ኢትዮጵያ መካን አይደለችም /አንተነህ መርዕድ/

ኢትዮጵያ መካን አይደለችም /አንተነህ መርዕድ/

ፈብሯሪ 2018

አባቶቻችን ለውጭ ወራሪ ሳያስደፍሩ ያቆዩአት ኢትዮጵያ ለብዙ የአፍሪካ አገሮች ነፃ መውጣት ተምሳሌት የሆነችውን ያህል ዛሬ ከኋላዋ የተነሱት ሁሉ በብልፅግናና በስልጣኔ ቀድመዋት በጨለማ ውስጥ ትገኛለች። ትናንትም ሆነ ዛሬ አገሪቱ ካለችበት አስከፊ ሁኔታ ለማውጣት አያሌ ልጆቿ መስዋዕት ከፍለዋል። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ረግጦ የያዛት ዘረኛና ዘራፊ ቡድን ያሳየውን ያህል ጭካኔና አገር አጥፊ እርምጃ በረጂም ታሪኳ አላጋጠማትም።

ትናንትም ለነፃነት መታገሉን ያላቆመው ህዝቧ ዛሬ በተለይም ወጣቱ የግፍ አገዛዝ እንዲያከትም ከዳር ዳር ተጠራርቶ ተነስቷል። ህፃናት ያለአሳዳጊ፣ ወጣቶች ያለነገ ተስፋ፣ አዛውንቱ ደግሞ ያለጧሪ የሚኖሩባት የሰቆቃ አገር መሆኗ እንዲያበቃ የሞት የሽረት ትግል በመካሄድ ላይ ነው። ይህንን ብሩህ ተስፋ እውን ለማድረግ ድምፃቸውን ስለአሰሙ ብቻ በጠራራ ፀሃይ በአጋዚ ጥይት ግንባር ግንባራቸውን እየተመቱ የወደቁት ህፃናት፣ ጎልማሶችና አዛውንት ደም ከንቱ የሚቀር አልሆነም። ህዝቡ ፍርሃትን አሸንፎ ወጥቷልና።

የዘረኞች ክንድ እየላመ፣ ቀናቸውም እየጨለመ በመሄዱ የሚያደርጉትንና የሚራመዱትን መንገድ እያስተዋሉ ሳይሆን የበለጠ ወደመጥፊያቸው እየተንደረደሩ ነው። አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ለአገልጋይነት ውስጣቸው ተሰልፈው የነበሩ ጮሌዎችም የተሳፈሩበት መርከብ ከመስጠሙ በፊት ለማምለጥ እንደሚጣድፉ አይጦች መውጫ እየፈለጉ ነው። እዚህ ላይ እውነተኛ ለውጥ እንዲመጣ የሚታትሩትን ሳንዘነጋ ይሁን።

ከዚህ ዘረኛና አስከፊ ስርዓት ውድቀት በኋላ “የት እንወድቅ ይሆን?” ብለው ከሚያስቡ የዋሆች ብዙ መለየት አለብን። ኢትዮጵያ መካን አለመሆኗን ዙርያ ገባውን መቃኘት ያስፈልጋል። ለህዝብ መብት በመታገላቸውና በመጮሃቸው በዘረኞች መንጋጋ ውስጥ የነበሩ ከናዚ ማጎርያ (ኮንሴንትሬሽን ካምፕ) ያመለጡ መስለው በአካል ደቅቀው፣ በመንፈስ ግን ገዝፈው የወጡትን ጀግኖቻችንን ስናይ፣ ለአገራቸው ያላቸውን ተመሳሳይ ራዕይ በርቱዕ አንደበታቸው የተናገሩትን ስናዳምጥ ኢትዮጵያ ተስፋ አላት እንድንል እንገደዳለን። ይህንንም መረራ ጉዲናን በአምቦ፣ በቀለ ገርባን በአዳማ፣ አንዱዓለም አራጌና እስክንድር ነጋን በከርቸሌ ደፍ፣ ኮሎኔል ደመቀን በጎንደር፣ እንዲሁም ሁሉንም እስረኞች በየአካባቢያቸው ህዝቡ ያሳየው አቀባበል መሪዎቹና የነገ ተስፋዎቹ ለመሆናቸው የሰጠው ሪፈረንደም ነው። ይህ የህዝቡ ያልተገደበ ስሜት ያራዳቸው አምባገነኖች የመውደቂያቸው ማፋጠኛ የሆነውን አስቸኳይ አዋጅ ማወጃቸውን ስናይ ኢትዮጵያን ያህል ትልቅ ህዝብ ለዚህን ያህል ጊዜ ማሰብ በተሳናቸው በትንንሽ ዘረኞች መገዛቱ ይቆጫል፣ያንገበግባል። ጥቂቶችን ፈትተው ኢትዮጵያን የሚያስር አዋጅ ማወጃቸው የጤንነት ምልክት አይደለም።

በጥቂቱም ቢሆን የተፈተኑ የኢትዮጵያን ልጆች እስኪ እንቃኛቸው። በጨካኞች መዳፍ ሲዳጡ የበለጠ እየጠነከሩ የወጡትን የወህኒ ሰለባዎች በቀለ ገርባ፣ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ መረራ ጉዲና፣ አንዷለም አራጌ፣ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ አበበ ቀስቶ፣ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ፣ አታላይ ዛፌ፣ ማሙሸት አማረ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ሃብታሙ አያሌው፣ ኦልባና ሌሊሳ፣አህመዲን ጀበልና ሌሎች ኡስታዞቻችን፣ ብዙ ሺዎች ስለሃገራቸው በየቦታው የተሰቃዩና የሚሰቃዩላት ቆራጥ ልጆች ያሏት ኢትዮጵያ መሃን አይደለችም።

በሰላማዊ ሆነ በመሳርያ ሃይል ኢትዮጵያ ነፃ ልትወጣ ይገባታል ብለው ህይወት፣ ጊዜና ጉልበታቸውን የሚሰው ብርሃኑ ነጋ፣ሌንጮ ለታ፣ ዲማ ነገዎ፣ ኮንቴ ሙሳ፣ አስገደ ገብረስላሴ፣ አብርሃ ደስታ፣ ይልቃል ጌትነትና ሌሎችንም ሺዎች ያፈራች ኢትዮጵያ ጨለማውን የሚያሻግሯትና በብሩህ መሰረት ላይ የሚያስቀምጧት የተበታተኑ ግን በመሰባሰብ ላይ ያሉ ልጆች አሏት።

ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት በወያኔ ሲዳጥ ተጨፍልቀው ነጥረው የወጡ የአምባገነኖች መቅሰፍትና የህዝብ ተስፋ የሆኑ ጋዜጠኞች በአገርና በመላ ዓለም ተሰራጭተው የኢትዮጵያን አየር በመረጃ እያጥለቀለቁ በመሆናቸው የጨለማ ሃይላትን መደበቂያ አሳጥተዋል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና አክቲቢስት ኢትዮጵያውያን ታማኝ በየነ፣ ወንድማገኝ ጋሹ፣ ጋሩማ በቀለ፣ ገአስ አህመድ፣ገብረመድህን አርአያ፣ አሊ ሁሴን፣ ገረሱ ቱፋ፣ ኦባንግ ሜቶ፣ ተማም አባ ቡልጉ፣ ዶክተር ያቆብ፣ የሰመጉ ጀግኖች የዘረኞችን ወንጀል እያጋለጡና በሰነድ እያስቀመጡ ለፍርድና ለታሪክ ግብአት እያኖሩ ነው።

ሳይማር ያስተማራቸውን ህዝብ ያልዘነጉና እውቀታቸውን በተለያየ አጋጣሚ እያካፈሉ የነገዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት ትውልዱን የሚያስተምሩ መስፍን ወልደማርያም፣ መሳይ ከበደ፣ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ፣ ጌታቸው በጋሻው፣ አክሎግ ቢራራ፣ አወል ቃሲም አሎ፣ ታደሰ ብሩ፣ ተድላ ወልደዮሃንስ፣ ደረሰ ጌታቸውን የመሳሰሉ እልፍ ምሁራን ያሏት ኢትዮጵያ ወድቃ አትቀርም።

ለገዥዎች መቅሰፍት ለህዝብ ደግሞ ተስፋ የሆኑ ቄሮዎችና ፋኖዎች ሃይላቸው የማይገደብ ምንጫቸው የማይነጥፍ ነጎድጓድ በመሆን ትግሉን እያጋሙት ናቸው። የድሏን ፍሬ የነጠቁ የትናንት ጉግ ማንጉጎች ትቢያ የሆኑትን ያህል የዛሬዎችም እየተፍረከረኩ ታሪክ ወዳዘጋጀላቸው ስፍራ እያዘገሙ ነው።

የነገዋ ኢትዮጵያ የጥቂት አድቢ ግለሰቦች፣ የአምባገነኖችና የዘራፊዎች እንዳትሆን እጅ ለእጅ ተያይዘን ጨለማውን በማለፍ ዓለም ወደደረሰበት አድማስ እናሻግራት። ኢትዮጵያ መካን አይደለችም እልፍ ጠንካራ ልጆች አሏት።

LEAVE A REPLY