በኢትዮጵያ ሁሉን አሳታፊ የፖለቲካ ውይይት እንዲደረግ የአውሮፓ ህብረት ጠየቀ

በኢትዮጵያ ሁሉን አሳታፊ የፖለቲካ ውይይት እንዲደረግ የአውሮፓ ህብረት ጠየቀ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፦ በኢትዮጵያ ሁሉን አሳታፊ የፖለቲካ ውይይት እንዲደረግ የአውሮፓ ህብረት ጠየቀ።በህብረቱ ቃል አቀባይ ካትሪን ሬይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ ለተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ ብቸኛው መፍትሄ ሁሉንም ወገኖች ያካተተ ሀገር ዓቀፍ ውይይት ማድረግ ብቻ እንደሆነ በአፅንዖት ተናግረዋል።

ቃል አቀባዋ በኢትዮጵያ ስልጣን ላይ ያለው ስርዓት ከተቃዋሚ ሀይሎች፣ሲቪል ማህበረሰብ፣ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ ውይይት በማድረግ ችግሩን ለመፍታትና መረጋጋት ለማምጣት ሁነኛ መፍትሄ ነው ብሎ ህብረቱ እንደሚያምን አስታውቀዋል።

የአቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን መልቀቅ ሌላ ችግር ይዞ እንዳይመጣ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትና የሚመጣው የመንግስት አስተዳድር ሙሉ አቅም ያለው፣ ለህዝብ ቅሬታዎች መፍትሄ የሚሰጥና አዎንታዊ እርምጃዎችን መውሰድ የሚች መሆን እንዳለበትም አስገንዝቧል::

ለሁለተኛ ጊዜ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የዜጎችን ህገ-መንግስታዊ መብት የሚጥስ ከመሆኑም በላይ ለሚደረግ ሽግግር ትልቅ እቅፋት እንደሚሆን ህብረቱ በመግለጫ አስታውቋል።

የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ ገዥው ቡድን ላለፉት 27 ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እርዳታና ብድር በመስጠት ለስርዓቱ የጀርባ አጥንት ሆኖ የቆየ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በኢትዮጵያ የሚፈጸመውን የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶችን በጥብቅ እያወገዘ ይገኛል።

LEAVE A REPLY