው ሕዝብ ዘንድ እግዚአብሔር ሁል ግዜ ጠንካራ እምነትና ብሩኀ ተስፋ ያጎናጸፈላቸው ዕድለኛ ቅዱሳን ብቻ ናቸው፡፡
እንደዚህ ያሉት አባቶች የተጠቀሰውን ዓይነት የዕርቅና የገላጋይነት በጎ ሥራ ሊሠሩ የሚችሉት በሃይማኖት በሚከተላቸው የራሳቸው ሕዝብ መካከል ብቻ ሳይሆን ከቅድስናቸው የተነሳ በቋንቋም ሆነ በሃይማኖት የሚለዩ ሳይቀሩ በከበሬታ ያዳምጧቸዋል፡፡ የጥንት ፃድቃን አባቶቻችንማ ሰውና እንስሳትንም ሳይቀር የማስታረቅ በረከት ከአምላክ ተሰጥቷቸው ነበር የሚል ጠንካራ እምነት በየገድሎቻቸው ተዘግቦ እናገኘዋለን” ብለው ነበር፡፡
እንደነዚህ አይነት አባቶች ለማግኘት እግዚአብሄር ይርዳን እኛም እንትጋ