“የምንኩስና ልብስ በሞት ጊዜ እንኳን አይወልቅም” /ዲ/ን ዳንኤል ክብረት/

“የምንኩስና ልብስ በሞት ጊዜ እንኳን አይወልቅም” /ዲ/ን ዳንኤል ክብረት/

በወኅኒ ያሉት የዋልድባ መነኮሳት የምንኩስና ልብሳቸውን እንዲያወልቁ መታዘዛቸውን ለፍርድ ቤት አመልክተዋል፡፡ ይህ ከሆነማ ወኅኒ ቤቱ የአንድን ሰው የመመንኮስ መብት ይነፍጋል ማለት ነው፡፡ እንድን ሰው የምንኩስና ልብስህን መልበስ አትችልም ካልከው መመንኮስ አትችልም ማለትህ ነው፡፡ የምንኩስና ልብስ እንኳን በእሥር ቤት በመቃብር አይወልቅምና፡፡

በዐፄ ዓምደ ጽዮንና በዐፄ ሰይፈ አርእድ ዘመን ለእውነት የታገሉት አራቱ ኃያላን መነኮሳት (አባ በጸሎተ ሚካኤል፣ አባ ፊልጶስ፣ አባ አኖሬዎስና አባ አሮን) በግፍ ከተቀጡት ቅጣት አንዱ የምኩስና ልብሳቸውን አውልቀው እንዲራቆቱ ማድረግ እንደነበር ገድሎቻቸው ይነግሩናል፡፡

በገድለ አሮን ላይ እንዲህ ይላል፡- ያን ጊዜም ንጉሡ(ሰይፈ አርእድ) ልብሶቻቸውን እንዲነጥቋቸው አዘዘ፡፡ ወታደሮቹም የቅዱሳኑን የአባቶቻችንን፣ የመበለታቱን የእናቶቻችንን ልብሶቻቸውንና አስኬማዎቻቸውን ገፈፏቸው፡፡ በዚህ ጊዜም ‹ራሴን ይቁረጡ፤ ሆዴንም ይውጉ፤ ከነ አስኬማዬም ልሙት፤ እንጂ ልብሰ ምንኩስናዬን አልሰጥም› ይሉ ነበር፡፡ ገረፏቸው፡፡ ፊታቸውንም በጥፊ መቷቸው፡፡ ወደ ምድርም ጣሏቸው፤ በእግሮቻቸውም ረገጧቸው፡፡

መታጠቂያዎቻቸውንም በስድብና በመከራ ፈቱባቸው፡፡ ያንን ነገር እንደ እጉሥታር(የዕሬት ወገን የሆነ መራራ ቅጠል) ሊናገሩት ይመራል፡፡ የጩኸታቸውና የእሪታቸው ድምፅ እስከ ሰማይ ተሰማ፡፡ በዚህም ጊዜ ልብሳቸውን ገፈፏቸው፤ ዕርቃናቸውንም ቆሙ… (አራቱ ኃያላን፣ 412) ይላል፡፡

ከ700 ዓመታት በኋላ ተመሳሳዩ ቅጣት መምጣቱ አስገራሚ ነው፡፡ሀገሪቱ አሁን የሚያስፈልጋት መግባባትና መከባበር፣ ሰላምና መረጋጋት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት የሕዝብን ምሬትና ብሶት የሚጨምሩ፣ ወደ ሰላምና መረጋጋት፣ ወደ ውይይትና መግባባት፤ የሚደረገውን ጉዞ የሚያደናቅፉትን ተግባራት የሚመለከታቸው ሁሉ ማረም አለባቸው፡፡ የመነኮሳቱን የምንኩስና ልብስ ማስወለቅ ለሀገሪቱ የሚፈይደው ምንድን ነው? አብረዋቸው የተከሰሱት እየተፈቱ የእነርሱ ፍርድ ቤት መመላለስስ ትርሙ ምንድን ነው?

አባ ፊልጶስን ንጉሥ ዓምደ ጽዮን መከራ ባጸናበት ጊዜ የተሰደደው ወደ ትግራይ ተንቤን ነበር፡፡ በተንቤን ታሥሮ ከነበረበት እሥር ቤት ያስፈቱት ደገኞቹ የተንቤን ምእመናን ነበሩ፡፡ ‹መኮንነ ተንቤን›ን አስጨንቀው፣ አባታችንን ማሠር የለብህም ብለው፤ የግፈኛውን ንጉሥ ትእዛዝ ሽረው፤ በሸዋ ያላገኘውን ነጻነት በተንቤን ለሦስት ዓመታት እንዲያገኝ ያደረጉት፤ ንጉሥ ዓምደ ጽዮን እስኪሞት በሰላም ያኖሩት የተንቤን ሰዎች ነበሩ፡፡ እንደ ተንቤን ሰዎች ያሉ፣ ‹ፍቱ› የሚሉ ደገኞች ዛሬ ወዴት አሉ?

መነኮሳቱን ፍቷቸው፡፡ በእሥረኞቹ መፈታት የተፈጠረልን ደስታ ፍጹም ይሆን ዘንድ መነኮሳቱን ፍቷቸው፡፡ ምንኩስና ታሥሮ ማየት አንሻምና መነኮሳቱን ፍቷቸው፡፡ ተገንዘው የለበሱት ልብሰ ምኩስና በኃይል ሲወልቅ ማየት አንሻምና መነኮሳቱን ፍቷቸው፡፡

LEAVE A REPLY