/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፦ በወልቃይት የማንነት ጥያቄ ምክንያት ከሐምሌ 6/2008ዓ.ም ጀምሮ በእስር ቤት ያሳለፉት ኮሎኔል ደመቀ በጎንደር ከሚገኘው አንገርብ እስር ቤት ዛሬ ከሰዓት በሗላ ተፈተዋል።
ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ከእስር ቤት ሲወጡም ከፍተኛ ህዝባዊ አቀባበል እንደተደረገላቸው ታውቋል። ኮሎኔሉን ሊቀበል በወጣው ህዝብ ላይ የመከላከያ አባለት ከፍተኛ ግርግር የፈጠሩ ቢሆንም የደረሰ ጉዳት እንደሌለም ተገልጿል።
ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ከእስር ቤት እንደወጡትም ለአማራ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት አስተያየት ፈጣራቸውንና ለእርሳቸው ሲል እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ ለከፈለላቸው ህዝብ ከፍተኛ መስጋና አቅርበዋል።
የአማራ ክልል መንግስት ከእስር እንዲፈቱ ከፍተኛ ጥረት በማድረጉ እንዲሁም በእስር ቤት በቆዩበት ወቅት የማረሚያ ቤቱና የአካባቢው የፀጥታ ሀይሎች የሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበር ላደረጉት ከፍተኛ ጥረትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ከ20 ወራትን በእስር ቤት አሳልፈዋል።
አክቲቪስት ንግስት ይርጋን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙት ሌሎች የወልቃይት የማንነት ጥያቄ አስተባባሪዎችም ከትናንት በስቲያ ክሳቸው እንደተቋረጠ የተነገረ በመሆኑ በያዝነው ሳምንት እንደሚለቀቁ ይጠበቃል።