ህዝቦች እኩል ከሆኑ እኔና መሰሎቼን ህዝቦች በሉንና ባንዲራችንን መልሱልን…

ህዝቦች እኩል ከሆኑ እኔና መሰሎቼን ህዝቦች በሉንና ባንዲራችንን መልሱልን…

/አስቴር በዳኔ/

ቱባ የተባሉ ባለስልጣናት እና ልማታዊ አርቲስቶችን ጨምሮ በርካታ ካድሬዎች በተገኙበት የደደቢት ጉዞ ላይ የህወሀት አመራሮችን ስልጠናችሁን ልቀቁ እስከማለት የዘለቀ ደፋር ንግግር በማድረግ የሚታወቀው ተዋናይት አስቴር በዳኔ ሰሞኑን በማህበራዊ መገናኛዎች በምታቀርባቸው ጽሁፎችና በተለይ የኢትዮጵያ ባንዲራን በተመለከተ የምታቀርበው መጣጥፍ በርካቶች የሚጋሩት ሆኖ ሰንብቷል።

ካቀረበቻቸው ጥያቄዎችም …

ይህቺን ባንዲራ ከሃገሬ ላይ ሊያጠፏት ይችላሉ። ከልቤ ውስጥ ግን ለሰከንድ ሊያጠፏት አይችሉም። …የዜጎችን መብት ለማክበር ቃል የገባ መንግስት የዚህችን ባንዲራ አፍቃሪዎች ረስቶና ጨፍልቆ ስለ ዜጎች እኩልነት ማውራት አይችልም.. .ብሄር.
ብሄረስቦችና ህዝቦች
እኩል ከሆኑ እኔና መሰሎቼን ህዝቦች በሉንና ባንዲራችንን መልሱልን…እናንተም የራሳችሁን እውልብልቡ። በባንዲራችን ምክንያት አትግደሉን። በቃ!!! ልለምናችሁ።

የሚለው መልእክት የሚገኝበት ሲሆን አስቴር ሃሳቧን በድፍረት በመግለጿ የሚደርሷትን ምልክቶች እንዲህ ታስነብባለች…

ሰሞኑን
ከፌስቡክ ውጭ በአካልና በስልክ የሚደርሱኝ መልዕክቶች፦

ቤተሰቦቼ፦
አንቺ ልጅ አርፈሽ አትቀመጪም እነዚህ ምስኪን ልጆችሽ አያሳዝኑሽም

አንዳንድ ሰዎች፦
አንቺ ልጅ ማንን ተማምነሽ ነው? አትፈሪም ? መኖር አትፈልጊም በእሳት ትጫወቻለሽ? እነ እንትና ላይ የደረሰውን አልሰማሽም? እየው ነግረንሻል ሴት መሆንሽን አትርሺ…ወይ ከሃገር ውጪ…

ወገኖች ፦
አስቴርዬ በርቺ። በጣም ነው የኮራንብሽ ሰው የለም ብለን ተስፋ ቆርጠን ነበር። አይዞሽ ለሁሉም ቀን አለው ከጎንሽ ነን። እውነት ነፃ ታወጣሻለች እግዚአብሔር ይጠብቅሽ…ብቻ እየተጠነቀቅሽ…

የመንግስት ደጋፊ ነን የሚሉ፦
ስሚ አርፈሽ ተቀመጪ! አጉል ጀግና ለመባል ነው?! በረጅም ገመድ እንደታሰርሽ እወቂያት! ከፈለግን ሳብ ማድረግ ነው። የምን እዩኝ እዩኝ ነው?! አርፈሽ ድራማሽን ስሪ!!!

ጥቂት ከፍተኛ ባለስልጣናት ፦
አንቺኮ ያመንሽበትን ሃሳብ ፊትለፊት በግልፅና በድፍረት መናገር የጀመርሽው ዛሬ አይደለም ። ሃሳብሽን በነፃነት መግለጽ ዲሞክራሳዊ መብትሽ ነው። ወደ አመፅ እስካልሄድሽ ድረስ። እንደውም ጠንከር ብለሽ ለምን የፖለቲካ ፓርቲ አትመሰርቺም። አያያዝሽ ከአርቱ ይልቅ ወደ ፖለቲከኛነቱ እያመዘነ ነው።…

ልጆቼ፦
ኧረ እማ ሰሞኑን አልተቻልሽም በጣም ተቀይረሻል። ግን አይዞሽ አትፍሪ የመሰለሽን አድርጊ …ግን ቢያስሩሽስ? እኛስ እንዴት እንሆናለን?…ግን እግዚአብሔር አለልን…

እኔ ለራሴ፦
አስቴርዬ አይዞሽ ልጆችሽን የሰጠሽ እግዚአብሔር ነው። የነሱን አደራ ለሱ ስጭው። ፍርሃት ቀድሞ የሚገድል በሽታ ነው! እየሞቱ የውሸት ከመኖር እየኖሩ መሞት ይሻላል። በዚህች ምድር ላይ የምትኖሪው አንዴ ነው። ትርጉም ያለው ዘመን አይሽሬ ስራ ሰርተሽ፤ የህዝብን ድምፅ አስተጋብተሽ ለእውነት ብትሰዊም አትከስሪም። ያለሽን ሁሉ ለሀገርሽ ስጭ። በቅንነት ለመታገል ከወሰንሽ መለወጥ የማይቻል ነገር የለም። አንድ ሰው ብዙ ነው። ኢትዮጵያ ላይ ሰላም እስኪሰፍን እንዳትተኚ። ከወገኖችሽ ጎን ቁሚ። እውነትን ግለጪ። ለኔ ሳይሆን ለኛ ከሚሉት ቆራጦች ጎን ቁሚ። ሃሳብሽን በምክንያትና በእውቀት ላይ ተመስርተሽ ማንፀባረቅሽን እንዳታቆሚ። እመኚ እንጂ አትፍሪ ለውጥ ይመጣል ። ኢትዮጵያ መሀን አይደለችም። በፍፁም አትፈራርስም!!!

LEAVE A REPLY