የቀውሱ ተጠያቂ በመገንጠል ሲመሽግ !!! /የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር/

የቀውሱ ተጠያቂ በመገንጠል ሲመሽግ !!! /የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር/

የህወሓት/ኢህኣዴግ ቁንጮዎች ለራሳቸው በማይገዙበት ሕገ-መንግስትና የሽብር ዓዋጅ በመሳሰሉ ‘ሕጎች’ ከለላ ህዝቡ ሓሳቡ የሚገልጽበት፥ ተቃውሞ የሚያሰማበትና ዜጋዊ ግዴታው የሚወጣበት መብቱን ለ27 ዓመታት ኣፍነው በመያዝ ስቃይ ሲያበዙበት በቃኝ ብሎ ቆርጦ መነሳቱ ባህሪያዊ ሂደት ነው። መከራና ግፍ መሸከም የበዛበት ህዝብ በቃኝ ብሎ ቢነሳ ታድያ ጥፋቱ የማን ሊሆን ነው? ይህ ገዢ ቡድን ስልጣን ላይ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ህዝብንም ሃብቱንም ቁጥጥሩ ስር ኣድርጎ፥ ሃገሪቱ የምትተዳደርበት ሰንካላ ሕጎችና ፖሊሲዎች በመንደፍና ተግባር ላይ በማዋል የተሰማራ ኣምባገነን ኣካል በመሆኑ ባመረረ ህዝባዊ ማዕበል ተከበዋል። በርግጥ የዚህ ኣምባገነን ኣካል ነጂው ቡድን ደግሞ የህወሓት ኣመራር ለመሆኑ ኣጠያያቂ ስለኣይደል፥ የማዕበል ግፊት በዋናው ተጠያቂ ቡድን ማረፉ ተገቢ ነው።

ይህ የህወሓት ኣመራር በእኩይ ስራዎቹ (ኣፈና፥ ግድያ፥ እስራት፥ ሙስና፥ ህልቀተ-ድርቅ፥ . . .) ምክንያት ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እየተጋጨ መጥቶ-መጥቶ፥ ኣሁን ደርሶ እንደ ማንኛው ኢትዮጵያዊ ሰለባ ባደረገው የትግራይ ህዝብ ጉያ ገብቶ ለመመሸግ የባጡን የቆጡን እያናፈሰ ይገኛል። ቀደም ሲል በሁሉም ጉባኤዎቹ ፈራ-ተባ እያለ፣ በሙስና በስብሰናል፥ ፍትህን ኣኮላሽተናል፥ ኣምባገነንነትን ኣንግሰናል፥ ህዝባችንን ለኣስከፊ ድህነት ዳርገናል፥ ኣጥፍተናል ግን ካሁን ወድያ ኣይለምደንም – ታድሰናልና ታገሱ ሲል እንደነበረ ይታወቃል። ያ’ሁሉ ስብከት ከንቱ ወሬ ብቻ እየሆነ ስለተቃጠለበት፥ ኣሁን ደግሞ ሌላ እኩይ ዘዴ በመሻት ላይ መሆኑ ከሚያካሂዳቸው ቅስቀሳዎች መገንዘብ ችለናል። ይህን ያህል በደል በሃገርና በህዝብ ላይ ያደረሰ ድርጅት፥ እውነት መበደሉን ተሰምቶት ቢሆን ኖሮ ቢያንስ ኣልቻልኩም ብሎ ከስልጣን መውረድ ፥ ኣልያም ለቅጣት ሕግ ፊት መቅረብ ነበረበት እንጂ ጥፋቱን ባዲስ መልክ ለመቀጠል መተራመስ ኣልነበረበትም። በርግጥ ጥፋትን ኣምኖ ከስልጣን መላቀቅ ለኣምባገነኖች እንግዳ ስለሆነ በተግባር ሊታይ ኣይታሰብም። ይልቁንስ የሚያሳዝነው፥ በኣሁኑ ወቅት ሁለት የከሰሩ ግን ኣደገኛ የቅስቀሳ ኣርማዎች ኣንግቦ በስፋት እየተንቀሳቀሰ መገኘቱ ነው።

1ኛው “የትግራይ ህዝብና ህወሓት ኣንድ ኣካል ናቸው” የሚል ሲሆን፥ 2ኛው ደግሞ “ተቃውሞ ከበዛብን እንገነጠላለን” የሚል መፈክር ነው። ሁለቱም መፈክሮች ጭንቀት የፈጠራቸው የደካማነት ምልክቶች እንጂ ጤነኛ ኣእምሮ ያለው ሰው የሚያፈልቃቸው የመፍትሄ ሓሳቦች ሊሆኑ ኣይችሉም። ኣንድ-ባንድ እንያቸው።

በቅድሚያ በማንኛውም ህብረተሰብ የተለያዩ ኣመለካከቶች፥ ዝንባሌዎች፥ እምነቶች፥ ፍላጎቶች፥ ወዘተ እስካሉ ድረስ ሁሉም በኣንድ ድርጅት ይወከላሉ ብሎ ማሰብ የግንዛቤ ጥበት ከመሆኑ ኣልፎ ኣምባገነንነትን ማስተናገድ ነው። ኣብዝሃነት (pluralism) የሚለው ጽንሰ-ሓሳብን ኣለማወቅ ኣልያም እያወቁ ሆን ብሎ ንቆ ማለፍን ያሳያል። ከዚህ እውነታ ስንነሳ ህወሓት በመሰረቱ “የትግራይ ህዝብና ህወሓት ኣንድ ኣካል” ኣድርጎ ማሰቡ ፍጹም ስህተት ነው። ከዚህ ኣልፎ ደግሞ በጠመንጃ ፥ በስለላ፥ በድርጅታዊ መዋቅር (ጥርናፈ)፥ በኣሸባሪ ፕሮፓጋንዳ ተጠፍሮ የተያዘ ህዝብን – በረት ውስጥ እንደታጎረ እንሰሳ ቆጥሮ – የኔ ነው ማለቱ የለየለት ድንቁርና ከመሆኑ ኣልፎ ያ’በረት የተጣሰ እለት የሚከተለውን ጣጣ ኣማትሮ ኣለማየትም ነው። ለነገሩ ኣምባገነኖች ከተሰቀሉበት ጣራ ክፉኛ የሚወድቁት በዚሁ ምክንያት መሆኑ ነው።

እግረ-መንገዳችን ኣንድ የሚገርም ምጸት ለማከል እንወዳለን። በኣንድ በኩል የህወሓት መሪዎች “የትግራይ ህዝብና ህወሓት ኣንድ ኣካል ነው” የሚለው ብሂል ሲያራግቡ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች ያንኑ ብሂል እንዳለ በመድገም “የትግራይ ህዝብና ህወሓት ኣንድ ናቸው” ይሉናል። የሁለቱም መነሻ ከላይ የጠቀስነው፥ ያው ድንክየው ኣመለካከት ቢሆንም፥ የፊተኞቹ ኣንድ ነን የሚሉት ሊጠቅሙት ኣስበውለት ሳይሆን፥ ሆን ብለው እንደ ምሽግ ሊጠቀሙበት ፈልገው ሲሆን፣ የኋለኞቹ ደግሞ “የትግራይ ህዝብና ህወሓት ኣንድ ስለሆኑ ኣብረው መጥፋት ኣለባቸው” ከሚል ደንባራ ኣመለካከት ተነስተው ነው። ምጸት ይሉታል ይህ ነው። ለነገሩ የሁለቱም ህብረተሰብዊ ግንዛቤ ኣንድ በመሆኑ ሁለት ገጽ ባለው ኣንድ ሳንቲም ሊመሰሉ ይቻላሉ።

2ኛው መገንጠልን እንደ ኣማራጭ መፍትሄ ወስዶ መቀስቀሱ ሌላኛው ኋላ-ቀር ብሎም ማለቂያ የሌለው ሰበቡን ካለመገንዘብ የሚነሳ የጨለምተኞች ስግብግባዊ ኣመለካከት ነው። ዓለማቀፋዊነት ሃገሮችን ይሁን ኣህጉሮችን የማዋሀድ ኣቅጣጫ በያዘበት 21ኛው ክፍለ-ዘመን የብሄር ግንጠላ ብሎ ማሰብ፣ ደግሞም ከበሰበሰ ኣገዛዝ ጋር፥ ከኋላ-ቀርነት የወረደ ዝቃጭና ጨለምተኛ ኣስተሳሰብ ነው ቢባል ኣይበዛበትም።

የህወሓት መሪዎች ለዓመታት በዘዴ ሲያራምዱት የነበረው የመገንጠል ሕልማቸው፥ ኣሁን በፈጠሩት ቀውስ ሳቢያ በመሳካት ላይ ያለ ስለመሰላቸው ነባር ኣፈ-ጮሌ ካድሬዎቻቸውን በማሰማራት “ተቃውሞ ከበዛብን መገንጠል ኣለብን” እያሉ መስበክ ጀምረዋል። እነሱ ቤት ሁሌም ፋሲካ ስለሆነ መገንጠል በህዝቡና በሃገሪቱ ቀጣይ እጣ ምን ዓይነት ምስቅልቅል እንደሚያስከትል ኣይታያቸውም። ከየት ተነስተው ወዴትና ማንን ይዘው እንደሚገነጠሉ የሚያውቁትም የሚሉትም ነገር ስለሌለ ህልማቸው ባዶ ቅዠት ከመሆን ኣልፎ ይዞኣቸው እንደሚበንም ከወዲሁ ልናስገነዝባቸው እንወዳለን።

ለመሆኑ መገንጠል እንደ መፍትሄ ማን ነው የሚያቀነቅነው? ለምንስ እንደ መፍትሄ ይነሳል? በንድፈ-ሓሳብ ደረጃ ስናየው ኣፋኝ ስርዓት ስር ከመኖር ይልቅ ስርዓቱ ካንሰራራበት ሃገር ተነጥለን፥ የራሳችን “ነጻ” ስርዓት መስርተን መኖር ይሻላል በማለት የፖለቲካ ልሂቃን/ነጋዴዎች ያነሱታል፣ ህዝቡም መስሎት ሓሳቡን ሊደግፍ ይችላል። የተገነጠሉ ህዝቦች ተመልሰው፥ ያንኑ ዓይነት ኣፋኝ ስርዓት እጅ መውደቃቸው ግን ኣልቀረም። እንደገና ኣፈና ውስጥ የገቡት፥ በተገንጣዩ ክልል ውስጥ የሚገኘው ብሄረሰብ ሁሉ የመገንጠል ጥያቄ ሊያነሱ ነው ማለት ነው። በዚህ ሂደት ማለቂያ የሌለው ግንጠላ ይከተልና መጨረሻው ሃገር-ኣልባ መሆን ነው። የሰከነ ኣእምሮ ያለው ሰው ይህን ኣያስብም።

ድሮውም ችግሩ ኣፋኝ ስርዓት ያሰፈነው እንጂ የመገንጠል ወይም ያለመገንጠል ጉዳይ ስላልነበረ የመገንጠልን ጥያቄ ትርጉም-ኣልባ ሆኖ ይቀራል። ስለዚህ ከኣፈና ለመላቀቅ፥ ኣፋኝ ስርዓቱ ነው መፍረስ ያለበት ወይስ ዘመናት ያስቆጠረው – ትውልድ ተሻጋሪ – የጋራው ሃገር ነው? የሚለው ጥያቄ እንድናነሳ እንገደዳለን። መልሱም ባጭሩ እነዛ መገንጠልን የቀሰቀሱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ለፍትሃዊ ስርዓት መመስረት መታገል እንጂ መገንጠል በራሱ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል ከታሪክም ከኣካባብያችንም መገንዘብ ይቻላል።

ጥንትም ይሁን ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝቦች (ብሄሮች ይባሉ ብሄረሰቦች) ጦረኛ መሪዎቹ ኣስወጥተን ስናያቸው፥ በመካከላቸው ይህ ነው የሚባል ቅራኔ የላቸውም። እንከን ባይጠፋውም፣ በፖለቲካ፥ በኢኮኖሚ፥ በሃይማኖት፥ በባህል፥ በትግል፥ ክሮች የተጠላለፈ የጎላ ረዥም የኣንድነት ታሪክ ግን ኣላቸው። የሁሉም ፍላጎት መብታቸው ተከብሮ፥ ሰርተው ግረው በሰላም መኖር ነው። ለስልጣንና ለብዝበዛ የተሰመሩ ገዢዎች ግን የህዝቡን በጎ ግንኙነትና የነቃ ኣንድነት፥ እላፊ ጥቅማቸውን የሚፈታተን ሆኖ ሲያገኙት፥ ፈተናውን ከህዝቡ ጋር ተመካክሮ እንደማለፍ ኣንዱን ወገን በሌላው ላይ በማነሳሳት የስልጣን ጊዜ ሊገዙ ሲንደፋደፉ ይታያሉ። ኣሁን በመላ ሃገሪቱ ተቀስቅሶ ያለው ቀውስና ግጭት በዚህ ምክንያት ነው። ስለዚህም የዚህ ሁሉ ግጭትና ቀውስ ፈጣሪው የህወሓት ኣመራር እንጂ ኣፈናና ድህነት ያንገፈገፈው ህዝብ ሊሆን ኣይችልም።

በርግጥ የግጭቱና የቀውሱ ባለቤት የህወሓት ገዢ መደብ ሰንካላ ኣመራር ሆኖ እያለ፥ ህወሓት ኣሁን ታሪክ ቢሆንም ድርጅቱ ከመፈጠሩ በፊት ጀምሮ በሃገሪቱ ተሰማርቶ፥ ሰርቶ-ግሮ በሚኖረው የትግራይ ሰው ጥቃት እየደረሰ እንዳለ ይታወቃል። ይህ ብሄር-ተኮር የሆነው ግብታዊ ጥቃት ኣጥብቀን እንቃወመዋለን። የኣፈናው፥ ግድያው፥ እስራቱ፥ ሙስናው፥ ህልቀተ-ድርቁ፥ ተጠያቂው የህወሓት/ኢህኣዴግ ኣመራር እንጂ፥ የነዚሁ እኩይ ተግባሮች ሰለባ የሆነው የትግራይ ህዝብ ሊሆን እንደማይችል ደግመን ደጋግመን ለመግለጽ እንገደዳለን። “መበደልማ ወታደሩ በድለዋል፥ ግን ገበሬ ይካስ” የሚለው ኋላ-ቀር ባላባታዊ ብሂል ካልተጠናወተን በስተቀር፥ የቀውሱም ይሁን ቀውሱን ተከትሎ እየደረሰ ላለው ጥፋት ዋናው ተጠያቂ የህወሓት/ኢህኣዴግ ኣመራር ስለሆነ ጥቃቱ በኣጥቂው ላይ ቢያርፍ የጋራው ትግላችን ውጤታማ ይሆናል ብለን እግረመንገዳችን እንመክራለን።

የተከፋው የትግራይ ህዝብ ደግሞ ኣልተቃወመም፥ ኣልተነሳም ተብሎ ኣይከሰስም። የሚዘግብለት ሚዲያ ኣላገኘም እንጂ፥ ካንዴም ሁለቴም በተምቤን-ዓቢይዓዲ፥ በኣጽቢ-2 ኣውላዕሎ፥ በኣድዋ-ነበለት፥ በዓጋመ-ዓዲግራት፥ በመቐለ-እግሪ ሓሪባ፥ ወዘተ ተቃውሞ በማስነሳቱ ኩፍኛ ተመትቶ በማገገም ላይ ነው የሚገኘው፣ ቁስሉም ኣልሻረም። የኣዲስ ኣበባ ህዝብ ካንዴም ሁለቴም ክፉኛ ተደብድቦ በማገገምና ለማይቀርለት ትግል በማኮብኮብ ላይ እንዳለ ሁሉ ያኛውም በዚሁ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው። ያም ሆኖ ከኣብራኩ የወጡ ልጆቹ በዓረና-ትግራይ፥ በትዴት/TAND፥ በዴምህት፥ እንዲሁም በተወሰኑ ሲቪል ማህበራት ተደራጅተው እየታገሉ ናቸው። ኣፈናው ኣላላውስ ብሎት በተናጠል ሲታገል የቆየው ወጣቱ ደግሞ ስዩም መስፍን “. . . ወዴት እየሄደ እንዳለ ማየት ኣቅቶታል፣ የጥፋት መንገድ እየተጓዘ ነው።” ቢለውም፥ በኣሁኑ ወቅት ተሰባስቦ ለፍትሃዊ ለውጥ መታገል ጀምረዋል። የትግራይ ህዝብና ህወሓት ፍጹም ኣንድ ኣይደሉም! ኣልነበሩም! ሊሆኑም ኣይችሉም። መገንጠል ለጨለመባቸው እንጂ በህዝባችን ዘንድ ተቀባይነት የለውም እያላቸው ነው።

በኢትዮጵያችን ኣምባገነኑ ስርዓት ተወግዶ የጋራ ፍትሓዊ ስርዓት (መንስህ) ሊመሰረት ከተፈለገ፥ ይህ የትግራይ ተቃዋሚዎች ትግል ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሃይላት ትግል ጋር ማቀናጀት የግድ ኣስፈላጊ ነው፣ ምክንያቱም ኣንደኛ ነገር ለ27 ዓመታት ስልጣን ላይ የተቀመጠው ኣምባገነኑ ህወሓት/ኢህኣዴግ እየተፍረከረክ ቢሆንም ዋናው ሃይሉ እንዳለ የለውጡን ሂደት በማደናቀፍ ላይ ነው የሚገኘው፣ ሁለተኛም ካሁን ወድያ በኢትዮጵያ መመስረት ያለበት መንግስታዊ ስርዓተ-ህዝብ (መንስህ) ለሁሉም እንደየእምነቱ በጋራ በሚደነገገው ሕገ-ህዝብ የሚያስተናግድ፥ በሁሉም ተሳትፎና ይሁንታ መምስረት ስላለበት ነው።

ትግሉ በዚህ መልክ እየተጋጋለ ባለበት ወቅት፥ ኣምባገነኑ ህወሓት/ኢህኣዴግ ሁለት ምርጫዎች ኣሉት። ኣንዱ ማስመሰሉን ትቶ፥ የለውጡ ኣጋር መሆን ነው፣ ለዚሁም ፖለቲካ ምህዳሩ በማስፋት ሁሉም ዜጋ እኩል የሚሳተፍበት መድረክ፥ ጸሓይዋ ሳትጠልቅ ማዘጋጀትና ፖለቲካ እስረኞች ያለቅድመ ሁኔት ባስቸኳይ መልቀቅ፥ ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ማሳተፍ፥ ዴሞክራሲን የሚያቀጭጩ ሕጎችን መሰረዝ፥ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚደረግበት ሁኔታ መፍጠር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ እየተጋጋለ ባለው ህዝባዊ ማዕበል ተጠራርጎ መወገድ ነውና ምርጫው ለሚመለከተው እዚህ ላይ እንተወዋለን። ትኩረታችንም የየራሳችን የቤት ሰራ በሰከነ መንገድ ማቀላጠፍ ነው።

ከብዙ ያልተሳካ ውጣ-ውረድ በኋላ፥ ኣሁን በመላ ሃገሪቱ ፍትሓዊ ለውጥን ታሳቢ ያደረገ በጋራ ተሳስቦ የመታገል ተስፋ ሰጪ ኣዝማሚያ እየታየ ነው። ቀደም ሲል መፈንጠቅ የነበረበት ይህ በጎ ኣዝማሚያ ሊበረታታና ጎልብቶ ተፈላጊውን ለውጥ ያስገኝ ዘንድ እያንዳንዱ ለውጡን ፈላጊ ግለሰብ ይሁን ድርጅት የበኩሉን ኣስተዋጽኦ ማከል ይጠበቅበታል። ሃገር የጋራ እንደሆነው ሁሉ ሃገርን የሚመራ ስርዓት ደግሞ የግድ የጋራ መሆን ኣለበትና!
የጋራ ስርዓት መስርቶ በእኩልነት ኣብሮ ለመበልጸግ ብቸኛው መንገዱ ይሀው ነውና፥ በትግሉ መስመር የቀደመውን እየደገፍን፥ ጽንፈኛውን እያረምን፥ ኋላ የቀረውን እያበረታታን በልበ – ሰፊነት ቆርጠን ስንታገል ነው እግባችን የምንደርሰው እንላለን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
ት. ዴ. ት.
ጥቅምት 2018 ዓ/ም/ፈ.

LEAVE A REPLY