* የተበላበት ሳውዲ …
* የምሽቱ ብስራት …
* እኔና ስደቱ …
* እናቴ ሆይ ደስ ይበልሽ …
ቀኑ ብሩህ ነበር … ማልጀ ቢሮ ገብቸ እንደወጣሁ ልጆቹን ወደ ሀገር ከሚልክ ከወንድም የከበደ ወዳጄን ጉዳይ ለመከታተል አብሬው ወዲህና ወዲህ ስል አመሸሁ። ተመላሹ ወገን እቃውን በኮንቴነር ለመላክ ከገባው ጣጣ እስከ ቀጣዩ የወገን ኑሮ ስጋት ከወዳጄ ጋር አንዱንም አንዱንም ሲያደርግ እየተመለከትኩ መታዘብ አልገደደኝም። “ስደቱ ከፍቷል” የሚለው ሰሞነኛውን የሳውዲ ስደተኛ ውሎ አዳር ጉዳይ የሚገልጸው አይመስለኝም። ከወዳጄ ጋር ጉዳየን ጨርሸ ሳንለያይ የስልክ መረጀ ደረሰኝ። መረጃው ከዚህ ቀደም ደጋግሞ የደረሰኝ መረጃ ነበር። ደጋግሜ ሰማሁት …
ጉዳዩ ከ200 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ነበር። የሀበሻ ደም ያለው ሳውዲ አሰሪና ሀበሾቹ በስራ ጉዳይ ተገነኝተው ” ሲያልቅ አያምር !” እንዲሉ አበው ስራ ጥፍቶ አሰሪና ሰራተኛ ተካርረው ጉዳዩ ጅደ ቆንሰል ድረስ ደርሷል። የጅደ ቆንስል ሽምግለና የ30 ሀበሾች መኖሪየ ፍቃድ አንዲታደስ ምክንያት ቢሆንም አሁን ላይ ከስራ ስራ የሌላቸው 200 ሀበሾች ጉዳይ አሳሳቢ ሆኗል። በሀበሻው ሳውዲ አሰሪና በቀሩተ ሀበሾች መካከል ያለው ግንኙንት ሻክሮ ነገር ወደ መበለሸቱ እየተጋዘ መሆኑን የደረሰኝ መረጃ ጠቋሚ ነበር ። እናም አንተም ተው አንተም ተው ለማለት ስልክ ስደዋውል አመሽሁ። ይህን ያስባለኝ የጉዳቱን መጠን ተረድቸው ነበርና ነው ። እናም ያለፈውን እያስታወስኩ መጭውን አስፈሪ ጊዜ በምናቤ አውጥቸ አወረድኩት !
የተበላበት ሳውዲ …
ከ22 ዓመት በፊት ወደ ሳውዲ ስመጣ ” ከተበላበት በኋላ መጣችሁ !” ይሉን ነበር። ዳሩ ግን ጥረን ግረን ሰርተን በመለወጥ፣ ትዳር መስርተንና ልጆች አፍርተን፣ ያማረ ኑሮን በሳውዲ ያሳለፍን ሳውዲን እንደ ሁለተኛ ሀገራችን የምንቆጥራት ሀበሾች ቁጥር እልፍ አዕላፍ ነው ። ሳውዲዎች አለም አቀፍ ስደተኞችን ድንጋጌዎች ተስማምተው አለመፈረማቸው ይጠቀሳል። ያም ሆኖ ሳውዲዎች የሚመሩበት የእስልምናው የሸሪአ ህግ ለስደተኛው ከአለም አቀፉ ህግ በላይ ለሰብአዊ ክብር ቦታ የሚሰጥ ቢሆንም ከትግበራው ይሰራበታል ለማለት አይቻልም። ኑሮን ለማሸነፍ ወደ ሳውዲ በህጋዊና በህገ ወጥ መንገድ ሳውዲ የከተመውን ስደተኛን በአለም አቀፉ ስምምነት መሰረትም ሆነ የሸሪአው ህግ ተከትለው መብቱን ጠብቀው አያስተናግዱትም።
ስደተኛውን እንደ ቀረው ስልጡን አለም ቋሚ የመኖሪያ ፍቃድ ፣ ጥገኝነትና ሌላው ቀርቶ በሀገራቸው ለሚወለዱ ልጆቻችን ዜግነትን አይሰጥም ። ያም ሁሉ ሆኖ ከሀገራቸው ዜጋ እኩል ሰርተን እንኖር ዘንድ እድሉን ሰጥተውን በሀገራቸው የኮንትራት ኑሮን በሰላም ግን ዘወትር በስጋት አኑረውናል። ሳውዲዎች በአብዛኛው ቅንና ደጎችም ናቸው፣ በላባችን ሰርተንም ቢሆን አብረናቸው ስንኖር አብዛኞች ከኩራትና ትምክህት ብሎ ነገር የጸዱ ናቸው። ሳውዲዎች በቆዳ ቀለም፣ በዘርና በሐይማኖት ልዩነት ሳያደርጉ በእኩልነት በሀገራቸው አኑረውናል! ሳውዲዎች ለእኛ ለመጤ የውጭ ዜጎች እንደተባለው የተበላባት ሀገር ሆና በረከቷን አልነፈገችንም! ይህ የእስከዛሬው ምስክርነት ነው። … ዳሩ ግን ትናንት ዛሬ አይደለም፣ ሳውዲ ላይ ለአብዛኛው ስደተኛ ነገሮች በፍጥነት ተለዋውጠዋል !
የምሽቱ ብስራት …
============= ዛሬ እኩለ ቀን ተሰራጭቶ ማምሻውን የሰማሁት መረጃ ህይዎቴን የሚቀይር ሆኗል። በእርግጥም ” እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ 746 ታራሚዎችና ተጠርጣሪ ዎች እንዲለቀቁ ተወሰነ” የሚለው የመረጃ ብስራት ታላቅ የደስታ ምክንያቴ መሆኑን መካድ አይቻለኝም። እናም ደስታዬ ወሰን አጥቶ አምሽቷል)
እኔና ስደቱ …
=========
ከ22 ዓመታት የኖርኩበትና እንደ ሁለተኛ ሀገሬ የማያትን ሳውዲ ለእኔ የስደትን ገፈት የቀመስኩበት ናት ብዬ ስደቴን አላካብደውም ። ዳሩ ግን በእኔ ከሆነው መልካም ነገር በከፈ መልኩ በስደቱ የተጎዱ ወገኖቸን መከራ ከጫፍ እስከ ጫፍ ስዘዋዎር አውቀዋለሁ። መከራ ሰቆቀውን ከተገፊ ወገኖቸ አንደበት አድምጨ ፣ በደሉን የተገፊዎች ገለ ተመልክቸ በሚገባ አውቀዋለሁና የአረብ ሀገሩን ስደት ህመሜ ሆኖ ሁለት አስርት አመታትን በመረጃ ቅበለው ገፍቻለሁ ። በባህሪዬ ክፉ ሰው ልሆን እችላለሁ ፣ ብስጩ ፣ ቁጡ ፣ አትንኩኝ ባይነቴን የመልደብቅ ፣ ስሜታዊ … ምናምንቴ ልሆን እችልም ይሆናል ። ከዚህ ሁሉ ግለ ባህሪዬ ውጭ ያለው የእኔና የተገፊ የአረብ ሀገር ስደተኛ ትስስራችን ከግል አመሌ በላይ ክቡር ጉድኝት ነበረን !!! እኔና ተገፊው ስደተኛ በእውነት ላይ የተመሰረተ ፣ ሰብዕናን መሪ ያደረገ የአካልና የመንፈስ ጉድኝት ነበረን ፣ አለንም !
ስደቱ ሊበቃኝ ማምሻውን ከራሴ ጋር ስማማል በወራት ውስጥ የሳውዲን ስደት በቤት ሰራተኝነት ለመለቀል በሽዎች የሚቆጠሩ ሊቀላቀሉ መሆኑን መረጃ በእጀ ገብቷል ። እናም ለኢትዮጵያ እነ ኦቦ ለማን መገርሳን የላከ ፈጣሪ ለስደተኛ ወገኖቸ የእኔ ክፍተት የሚተካ መረጀ አቀባይ ብቻ ሳይሆን ከእኔ የተሻለ ትጉህ ፈጣሪ ይነፍገናል አልልም ! እኔ ስደቱ በቃኝ ብዬ ለመለየትና ለመጀመሪያ ጊዜ ነፍሴ ፈቅዶ እቆርጥ ዘንድ የፈጣሪ ፈቃድ ሆኗል …! እነሆ ስደት ሊበቃኝ ዛሬ ቀኔን አንድ ብዬ መቁጠር እጀምር ዘንድ ፈቃዱ ለሆነው ፈጣሪ ምስጋና ይድረሰው! ሰው ያስባል ፣ ፈጣሪ ይፈጽማል! እዚያ እስክንደርስ ግን መረጃ ቅበላውን እንገፋበታለን !
እናቴ ሆይ ደስ ይበልሽ … ለፈጣሪ ምስጋና ይግባው !
ነቢዩ ሲራክ
የካቲት 2 ቀን 2010 ዓም