/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፦ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ኢህአዴግ ያወጀውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው አለ።
በኤምባሲው ዛሬ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ኢህአዴግ ያወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፍፁም እንደማይቀበለው አስታወቀ።
አዋጁ መሰብሰብና ሀሳብን መግለፅን ጨምሮ በመሠረታዊ መብቶች ላይ ክልከላ የጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመደንገግ የኢትዮጵያ መንግስት ባሳለፈውን ውሳኔ እንደማይቀበለው ኤምባሲው አስታውቋል። በኢትዮጵያ የሰው ህይወት የጠፋባቸው አጋጣሚዎችንና ሁከቶች መኖራቸውን የምንጋራ ቢሆንም ነጻነትን በመንፈግ ግን ለውጥ ሊመጣ እንደማይችል በአፅንዖት እናምናለን ሲል የኢምባሲው መግለጫ ያትታል።
ዴሞክራሲያዊ ማሻሻያዎችን በማድረግ በኩልም ይሁን የምጣኔ ኃብት እድገትን በማስመዝገብ ወይም ዘላቂ መረጋጋትን በማስገኘት መስክ ኢትዮጵያ ያሉባትን ፈተናዎች በተሻለ ሁኔታ ልትወጣቸው የምትችለው ክልከላዎችን በመደንገግ ሳይሆን አሳታፊ በሆኑ ውይይቶችና በፖለቲካዊ ለውጦች ነውም ብሏል።
በመሆኑም “መንግስት” ለአስተማማኝ ለውጥ ውይይቶችንና የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት እንዳለበት አስገንዝቧል። “ለህዝቡ ጥያቄም ዝቅም ከፍም የማይል ምላሽ እንደሚያስፈልገው ኤምባሲው ጨምሮ ገልጿል።