ለአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ
የ.ኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር
አዲስ አበባ
ሀ. ጉዳዩ፡- ምን በድዬ ይሆን?
ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር እኔ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ የተባልኩትን ግለሰብ ከስሜ እና ከአንዳንድ ነገሮች ውጪ ብዙም ስለ እኔ ያውቃሉ ብዬ ስለማልገምት ስለ ራሴ አጭር ገለፃ ሳደርግ በድፍረት ሳይሆን አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ መሆኑን በቅድሚያ ለመግለፅ አወዳለሁ፡፡
አመልካች በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ስዊድናዊ ስሆን በደርግ ጊዜ የነበረው የቀይ ሽብር ዘመቻ ሁለት ወንድሞቼን አጥቼ እኔም ተሰድጄ በስዊድን ሃገር 43 አመታትን አስቆጥሬያለሁ፡፡
ክቡር ጠ/ሚኒስቴር ከ25 አመታት የስደት ኑሮ በኋላ ባለን የልብ ህክምና ሙያ ሃገሬን እና ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼን ለማገልገል በመወሰን ከስዊድን መንግስት እና ስዊድናውያን ባለሃብቶች እንዲሁም ጥቂት ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ ጋር በመሆን በአይነቱ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነ ሆስፒታል በአዲስ አበባ እንዲከፈት በማድረግ ያከናወንኳቸው፡-
1ኛ. ሕክምናው እና መሳሪያው በኢትዮጵያ ውስጥ ባለመኖሩ ለዘመናት ለህልፈተ ሕይወት ይዳረጉ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች እድሉን በሃገራቸው እንዲያገኙ ሕይወታቸውን ለመታደግ ችያለሁ፡፡
2ኛ. በኢትዮጵያ ውስጥ በሙያው የሰለጠኑ አንድም ኢትዮጵያዊያን የልብ ሃኪሞች ስላልነበሩ ባለፉት 10 ዓመታት ስድሰት ሐኪሞች ወደ ሲዊዲን በመላክ ልዩና ዘመናዊ የልብ ስፔሻላይዜሽን ሰልጥነው ወደ አገራቸው በመመለስ ፈር ቀዳጅ የሆነውን ሕክምና በሃገራችን ውስጥ እንዲያከናውኑ ረድቻለሁ፡፡ እንዲሁም ቁጥራቸው ትንሽ የማይባል ነገርሶችም ወደ ስዊድን ሄደው ልዩ ትምህርት አግኝተው በመምጣት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
3ኛ፡ ይህንኑ ልዩ የልብ ሕክምና ለማግኘት ወደ ውጭ የሚሄዱትን ኢትዮጵያውያን እዚሁ ሕክምናውን እንዲያገኙ በማድረግ ሀገሪቱ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማሰቀረት ተችሏል፡፡
4ኛ፡ ወቅታዊ ለሆነው እና ታላቅ ሃገራዊ ፋይዳ ያለው የሕዳሴው ግድብ መሰረት ከተጣለ በኋላ በተከናወነው የቦንድ ግዥ መሰባሰብ ሥራ የግሉን የጤና ዘርፍ ወክዬ ከዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር በመሆን የብዙ ሚሊኒዬች የቦንድ ግዥና እርዳታ እንዲፈፀም በማድረግና በተጨማሪም የግሌና በህክምና ሆስፒታሉም ስም ቦንድ በመግዛት ሀገራዊ ግዴታዬን ተወጥቻለሁ፡፡
ወደ ጉዳዬ ስገባ :_
ለ. ባለፈው የፍርድ ሂደት፡
1. በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. ከቀድሞው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣኖች ጋር የጥቅም ግንኙነት በማድረግ ክስ እንዲቋረጥ አድርገሃል ተብሎ ክስ ተመሰረተብኝ፤
2. ከ 3ዓመት የተጓተተ የፍርድ ሂደት በኋላ ምንም አይነት የሰነድም ሆነ የሰው ማስረጃ ሳይቀርብብኝ በስሚ ስመሚ ብቻ ክሱን እንከላከል ተበየነ፤
3. ክረምቱ ካለፈ በኋላ በሚኖረው የፍርድ ቤት ሂደት በኋላ ክሴን ለመከላከል ስዘጋጅ በድንገት ነሀሴ 27 ቀን 2008ዓ.ም. ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተልኬ በዕለቱ የግራ ሳንባ መበላሸት (ኮላፕስ) ስለደረሰብኝ የመጀመሪያውን የሳምባ ህክምና ተደረገልኝ፡፡
4• በተከታታይ የግራ ሳምባዬ እየተበላሸ በማስቸገረ ወደ ውጭ ሀገር ብቻ ሄጄ የቀዶ ጥገና ማድረግ እንዳለብኝ አምስት የጥቁር አንበሳ ቦርድ ስፔሻሊስቶች በውሳኔ አረጋገጡ
5. በነበርኩበት ሁኔታ የፍ/ቤት ሂደቴን ልከታተል ባለመቻሌ ለለመከላል ስወስን፤ አፋጣኝ ፍትህ በማግኘት ወደ ውጭ ሃገር ሄጄ ለመታከም በማሰብ ሲሆን በእርስዎ ድጋፍ እና ትብብር አፋጣኝ ፍርድ እንዳገኝ ተደርጎ፤ ችሎቱ በተኛሁበት ሆስፒታል ድርስ በመምጣት የ4 አመት ከ8 ወር እስራት ፍርድ መሰወኑ ተገልፀልኝ፡፡ ይህ ወሳኔ ከታሰርኩበት ጊዜ ጀምሮ ስለሚቆጠር እንደምታ ተስፋ አድርጌ ስጠብቅ፤ ባልነበርኩበት እና ስብእናዬም ሆነ ሙያዬ የማይመጥን በፈጠራ ላይ የተመሰረተ ሌላ ክስ ቀረበብኝ፡፡
6• በሽታዬ መታከም አለበለዚያ መሞት መርጫ ስለነበረ የስዊድን ሐኪሞች በመምጣት ከኢትዮጵያዊያን ሐኪሞች ጋር በመሆነን ኦፕራሲዬን አድርገውልኝ ለጊዜው ሕይወቴ ሊድን ችሏል፡፡
7. የግራ ሳምባዬ ላይ የተከሰተው በሽታ ሳምባዬ ላይ ሊከሰት ስለሚችል የሚፈነዳ ቦምብ በሰውነቴ ይዤ ህክምና በማላገኝበት ሁኔታ ላይ እገኛለሁ፡፡
8• የተፈረደብኝን ፍርድ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለት ችሎቱም በተፋጠነ ሁኔታ መርምሮ ክሴን እና ፍርዱን ውድቅ በማድረግ በነፃ አሰናብቶኛል፡፡
ሐ. የአሁኑስ ክስ የፍርድ ሂደት
በጥቅሉ ክሱ በሚለው በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በተሳው እረብሻ ቃጠሎ የ23 ታራሚ ህይወት እና ንብረት ለመውደሙ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ የገንዘብና የማስተባበር እርዳታ ግንቦት 7 ለተባለ “ሽብርተኛ” ቡድን በማድረግ ተሳትፈዋል፤ አንቀፁ ቢያንስ 15 አመት ፅኑ እስራት አለበለዚያም ሞት ያስፈርዳል ይላል፡፡
1ኛ ምስክር ም/ሳጅን ———– የማረሚያ ቤቱ የዞን ሁለት ቤት ደልዳይና ተቆጣጣሪ ሲሆን፡
‹ዶ/ር ፍቅሩ በነገሩኝ መሰረት ለድሆች ልብስ መግዣ እና ለዋሰትና የሚሆን አራት ጊዜ በጠቅላላው ብር 176000.00 የምሳ ሳህን ስለማይፈተሸ (በሃሰት) አስገብቼ በቢሮ ውስጥ ሰጥቻለሁ፡፡ ገንዘቡም የተቀበልኩት ከማላወቀው ሰው ነው ብሏል፡፡
የሚደንቀው ነገር ግን ይህ ማረሚያ ቤት አባል ሀገሩንና ህገ መንግስቱን ለማክበር ምሎ ሊያገለግል የነበረ፤ ይህንን ይቅር የማይባል አንዴም ሳይሆን ለ4 ጊዜ እና (ለሌላም ተከሳሽ አስገብቻለሁ) ብሎ መስክሮአል፡፡ ሆኖም ይህን እምነት አጉድሎ አሁንም ተመልሶ በማረሚያ ቤት ውስጥ ስራውን ቀጥሎ መገኘቱ ነው፡፡
2ኛ ምስክርም የማ/ቤቱ የሚገኝ በከባድ ነፍስ ማጥፋት ወንጀል የተከሰሰና ማስረጃ የተሰማበት የህግ ታራሚ ሲሆን፡-
‹ ዶ/ርን አንድ ቀን የሆነ ሰው ሲያስተዋውቀኝ ደርሻህ ነው ብለው ገንዘብ ሰጡኝ፡ ከዚያ ቀጥሎ ነሀሴ 28 ቀን 2008ዓ.ም. የቃጠሎው ቀን ጠዋት ሌላ ገንዘብ ሰጡኝ› በገንዘቡ ግን ምንም ሳላደርግበት ተቃጠለ ብሏል፡፡ (እኔ ነሀሴ 28 ቀን 2008ዓ.ም. በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተኝቼ በህክምና ላይ ነበርኩ፡፡)
3ኛ ምስክር፡-ከፍተኛ የክልል መንግስት የደህነነት ክፍላ ሃላፊና የገቢዎችም ዳይሬክተር የነበረ፤ አሁን በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተከሰሰ ነው፡፡ በሰጠው ምስክርነት ‹ እኔና ዶ/ር ፍቅሩ አንተዋወቅም ታስረን የነበርነውም በተለያየ ዞን ነው ። ነገር ግን እሳቸው የግንቦት ሰባት አባለትን በገንዘብ ይረዳሉ ሲባል ሰዎች ሲያወሩ ሰምቻለሁ፡፡” ብሎ ነው የመሰከረው፡፡
4ኛ ምስክር፡- የፌዴራል ፖሊስ የነበረ በከፍተኛ ውንብድና የተከሰሰ ነው፡፡ በሰጠውም ምሰክርነት “አንድም ቀን የኦነግ አባል በመሆን የተጠረጠሩና፤ የኦነግ አባል ነኝ ብሎ ያናገረኝ ታራሚ በማረሚያ ቤቱ ሜዳ ላይ በግልጽ ‹ታይኳንዶ› ሰሰለጥኑ ‹አይዞአችሁ› በርቱ ጊዜው ደርሷል ብከው ሲያበረታቱ ሰምቻለሁ፤ እንዲሁም አንድ የአዕምሮ በሽተኛ ዱላ ይዞ ራቁቱን በመሆን ከ 1000 በላይ ለሚሆኑ ታራሚዎች እያባረረ በየክፍላቸው ሲያስገባቸው እሳቸው ብቻ አጠገቡ ሄደው ‹ አይዞህ ንዳቸው› ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ “ብሎ መስክሯል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር የሚገርመው እና የሚደንቀው አቃቤ ህግ በቃጠሎው ለምን እንዳልነበርኩ ሲያብራራ ‹ መድሃኒት ወስጄ አሞኛል ብዬ ወደ ሃኪም ቤት እሄዳለሁ እናንተ ቀጥሉ› ብሎአል ይላል፡ ሌላው አስገራሚ ነገር ደግሞ በሁሉም ደረጃ ሲወራ የነበረው ‹ ዶ/ር ፍቅሩ የስኳር በሽተኛ ስለሆኑ ብዙ ቼኮሌት በመብላት ሳምባቸውን አፍንድተው ነው ሆስፒታል የገቡት ተብሏል፡፡›ቢሆን እንኳ የቼኮሌት መድረሻ ጨጓራ እንጂ ሳምባ መሆኑን ሳይንስ አላረጋገጠም፡፡ ምን አልባት መለኮታዊ ኃይል ይሆን?
መ. እኔ በመታሰሬ የደረሰ ጉዳት
1ኛ፡ በእኔ ተማምነው በየ 7 ዓመቱ የሚቀየር የልብ ማንቀሳቀሻ ባትሪ ሕክምና የወሰዱ ዜጎች ይህንን የሚሰራ ሌላ ሃኪም በኢትዮጵያ ባለመኖሩ ብዙ ህሙማን ለሕልፈተ ህይወት ተዳርገዋል፤ እየተዳረጉም ነው፡፡
2ኛ. በእኔ ሙያ ሊታከሙ የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ተጎድተዋል፡፡
3ኛ. ፈር ቀዳጅ የሆነው የልብ ሆስፒታል በብዙ ሚሊዮን ዶላር ሊስፋፋ የነበረው ባለበት ቆሟል፡፡
4ኛ. ከስዊድን በመምጣት የልብ ቀዶ ጥገና የሚያደርጉ ሀኪሞች እኔ በመታሰሬ መምጣት አቁመዋል፡፡
5ኛ. በመጀመሪያው የፈጠረራ ክስ ከ 4 ኣመት እስር እና እንግልት በኋላ ነፃ መሆኔ የእኔን፤ የቤተሰቤን እና የወዳጅ ዘመዶቼን ቅስም በከባድ ሁኔታ የሰበረ እና ለከፍተኛ ጉዳትና እንግል የዳረገ ነው፡፡
6ኛ. እኔ በሐሰት እና ማስረጃ በሌለው ጉዳይ በተደጋጋሚ ክስ ሲቀርብብኝ እኔን ያዩ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ከመጠራጠራቸውም አልፎ ለለመምጣት እስከመወሰን ይደርሳሉ፡፡
7ኛ. ሰዊድን እንደ ነጻ ሃገር ና የአውሮፓ ማህበር አባል በመሆኗ በስዊዲን ሲቀጥልም በአውሮፓ እና በኢትዮጵያ ግንኙነት ላይ ተፅእኖ ሊያደርስ ይችላል፡፡
8ኛ. በየጊዜው በሐሰት ተከስሼ ከብዙ አመታት አስርና እንግልት በኋላ ነፃ መውጣት የፍትህ ስራአቱ በህዝብ ዘንድ ያለውን ተአማኒነት በከፍተኛ ደረጃ ያሳጣል፡፡
ሠ. እኔ በመታሰሬ የተገኘ ወይም የሚገኝ ጥቅም ስላለመኖሩ፡
ኢትዮጵያ እንደ ሃገር፤ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ መንግስት በእኔ መታሰር ጉዳት እንጂ ምንም ጥቅም አላገኘም፡፡ ወደፊትም አይገኝም፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር፡- ማንም ሰው ከህግ በላይ እንዳልሆነና ካጠፋ በህግ ሂደቱ አፋጣኝ ፍትህ በማግኘት ተመጣጣኝ እና አስተማሪ የሆነ ቅጣት መቀበል እንዳለበት ጠንቅቄ የማውቅ ነኝ፡፡ እርስዎም በፍትህ ስርአቱ ውስጥ ጣልቃ ገብተው የእኔን ጉዳይ እንዲመለከቱም አይደለም፡፡ የኔ ዋና ጥያቄና ለብዙ አመታት አእምሮዬን በማስጨነቅ፤ ዘመድ ወዳጅን በማወያትና በመጠየቅ ለዚህ ሁሉ መከራና ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ምን ጥፋት አጥፍቼ እንደሆነ ብፈልግ ምንም ነገር ባለማግኘቴ ለህሊናዬ ምላሽ ያጣ ጥያቄ በመሆኑ ምናልባት ባልዎት ሥልጣን እና ሃላፊነት ለአንድ ሰው መቆርቆር ለሞላው ህዝብ መቆርቆር ነውና ለጥያቄዬ ምላሽ ያገኙልኛል በሚል ከፍተኛ እምነት ላይ በመመስረት ነው፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር፡- ትናንት የሰራነው የዛሬ ታሪክ ነው፤ ዛሬ የምንሰራው የነገ ታሪክ ነውና የለብዎትን የጊዜ መጣበብ ከግምት በማስገባት በሚያመችዎ መንገድ ምላሽ እንዲሰጡኝ በትህትና እና በአከብሮት አጠይቃለሁ፡፡
ከከበረ ሰላምታ ጋር
ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ
ከአ/አ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት