የካቲት 2010
ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በፈቃዱ ከባለሥልጣንነት ተሰናበተ፤ ብዙ ሰዎች አስተ አስተያየታቸውን በቴሌቪዥን ሲገልጹ እንደሰማሁት ከጠቅላይ ሚኒስትርነት በፈቃዱ ለመሰናበት ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ ነው ይላሉ፤ ይህ የማስታወስ ችሎታችንን ዝቅተኛነትን ያመለክታል፤ ጸሐፌ ትእዘዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድን ረስተናል! (ስለዚህ ጉዳይ በእንዘጭ! እምቦጭ! የኢትዮጵያ ጉዞ ላይ ዘርዘር አድርጌ ገልጫለሁና ወደዚያ አልገባም፤)፡፡
ኃይለ ማርያም የለቀቀው በእርግጥ በፈቃዱ ነው ወይስ ተገፍቶ ነው የሚለውን ጥያቄ አሁን ለመመለስ አይቻልም፤ ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስንብት ከዛሬው የኢትዮጵያ ከባድ ችግር ጋር፣ ከለማ መገርሳና ከዓቢይ አስተሳሰብ ጋር፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ንቃት ጋር ምን ዓይነት ገመድ እንደሚያያይዛቸው ወደፊት ጊዜ ይገልጥልናል፤ በኃይለ ማርያም ስንብት ማግስት የተተኮሰው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርቅንና ሰላምን መመኘትን አያመለክትም፤ በአንጻሩ ብዙ እስረኞች መፈታታቸው ለሰላምና ለእርቅ የሚጋብዝ ይመስላል፤ ማታለል ካልሆነ!
የሆነ ሆኖ ለሃያ ሰባት ዓመታት ሙሉ መተማመን እየጠፋ ጥላቻ እየከፋ፣ የባለሥልጣኖች ንቅዘት እየተስፋፋ በመሄዱና የደሀው ሕዝብ መራቆት አዲስ ያልተጠበቀ አደጋን አንጠልጥሎ መጣ፤ ለሦስት ሺህ ዓመታት የቆየውን ባህላዊ ትስስር ሰባብሮ የጎሣ አገዛዝና የጎሣ መለዮ የተጫነበት ሕዝብ አኮረፈ፣ ተነጫነጨ፣ ተቆጣ፤ ያገኘው መልስ መታሰር፣ መደብደብ፣ መገደል ብቻ ሆነ፡፡
በታኅሣሥ 2013 ትዝብት በሚል ጋዜጣ ላይ የወጣ የጊዜውን ሁኔታ የሚገልጽ ዘገባ ነበር፤ ርእሱ የዛሬው ሁኔታ የት ያደርሰናል የሚል ነበር ቀደም ብዬ ከዚያ በፊት ጊዜው ሳይደርስ ገና በ2009 ዓ.ም. የክህደት ቁለቁለት በሚል ርእስ አንድ መጽሐፍ አበርክቼ ነበር፤ ቀጥዬም በ2010 ዓ.ም. እንዘጭ! –እምቦጭ! የኢትዮጵያ ጉዞ በሚል ርእስ ሌላ መጽሕፍ አሳተምሁ፤ እነዚህ መጻሕፍትና ሌሎችም ጽሑፎች የአገዛዙንም ሆነ የሕዝቡን ችግር ፈልፍለው የሚያሳዩ መስሎኝ ነበር፤ነገር ግን አሁንም አዝማሚያችን ባህል ያደረግነውን አንዱ ጉልበተኛ በሌላ ጉልበተኛ ሲመታ፣ ሕግ በጉልበተኛነት ተሸንፎ ሕዝብን በጣም የሚያስጨቅ ሁኔታ ሲሰፍን ነው፤ በ1983 ዓ.ም. የተወጠነው የአገር አገዛዝ ዓላማና አቅጣጫ የሕዝብን ስሜት ያላካተተ ነበር፤ ገዢዎቻችን በዚያን ጊዜ በድንቁርና የፈጠሩትን ችግር ዛሬ በግዳቸው ተጋፍጠውታል::
በ1983 የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደልማዱ የተነቀለውን በደስታና በእልልታ ሸኘና ጉልበተኞች የተከሉትን በደስታና በእልልታ ተቀበለ፤ ወዲያው ማልቀስ ጀመረ፤ ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ አለቀሰ፤ ተፈናቀለ፤ ተጎሳቆለ፤ ተባረረ፤ ተደናበረ፤ ደኸየ፤ ተራቆተ፤ እንባውን አሟጠጠ፤አግዜርን ተለማመጠ፡፡
እግዚአብሔር በጥበቡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንቂ አጋር የሚሆኑትን ላከለት፤ ኮሎኔል ደመቀ፣ ፍቅሬ ቶሎሳ፣ ሰሎሞን ዴሬሳ፣ ከዚያም ለማ መገርሳ፣ ዓቢይ (ዶር)፣ ሬሳ የመሰለው የኢትዮጵያ ሕዝብ አጋር ሲያገኝ ተንቀሳቀሰ፣ ትንፋሽ ተነፈሰ፣ ያለነው እዚህ ላይ ነው፡፡
የጻእረ ሞት እንቅስቃሴና የንቃት እንቅስቃሴ ሊመሳሰሉ ይችላሉ፤ ግን ሁለቱን ማሳሳት (ንቃትን እንደጻእረ ሞት ወይም ጻእረ ሞትን እንደንቃት መቀበል) በጣም አደገኛ ነው፤ ንቃት የሕያውነት ብሥራት ነው፤ ጻእረ ሞት የሞት ብሥራት ነው፤ ኢትዮጵያ ዛሬ በሁለት ብሥራቶች መሀከል ነች፤ መግደል የሞት አጋፋሪ ነው፤ መግደል የሕይወት ጸር ነው፤ ንቃት የአዲስ ሕይወት፣ የነጻነት ክህሎት፣ የሀሳቦች ፍጭት፣ የልማትና የእድገት ውደድር፣ የዜግነት ኅብረት መሠረት ነው፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበት መንታ መንገድ አንዱ ጻእረ ሞትን ያሳያል፤ ሌላው ሕይወትን ያሳያል፣ በምርጫችን እንሞታለን፤ ወይም በምርጫችን እንለመልማለን፡፡
ኃይለ ማርያም ደሳለኝም የመፍትሔው አካል ለመሆን መንፈሳዊ ምኞት አድሮበታል፤ የኃይለ ማርያም ከሥልጣን መሰናበት ችግርም አለው፤ የመፍትሔው አካል መሆን ችግሩን ሊያደነድነው ይችላል፤ ችግሩ ሲደነድን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ይወልዳል!
ግራም ነፈሰ ቀኝ የኢትዮጵያ የፖሊቲካ ኳስ በፈረንጆች የአነጋገር ፈሊጥ ለመጠቀም አሁን ያለችው በወያኔ እግር ስር ነች፤ አሁን ትልቁ ችግር ወያኔ ኳስ መጫወት የማይችል መሆኑ ነው፤ ኳስ ጨዋታ ሕጎችና ዳኞች አሉበትና፤ የሚቀጥሉት ቀኖችና ወሮች ከምንጊዜም የበለጠ ሕጎችና ዳኞች ያስፈልጋሉ፤ ሌላውን አዲሱን የፋና ቴሌቪዥን ፈሊጥ በመከተል በቅርቡ እናየዋለን፡፡
አልአዛርን ከመቃብር ያወጣ አምላከ፣ ዳዊት ጎልያድን እንዲያሸንፍ ያደረገ አምላክ ኢትዮጵያን ለዳግማዊ ትንሣኤ ያበቃታል ብዬ አምናለሁ፡፡