ህገ መንግስቱን የጣሰ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ እና አንደምታው! /በዳዊት ከበደ ወየሳ/

ህገ መንግስቱን የጣሰ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ እና አንደምታው! /በዳዊት ከበደ ወየሳ/

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አለመረጋጋት ተከትሎ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ታውጇል። ይህ ማለት “አገሪቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በወታደራዊ የደርግ አስተዳደር ስር ወድቃለች” ማለት ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ፤ አዋጁ ህጋዊውን መስመር የተከተለ መሆን አለመሆኑን በቅድሚያ እንመልከት።

አሁን ባለው የኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሰረት፤ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የሚደረገው፤ “የውጭ ወራሪ ሲያጋጥ፣ ህገ መንግስቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰት፤ የበሽታ እና የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት ነው።” አሁን የተሰጠው ሰበብ “ህገ መንግስቱ አደጋ ላይ ወድቋል።” የሚል ነው።”

በ’እርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ አገሪቱን በወታደር ደርጋዊ ስርአት ውስጥ እንድትገባ የሚያስገድድ ነው ወይ?” የሚለውን ጥያቄ ለህሊና ፍርድ በመተው፤ ሂደቱ በራሱ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን የተከተለ አለመሆኑን በማስረጃአብረን እንመልከት።

1ኛ- የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የሚደነገገው በሚንስትሮች ምክር ቤት ነው። ይህ የተባለው አስቸኳይ ግዜ አዋጅ፤ በሚንስትሮች ምክር ቤት አማካኝነት የታወጀ ቢሆንም… በህገ መንግስቱ አንቀጽ 74 መሰረት፤ የሚንስትሮች ምክር ቤትን የሚሰበስበው ጠቅላይ ሚንስትሩ ነው። ውሳኔውን መስጠት ያለበት በጠቅላይ ምንትሩ አማካኝነው ይሆናል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ጠቅላይ ሚንስትር የለም። የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ያለ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሰብሳቢነት አዋጅ ሊያወጣ አይችልም። አሁን የሚንስትሮች ምክር ቤት በማን ሰብሳቢነት አዋጁን እንዳወጣ ግልጽ አለመሆን ብቻ ሳይሆን፤ ስርአቱን የተከተለ አለመሆኑን ልብ ይሏል።

2ኛ- የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሲታወጅ፤ በስራ ላይ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት በ48 ሰአት ውስጥ ሊያጸድቀው ይገባል። ምክር ቤቱ አሁን በስራ ላይ ቢሆንም፤ አዋጁን እንዲያጸድቅ አልተደረገም። በህጉ መሰረት የሚንስትሮች ምክር ቤት ተጠሪነታቸው ለተወካይ ምክር ቤቱ ነው። በህገ መንግስቱ አንቀጽ93/2/ሀ መሰረት” የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ለፓርላማው አቅርቦ በ2/3ኛ ድምጽ መጽደቅ ይኖርበታል፤ ካልሆነ ግን ወዲያውኑ ይሻራል።” ይላል ህገ መንግስቱ። አሁን እንደሚታየው ግን… ይህ አልተደረገም። ስለዚህ ይህ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የህገ መንግስቱን አንቀጽ 93/2/ሀ ሳይከተል የታወጀ ነው።

ከላይ የተገለጹት ሁለት አብይ ምክንያቶች እንዳሉ ሆነው፤ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ለምን ያህል እንደሚቆይ፤ በማን ኮማንድ ፖስት ስር እንደሚሆን አልተገለጸም። ይህ ብቻ ሳይሆን…የሚንትሮች ምክር ቤት በጠቅላይ ሚንስትሩ አማካኝነት አልተሰበሰበም፤ አዋጁም በተወካዮች ምክር ቤት አልጸደቀም።

በአጠቃላይ የሚንስትሮች ምክር ቤት ተጠሪነቱም ለተወካዮች ምክር ቤት ሆኖ ሳለ፤ አዋጁን በምክር ቤቱ ሳያስጸድቅ ከህግ ውጪ… ህዝብ የሚገደልበትን ወታደራዊ አዋጅ ይፋ አድርጓል። የሚገርመው ደግሞ… በሰላማዊ መንገድ ድምጹን የሚያሰማውን ህዝብ… “ህገ መንግስቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ” በማለት ፈርጀው፤ እራሳቸው ግን ህገ መንግስቱን አደጋ ላይ የሚጥል ህገ ወጥ ተግባር መፈጸማቸው ተጠያቂ ያደርጋቸዋል። ይህ አዋጅ ህገ ወጥ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ ከዚህ በኋላ በዚህ ወታደራዊ አስተዳደር ደርጋዊ ስርአት ለሚጠፋው ንብረት እና ህይወት፤ እያንዳንዱ የሚንስትሮች ምክር ቤት አባላት ተጠያቂዎች ሊሆኑ እንደሚገባ ዜጎች ልብ ሊሉት ይገባል።

ይህ አዋጅ ህገ መንግስቱን ያልተከተለ በመሆኑ የክልል አስተዳደሮች፤ የአማራ፣ የደቡብ፣ የኦሮሚያ እና ሌሎች ክልሎች ሊቀበሉት አይገባም። እያንዳንዱ ክልል የራሱን ምክር ቤት በመሰብሰብ በዚህ አዋጅ ላይ መነጋገር እና መምከር አለበት። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ህገ ወጥ የሆነውን አዋጅ ተከትለው ወደየክክሉ የሚገቡ የሰራዊቱ አባላት ለሚያጠፉት ህይወት፤ ወደፊት የየክልሉ አስተዳደሮች ጭምር ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ መዘንጋት የለባቸውም።

እራሳቸው… ህገ መንግስቱን እናከብራለን ወይም እናስከብራለን የሚሉት የሰራዊት አባላት እና ኢህአዴጎች ጭምር ይህን ጉዳይ ሊያውቁት ይገባል። ማወቅ ብቻም ሳይሆን ከዚህ በኋላ በህገ ወጥ መንገድ የሚጠፋው የሰው ልጅ ህይወት ትልቅ ዋጋ የሚያስከፍላቸው ይሆናል። ይህ ብቻ አይደለም። ነገ እና ከነገ ወዲያ… በዚህ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ምክንያት ብዙዎች ሊገደሉ እና ሊታሰሩ ይችላሉ። ህዝቡም የሞቱትን ለመቅበር የታሰሩትን ለማስፈታት ትኩረቱን ወደ አንድ አቅጣጫ ያደርጋል። በዚህ መሃል የዚህ ህገ ወጥ እና የራሱን ህገ መንግስት እንኳን ያላከበረ አዋጅ ለአንድ አፍታም ቢሆን ሊዘነጋን አይገባም።

በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት የሚንስትሮች ምክር ቤት ያወጣው መግለጫ የራሱን ህግ የጣሰ፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አገሪቱን ወደ ወታደራዊ አስተዳደር ገፍትሮ የሚያስገባ ነው። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ አገሪቱ በጠመንጃ መመራቷን ትቀጥላለች። በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሳይሆን በጠመንጃ ስልጣን የሚይዝን አካል ደግሞ የተባበሩት መንግስታት እንደድሮው አይቀበልም። ሁኔታውን በትኩረት እና በርቀት ካየነው ታዲያ… የተባበሩት መንግስታት በጠመንጃ አስገዳጅነት ስልጣን የሚይዝን አካል ማውገዝ ብቻ ሳይሆን እንደአገር የማይቀበልበትን አዲስ ህግ ስላለው፤ አገሪቱ በወታደራዊ አስተዳደር የምትመራ ከሆነ ኢትዮጵያ የምትባለዋ አገር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባልነት ጭምር መቀጠሏ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ይህም በኛ ዘመን ኢትዮጵያ በአለም ፊት እንድትዋረድ፤ ባንዲራዋም እንዲወርድ የሚያስደርግ አላስፈላጊ ዋጋ ያስከፍላል። ከዚሁ ጋር አያይዘን የሳንቲሙን ሌላ ገጽታ ካየነው ደግሞ ለአፍሪቃ ምሳሌ የሆነችው አገር… በመጥፎ ምሳሌነት ትጠቀሳለች። በሂደትም የአፍሪቃ አንድነት መቀመጫነቷን ልታጣ ያስችላታል።

ይህ በመጨረሻው አንቀጽ ላይ የተገለጸውን መላ ምት እንደዋዛ መመልከት አይገባም። ዛሬ አገሪቱ ወደ ብሔራዊ እርቅ በመሄጃዋ ሰአት ህገ ወጥ አስቸኳይ አዋጅ አውጆ፤ የህዝብን ደም ለማፍሰስ መቻኮል፤ አገርን አስተዳድራለሁ ከሚል አካል የሚጠበቅ አይደለም። አሁን የታወጀው ህገ ወጥ አዋጅም… የኢህአዴግን አምባገነናዊነት የሚመሰክር፤ አገሪቱን ወደባሰ አዘቅት ውስጥየሚጨምር ነው። በመሆኑም… ልብ ያለው ልብ ይበል!

LEAVE A REPLY