የቴዲ አፍሮ ማናጀር አቶ ጌታቸው ማንጉዳይ ስለ ባህር ዳሩ ኮንሰርት ለአዲስ አድማስ ሲናገሩ “የሆነ ጫፍ የደረሰ ስሜት ነበር” ይላሉ።
*******
· የሙዚቃ ድግሱን 65 ሺህ ሰው ገደማ ታድሞታል
· መላው የኢትዮጵያ ምድር አገራችን ነው
· በሌላ ትልቅ ከተማ ቀጣይ ኮንሰርት ይኖረናል
ብዙዎች በጉጉት ሲጠበቁት የነበረው “ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር” የተሰኘው የድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የሙዚቃ ኮንሰርት፣ ባለፈው ሳምንት እሁድ፣ በባህርዳር ስታዲየም በስኬት ተጠናቅቋል፡፡ ሆኖም ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ረብሻ እንዳይፈጠርና ዝግጅቱ እንዳይበላሽ በአዘጋጆቹ ዘንድ ከፍተኛ ስጋት ነበር፡፡ በባህርዳር ወጣቶች ቀና ትብብር ግን ኮንሰርቱ በሰላምና በስኬት መጠናቀቅ ችሏል – ይላሉ የቴዲ አፍሮ ማናጀር፣አቶ ጌታቸው ማንጉዳይ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከአቶ ጌታቸው ማንጉዳይ ጋር የአፍታ ቆይታ አድርጋለች፡፡
እንደ ማናጀር የባህርዳሩ ኮንሰርት ምን ያህል ውጤታማ ነበር ትላለህ?
ለእኔ ስኬቱ ትልቅ ነው፡፡ ከአራቱም ማዕዘን ህዝብ ተገናኝቶ፣ ኢትዮጵያዊነታችንን አክብረን፣ ያለ ምንም እንከን መጠናቀቁ በጣም ድንቅ ነው። ለባህርዳር ከተማም፣ ለእኛም፣ ለህዝቡም ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በጣም ደስ ብሎናል፡፡
ኮንሰርቱ ያለ ችግር፣ በሰላም እንዲከናወን፣ የባህርዳር ወጣቶች አስተዋጽኦ ምን ነበር?
እውነት ለመናገር፣ ኮንሰርቱ ያለ ባህርዳር ወጣቶች፣ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል እርግጠኛ ሆኜ ነው የምነግርሽ፡፡ ምንም ነገር ያለ እነሱ ተሳትፎ አይሳካም ነበር፡፡ “ሁሉን ነገር ለእኛ ተውልን” ነው ያሉት፡፡ እኛ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ያለውን የፀጥታውን ችግር ሁሉ እናውቃለን፤ ሳናውቅ አይደለም የገባነው፡፡ ለወጣቶቹ ምን አልናቸው መሰለሽ? “እኛ በመትረየስ ተጠብቀን አናውቅም፤የእኛ ኮንሰርት በታንክ ተጠብቆ አያውቅም፤ የመጣነው እናንተን ብለን ነው፡፡ ቆመን የምንሄደው በመድሀኒያለም ሀይል ነው። ከመድሀኒያለም ቀጥሎ ደግሞ እናንተ ጠብቁን” አልናቸው፡፡ እነሱም ደግሞ ሁሉን ነገር በጉልበት ሳይሆን በፍቅር ተቆጣጥረው፣ ኮንሰርቱ የተሳካና የሚያምር እንዲሆን አደረጉ፡፡ በጣም ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡ ለባህርዳር ወጣቶች ትልቅ ውለታ አለብን፡፡ ወደ 300 የሚጠጉ ወጣቶች ናቸው፤ይህን ትልቅ ሀላፊነት ጫንቃቸው ላይ ተሸክመው ስኬቱን ያመጡት፡፡
“ጃ ያስተሰርያል” እንዲዘፈን ታዳሚው አጥብቆ ቢጠይቅም አንተ ግን እንዳይዘፈን ከልክለሃል፡፡ ውሳኔዬ ትክክል ነው ብለህ ታምናለህ?
አዎ፤ በትክክል አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም እዚያ ቦታ ላይ ሴቶች፤ ህፃናትና ወጣቶች ነበሩ፡፡ ያ ዘፈን እንዲዘፈን ያልፈቀድኩት፣ ከቴዲ ይልቅ ለህዝቡ በማሰቤ ነው፡፡
እንዴት ማለት?
መስዋዕትነት ለቴዲ አዲስ ነገር አይደለም፤ ብዙ መስዋዕትነት ሲከፍል ነው የኖረው፡፡ ይሄ ለእኛ አዲስ አይደለም፤ ነገር ግን የሆነ ጫፍ የደረሰ ስሜት አለ፡፡ ያ ዘፈን እንዲዘፈን ቢፈቀድ፣ የህዝቡ ስሜት በቀላሉ የሚቆም አልነበረም፡፡ እዚያ ቦታ ላይ ህፃናት፣ ሴቶችና ወጣቶች እያሉ፣ ህዝቡ ስሜቱን መቆጣጠር ቢያቅተውና፣ በእኛ ምክንያት አንድ ሰው ላይ አንድ ጉዳት ቢደርስ፣ በህሊናችን ጥቁር ነጥብ ጥሎ ነበር የሚያልፈው፡፡ ትልቅ ፀፀትም ይሆን ነበር፡፡ ስለዚህ ያንን እርምጃ በመውሰዴ፣ ትክክል ነኝ ብዬ አምናለሁ፡፡
ባህርዳር ስቴዲየም በጣም ትልቅ ነው፡፡ ምን ያህል ታዳሚ በኮንሰርቱ ላይ ተገኘ?
ከ60-65 ሺ ሰው ተገኝቷል፡፡ በጣም የሚገርም ስኬት ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ህዝብ ታድሞ፣ ያለ እንከን መጠናቀቁን ስመለከት፣ ሥራውን የሰራው መድሀኒያለም ነው እላለሁ፡፡ ያለ እርሱ እርዳታ፣ ይሄን ከባድ ስራ መስራት የማይታሰብ ነው፡፡
በሌሎች ከተሞችስ ቀጣይ ኮንሰርቶች አላሰባችሁም?
እንግዲህ መላው የኢትዮጵያ ምድር አገራችን ነው፡፡ በቀጣይ በአንድ ትልቅ ከተማ፣ ከትልቅ ህዝብ ጋር፣ በደማቅ ኮንሰርት እንገናኛለን፡፡ ቦታውንና ጊዜውን ቀኑ ሲቃረብ ይፋ እናደርጋለን፡፡ በባህርዳር በስኬት ለተጠናቀቀው “ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር” ኮንሰርት ግን ፈጣሪንም፣ ለስኬቱ የደከሙትን አካላትም፣ ህዝቡንም በጣም እናመሰግናለን፡፡