ኢ.ቢ.ሲ. በሰበር ያስተናግደውን የኃይለማርያም ደሳለኝ መግለጫ፤ ዞምቢዎቹ ተሯሩጠው ለማጽደቅ ግዜ አልወሰደባቸውም። እሳቸውም ልክ ስልጣን እንደነበረው ጠቅላይ ሚኒስቴር “ስልጣን አስረክቢያለሁ” ሲሉ እፍረት የሚባል ነገር ፊታቸው ላይ አይታይባቸውም ነበር። ሹመት እንጂ ሕገ-መንግስቱ የሚፈቅደው ስልጣን እጃቸው ላይ እንዳልነበር ሕጻናትም ያውቁታል። የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መልቀቅያቸውን በብርሃን ፍጥነት ሲያጸድቀው፤ ድርጊትዋን ከደቡብ አፍሪካው ጃኮብ ዙማ ክስተት ጋር ለማመሳሰል የተተወነች ድራማም አስመስሏታል። ስልጣን ሳይኖር “ሰላማዊ ሽግግር” የሚሏት ፌዝ …
ኃይለማርያም ደሳለኝ ተሸክመውት የነበረው ሹመት ይሁን ስልጣን ሲለቅቁ፤ “ከደሙ ነጻ ነኝ” ብለው ለተሰራው ወንጀል ሁሉ እንደ ጲላጦስ እጁቸውን ሊታጠቡ እንደማይችሉ ግን እርግጥ ነው። ከዚህ ባለፈ ግን የእሳቸው መውረድ በሃገሪቱ ላይ ሊያመጣ የሚችለው ለውጥ ከቅርብም ይሁን ከሩቅ አይታይም። እንደማንኛውም የድል አጥቢያ ካድሬ፤ ቆሻሻውን እና የሸክሙን ስራ ሲሰሩ የሰነበቱ ሰው ነበሩ።
ሰውየው ለጥፋቱ ሁሉ ጠጠያቂ የሚያደርገው ሃላፊነት ቦታ ላይ ይቀመጡ እንጂ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ እሳቸው መሳለቅያ የሆን መሪ አልነበረም። ተጠያቂነቱ እንዳለ ሆኖ ግና የራሳቸው ራዕይ እና አንዲት ቀን እንኳ የራሳቸው አቋም ያልነበራቸው አሸንጉሊት ነበሩ። “የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ይለቀቃሉ!” ብለው በገዛ ገጻቸው የጻፏት መግለጫ እንኳን በዞምቢዎቹ ስምንት ግዜ ተሰርዛ – ስምንት ግዜ ተደልዛለች። ኃይለማርያም በዚህ ደረጃ ለመዋረድ ራሳቸውን ስላዘጋጁ፤ ይህ ድርጊት ለሳቸው አዲስ ነገር አይደለም። “መረጃ አይሰጡኝም። ስራዬን የማከናውነው ያለመረጃ ነው።” እያሉ አንዳንዴ ጣል የሚያደርጓቸው እውነታዎች “ጉድ ነው” ቢያስብሉም፤ አጃኢብ የሚያሰኙ ንግግሮችንም በአደባባይ ይለቅቃሉ። ኢትዮጵያ፤ አንድ በመንገደኛ ፌደራል ፖሊስን በጥፊ የሚመታበት ሃገር እንደሆነች በቴሌቭዥን ቀርበው የሚናገሩ ሰው ናቸው። ለንግድ የሚነሳ ማንም ሰው ሰፌድ ብቻ ይዞ ትግራይ እና ደቡብ በመሄድ ወርቅ ማፈስ እንደሚችልም በብሄራዊ ቴሌቭዥን ተናግረዋል። “ኮብልስቶን” ድንጋይ ማንጠፍ እጅግ የሚያዋጣ ስራ እንደሆነ ለዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ሲመክሩም ተደምጠዋል።
ስልጣን የለቀቁበት ምክንያት ግን ግራ ሳያጋባ አልቀረም። “ሃገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው። ከፍተኛ የሆነ ያለመረጋጋት እና ችግር አለ። በርካታ ህይወት ጠፍቷል። በርካታ ሰዎች ተፈናቅለዋል… ” ብለውናል ኃይሌ። ችግሩ ይህ ሆኖ ሳለ ለችግሩ መፍትሄ ለመሆን እንዲያስችላቸው እሳቸው መውረድ እንዳለባቸው ነው የገለጹት። ከፍተኛው የመንግስት ስልጣን ላይ እያሉ ያልፈቱትን ችግር – ከዚያ በመውረድ የሚፈቱበትን ፎርሙላም በመግለጫቸው ጀባ ቢሉ ጥሩ ነበር። ሕዝቡ ለሚያነሳቸው በርካታ ጥያቄዎች የጥይት ምላሽ ሲሰጡ እንዳልነበረ። ሕዝብ ላይ ሲተኩሱ ለነበሩ ወታደሮች ማዕረግ ሲያንበሻብሹ እንዳልነበር – ይህንን ደፍረው ተናገሩ። ሹመቱ ወር እንኳ መች ሞላው?
ከምህንድስና ሰራቸው አንስቶ የተዋጣለት ካድሬ ያደረጋቸውው የስልጣን ፍቅር ይሁን የበታችነት ስሜት – ብቻ አሁን ላይ ደርሰው በራስ መተማመንን ሳይቀር እንዳሳጣቸው ከንግግራቸው መገንዘብ አይከብድም። እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆን ይልቁንም እንደ ተላላኪ ሆነው ለማገልገል ሙሉ ፈቃዳቸውን ባይሰጡ እነሱም እንደ ጅሉ ሞሮ አይቀልዱባቸውም ነበር። ከተራው ሕዝብ ርቀው ጫፍ ላይ በመቀመጥ ሀገራዊ መርዶ ሲጋቱ ከከረሙ በኋላ ማልቀስ እና ማላዘን ምንም ትርጉም አይሰጥም።
በቅርቡ አሜሪካ የገባው የሳቸው ፕሮቶኮል ኃይሌ በግዞት ውስጥ ያሉ እስረኛ እንደሆኑ ቢናገርም እሳቸው ግን አንዲት ቃል እንኳ አልተነፈሱም ነበር። እንዲያውም በቅርቡ ሰጥጠውት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ የሃገሪቱ እድገት “የሚያስጎመጅ” በመሆኑ ሁሉም እንደሚመኙት በመናገር ትንሽ ፈገግ አድርገውናል። ይህንን ፈገግታችንን ሳንጨርስ ትላንት በ ኢ.ቢ.ሲ. ቀርበው ኢትዮጵያ በገባችበት አስከፊ ችግር ሳብያ ኢንቨስተሮች ሳይቀሩ ሃገሪቷን እየለቀቁ እንደወጡ አፈረጡት።
“በደርግ ዘመን ማሰቃያ የነበረው ማእከላዊ እንዲዘጋ እና ሙዚየም እንዲሆን” መወሰኑን ቢነግሩንም ይህንን ሚዚየም ሳያስመርቁ መሰናበታቸው ግን ቅር ያሰኛል። ይህንን መናገራቸው ባልከፋ ነበር ግና ጽድቁ ቀርቶ እንዲሉ መንግስት የጀመራቸውን እቅዶች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለባቸው በስንብታቸውም ሳይጠቅሱ አላለፉም። የእስካሁኞቹ የመንግስት እቅዶችም ያየናቸው ናቸው። መብቱን ያወቀ እና መብቱን የጠየቀ ዜጋን ማሰር – ማፈናቀል – መግደል…. ናቸው።
ባለ ሙሉ ስልጣን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ ምህላ ሲያደርጉ፤ “እዚህ ያለሁት የመለስን ራዕይ ለማስፈጸም ነው።” ብለው ነበር። ያን ለማድረግ ደግሞ የበላዮቼ እና የበታቾቼ የሚያዙኝን ሁሉ አደርጋለሁ ሲሉ ቃል መግባታቸው ይታወሳል። የበላዮቼ ያሉት ምክትል ሆነው የተሾሙ እነ ደብረ ጽዮንን መሆናቸው ነው። አድፍጠው ይህችን ወቅት ይጠብቁ የነበሩ እነ አቦይ ስብሃት ዛሬ አደባባይ ወጥተው፣ “የመለስ ራዕይ የሚባል ነገር የለም” ማለት ሲጀምሩ “ታላቁ መሪ” ን የተኩት “ታዛዡ መሪ” አይናቸው ፈጠጠ። መለስ የጀመረውን ለመጨረስ ቢፍጨረጨሩም ዳር አላደረሱትም። የመልሰ “ዜጎችን በዘር ከፋፍሎ 100 አመት የመግዛት” ስትራቴጂ በነቄው ትውልድ ሲከሽፍ – እጅ መስጠት ግድ ይላል። እኚህ ሰው ነጸ አልነበሩም። ነጻ ሆነው ሲናገሩ የምንሰማቸው ጠቃዋሚ ሃይሎችን እና ጋዜጠኞችን ሲሳደቡ ብቻ ነው።
ዛሬ ኳሷ ሕዝብ እጅ ላይ ስትወድቅ እሳቸውም ም ባነኑ። ከመለስ ወርሰው የተሸከሙት ነገር ራዕይ ሳይሆን – ቅዠት እንደሆነ የተረዱት በዚህ ሰዓት ይመስላል። ይህንን እስኪረዱት ግን ሕዝብ ማለቅ ነበረበት። መለስ የጀመረው ለእልቂት የተጠነሰሰ የፌዝ ፌደራሊዝም እጨርሳለሁ እንዳሉት ከግብ ባያደርሱትም፣ ብዙ ገፍተውታል።
የፖለቲካ አክሮባቱን ተስተምረው – የሃይል ሚዛን እያዩ የመገለባባጥ አባዜ ከልሆነ በስተቀር ሃገሪቱ 27 አመት ሙሉ ችግር ላይ ናት። የሕዝብ ድምጽ ሲዘረፍ አብረው ዘርፈዋል፤ መቶ ሺህ የኦሮሞ ወገናችን ከሃረር ሲፈናቀል አብረው ነበሩ። ኮንሶ ላይ ወገኖች እንደ ባርያ አሳዳሪ በሰንሰለት ሲጠፈሩ አልሰማሁም አይሉንም። ጉራ ፈርዳ ላይ በአማራ ወገናችን የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸምበት አንዲት ነገር አልተነፈሱም። እሬቻ ለበዓል የወጣ ከሺህ በላይ ሰው ሲያልቅ ሰራዊታችን አንድም ጥይት አልተኮሰም ነበር ያሉት። የጎንደር እና የባህርዳር ወጣቶች እንደቅጠል ያረግፍ የነበረው እሳቸው የሚተዳደረው ሰራዊት ነበር። በወልድያ እና በቆቦ ግድያን ሲቃወሙት አልሰማንም። መግለጫቸውን እያነበቡ በነበሩበት ቅጽበት እንኳን በ እሳቸው ጠቅላይ አዛዥነት የሚመራው ሰራዊት ሶስት ሰዎችን ገድሏል።
ልብ ያለው ሰው ሁሉ ወቅቱ የሚናገረውን ድምጽ ያደምጣል። የ”ታህሳሱ ግርግር” ለሃይለስላሴ መንግስት ምልክትን አሳይቶ ነበር። እሳቸው ግን አይተው እንዳላዩ አለፉት። የህዝብን ቁጣ በንቀት ከማለፍ ይልቅ በአግባቡ ቢያስተናግዱት ኖሮ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ከመዋረድ ይድኑ ነበር። ደርግም ቢሆን የሕዝብ ጥያቄን በጥይት ለመፍታት ሲጥር የተሞከረበትን መፈንቅለ መንግስ በ “ጥቂት ጀነራሎች” ስም ከሚያጣጥለው ይልቅ ብሄራዊ እርቅ ቢያደርግ ኖሮ የሃገሪቱ ችግር መፍትሄ ያገኝ ነበር።
ዛሬም የመውረድ ወይንም የመዋረድ ደወል እያቃጨለ ነው። ገዢው ፓርቲ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ፈትቶ፤ ከእውነተኛ ተቃዋሚዎች ጋር ወደ ብሄራዊ እርቅ መጓዝ ሲችል ችግሩን ይፈታዋል። በአንድ ነገር እርግጠኛ እንሁን። ሕዝብን በጠመንጃ ያሸነፈ ሃይል በታሪክ ኖሮ አያውቅም።
ብሄራዊ ቀውስ – ችግር ብቻ አይደለም። ቀውስ እድልም ነው። ወያኔ ይህንን እድል ለእውነተኛ ብሄራዊ መግባባት ቢጠቀምባት ለራሱም ይበጀዋል። ይህ ዕድል ካመለጠው ግን ተዋርዶ ፤ ይወርዳል።