በለውጥ ማዕበል ውስጥ የምትናወጠው የኢህአዴግ መርከብ! /በዳዊት ከበደ ወየሳ/

በለውጥ ማዕበል ውስጥ የምትናወጠው የኢህአዴግ መርከብ! /በዳዊት ከበደ ወየሳ/

ኢትዮጵያዊነት ሞቶ ፍታት እየተደረገለት ነው ከሚባለው ኦሮሚያ ምድር፤ የአዳዲሶቹን መሪዎች ንግግር እየሰማን ቀልባችን ወደነሱ መሳብ ከጀመረ ሰነባበተ። ህዝቡ ይህን ያህል ስሜት ሰጥቶ ሊሰማቸው የቻልንበት ዋና ምክንያት ደግሞ፤ ሲባልለትና ሲጮህለት የነበረውን ኢትዮጵያዊነት ካልጠበቀው ወገን፤ ጎልቶ እና ጎልብቶ ይሰማው ስለጀመረ ነው። እናም ይህን መልካም ጅምር የሚቃወም አንደበት ባይኖረንም፤ አሁንም ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎችን ግን ደጋግመን ማንሳታችን የማይቀር ነው። ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎችና ያልታበሱ እንባዎች አሉ።

እርግጥ ነው… ዛሬ ከኦህዴድ/ኢህአዴግ አመራሮች የምንሰማቸው የኢትዮጵያዊ ማንነት ዘርፈ ብዙ ትንታኔዎች፤ “ምነው እስከዛሬ የት ነበራቹህ?” እያልን እንድንቆጭ ማድረጉ አልቀረም። የነዚህ በሳል ኢትዮጵያውያን ንግግም… የኦሮሞ እና የአማራ ህዝብ እድሜ ልኩን እየተፋጨ እና እየተጋጨ እንዲኖር ይፈልጉ ለነበሩት ወገኖች፤ ልብ የሚያስከፋና አንገት የሚያስደፋ ሆኗል።

ከአስርቱ ቃላት አንዱ… “ግብዝ አትሁን!” ይላል። ዛሬ እነዶ/ር አብይ አህመድ ለምታደርጉት መልካም ንግግር፤ ከመቀመጫችን ብድግ ብለን ልናጨበጭብላቹህ እንችል ይሆናል። ነገር ግን የመጣችሁበት እና ከዚህ ያደረሳችሁን ኢህአዴጋዊ መንገድ ስለምናውቀው፤ ከጭብጨባ አልፈን፤ እየሰመጠች ባለችው የኢህአዴግ መርከብ ላይ ለመሳፈርም ሆነ በምትሄዱበት መንገድ ለመሄድ የሚቸገሩ ብዙ ናቸው።

በጌተሰማኒ ኢየሱስን አቅፎ ከሳመው በኋላ ምሽቱን የከዳው የአስቆሮቱ ይሁዳና ኢህአዴግ ተወራራሽ ጸባይ ስላላቸው፤ መቼ ልትከዱን እንደምትችሉ አናውቅምና፤ በግብዝነት ተሞጋግሰን፤ ይሄም ቀን አልፎ እንዳንተማማ… ለግዜው እሩቅ ለሩቅ ሆነን የሆድ የሆዳችንን እንጨዋወት።

እንደእውነቱ ከሆነ… ዛሬ እናንተ የምትናገሩትን የኢትዮጵያዊነት መልዕክት፤ ትላንት በተለያዩ መድረኮች የኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ይናገሩት የነበረ በመሆኑ፤ ለብዙዎች አዲስ ነገር አይደለም። አዲስ የሆነብን ነገር… ኢትዮጵያዊነትን እንዲጠሉና እንዳይቀበሉ ብዙ ስራ ከተሰራበት የኦሮሚያ ምድር፤ ጥቂት የኦሮሞ ልሂቃን ከያላችሁበት ብቅ ብቅ ብላቹህ፤ ስለኢትዮጵያዊነት ስትመክሩ እና ስትመሰክሩ መስማታችን ነው። በዚህ ኢትዮጵያዊነት እንደቀጭን ፈትል እየሰለለ መጥቶ ሊበጠስ በተቃረበበት ዘመን፤ እነሆ ከናንተ አንደበት ስለኢትዮጵያዊነት መስማት… እንደመልካም ሙዚቃ፤ ደስ የሚያሰኝ እና የማይሰለች ሆኖብናል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ እና ተሰምቶ በማይታወቅ ደረጃ፤ አንድ በስልጣን ላይ ያለ መንግስት አንደኛው ህዝብ በሌላኛው እንዲነሳሳና እንዲጠላው፤ በሃይማኖት ልዩነት አንደኛው ሌላውን በጥርጣሬ እንዲያየው የሚያደርግ ስራ የሰራ ብቸኛ አካል ቢኖር ኢህአዴግ ብቻ ነው። ከኢህአዴግም ደግሞ ይህንን የ“ከፋፍለህ ግዛ!” ስልት በመጠቀም ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተው ህወሃት ወይም የትግራይ ወያኔ ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት በተለይ ኦሮሞው በአማራ ላይ እንዲነሳ እና እድሜ ልኩን አማራውን እየወቀሰ እና እያለቀሰ እንዲኖር ሰፊ ዘመቻ ሲሰራ ቆይቷል።

የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ አንድነት ታሪክ ውስጥ ሰፊ ድርሻ ያለው ህዝብ ቢሆንም፤ ይህንን ታሪክ በመሰረዝና በመደለዝ፤ የኦሮሞ ህዝብ በአማራ ህዝብ ሲጨቆንና ሲገደል እንደነበር ተደርጎ በተደጋጋሚ ተለፍፏል። በትምህርት ቤት ጭምር የኦሮሞ ልጆች እንዲህ አይነት የጥላቻ ታሪክ እንዲማሩ ተደርጓል፤ እየተደረገም ነው። የኦሮሞ ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር በአማርኛ ቋንቋ እንዳይግባባ፤ ፊደሉንም እንዳይማር ተደርጓል። ለ27 አመታት በተደረገ የጥላቻ ፖለቲካ ምክንያት… የኦሮሞ ህዝብ እንኳንስ በአማርኛ ሊጽፍ ቀርቶ፤ በአማርኛ የተጻፉ ታሪኮችን ቀዳዶ የሚጥል፤ እንኳንስ የአንድነት ታሪኩን ሊያነበው ቀርቶ፤ በአንቀጽ 39 ቀቢፀ ተስፋ አገሩን በሃሳብ ሲገነጣጥል የሚውል አዲስ ትውልድ ለማፍራት፤ በህወሃት በኩል የማያቋርጥ ዘመቻ ሲደረግ እንደነበር የማያውቅ ኢትዮጵያዊ ካለ፤ በራሱ ታሪክ ላይ ተኝቶ ሲያበቃ ገና አሁን ከእንቅፉ የባነነ ምስኪን መሆን አለበት።

ስለኢትዮጵያ ክብር አድዋ ድረስ ዘምተው ደረታቸውን ለጣልያን ጥይት የሰጡት፤ የፊታውራሪ ገበየሁ አባጎራው እና የኦሮሞ ፈረሰኞች ታሪክ፤ የነፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግሴ እና የነባልቻ አባነፍሶ ገድል በኦሮሚያ ምድር አይነገርም። በ19ኛው ክፍለ ዘመን የኦሮሞን ህዝብ ከዳር እስከዳር አንድ ያደረጉት፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉት ራስ ጎበና ዳጨ… እንደከሃዲ እንጂ፤ እንደጀግና ክብር አልተሰጣቸውም። የ“ኦሮሞን ህዝብ አትንኩ!” ብለው፤ ህዝቡን ለመከላከል በእምባቦ ጦርነት ትልቅ ትግል ያደረጉት አጼ ምኒልክ… እንደወራሪ እንጂ እንደኦሮሞ ህዝብ ወዳጅ ተደርገው ሲቀርቡ ከቶውኑ በኦሮሚያ ምድር ላይ አንሰማም።

የሌሎች አገር ዜጎችን በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ስር በማሰባሰብ በጣልያን በርሃዎች በመዋጋት፤ አለምን ያስደነቀው ጀግናው አብዲሳ አጋ በተወለደበት የወለጋ ምድር ሃውልት አልቆመለትም። እነደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፣ እነአቢቹ፣ እነጄነራል ጃጋማ ኬሎ፣ የነጄነራል ሙሉጌታ ቡሊ… የኦሮሞ ምድር ያፈራቸው፤ ለኢትዮጵያ አንድነትና ፍቅር ከፍ ያለ ስራ ሰርተው ያልፉ ጀግኖች፤ ዛሬ መልካም ስማቸውና ስራቸው በኦሮሚያ ክልል አይዘከርም።

በአጠቃላይ… በዘር ተደራጅቶ ወደ ውጭ ሳይሆን ወደ ውስጥ እንዲያስብ፤ ለ27 አመታት ኢትዮጵያዊነትን እንዲጠላ ትምህርት ሲሰጠው የነበረው የኦሮሞ ህዝብ፤ እንኳንስ የሌላውን ሊያደንቅ ቀርቶ የራሱንም ጀግኖች እንዳያውቅ እና እንዳይመርቅ ተደርጎ፤ በጨለማ ውስጥ እንዲኖር ለማድረግ ህወሃት ቀዳሚውን ሚና ተጫውቷል። ከነሌንጮ ለታ እስከነሃሰን አሊ ድረስ፤ በዘር መስመር ወደታች የሚያስብ እንጂ በኢትዮጵያዊነ መንፈስ ስለአንድነት የሚሰብክ አንድም የኦህዴድ ባለስልጣን ሳናይ፤ እነዶር መረራ እና በቀለ ገርባን እያደነቅን ብዙ አመታት አስቆጠርን።

በአንድ ወቅት አባ ዱላ ገመዳ ላይ የሆነውን ጉዳይ በዚህ አጋጣሚ እንጨዋወት። አባዱላ ገመዳ ሰፊ የኦሮሞ ህዝብ ድጋፍ ለማግኘት፤ ወደ ሰላሌ ይዘልቃል። የሰላሌ ኦሮሞ በባህሉ መሰረት ለአባ ዱላ ገመዳ አስፈላጊውን አቀባበል አደረገለት። ከደብረሊባኖስ ማዶ “ሽንኩርት ሚካኤል” የተባለችው መንደር በአባ ዱላ ገመዳ ድግስ ደመቀች። የአገር ሽማግሌዎች ምርቃት አደረጉ። በሬ ታረደ፤ ጠጅ ተጠጣ። ደስታ በደስታ ሆነ። በመጨረሻም ጭፈራ ተጀመረ። ይሄን ግዜ ኢጆሌ ሰላሌ ፈረሱ ላይ ሆኖ ዳንጋላሳ እያረገ… “ያ ሆ!” ይል ጀመር። አባዱላ ገመዳን የሚያሞግስ ዘፈን እና ጭፈራ ያደርጋሉ ተብሎ ሲጠበቅ…
“ያ መረራ… ኦ!
ያ በቀለ ገርባ… ሆ!” እያሉ ዘፈን እና ጭፈራውን፤ ሽለላ እና ሙገሳውን በቦታው ላልተገኙት፤ ከቶውኑም ላልጋበዟቸው፤ ነገር ግን ለሚወዷቸው ሰዎች ሰጡ። ይሄ ከሆነ ጥቂት አመታት ተቆጠረ። እኛን ፈገግ አሰኘን፤ ለኦህዴድ የኦሮሞ ባለስልጣኖች ግን ትምህርት ሰጥቶ አለፈ።

እናም ይሄ ሁሉ ሆኖ… በኦሮሚያ ላይ ከተዘራው የአረም እርሻ ፈንጠር ብለው፤ እነበቀለ ገርባና እነዶ/ር መረራ ጉዲና መብቀላቸው ደስ የሚለንን ያህል፤ እንደነለማ መገርሳ እና ዶ/ር አብይ አህመድ አይነት ኢትዮጵያውያን ደግሞ በዘረኝነት አረም መሃል እንደዋርካ ዛፍ በቅለው፤ ከስር የበቀለውን የዘረኝነትን አረም ሲያቀጭጩት ማየት፤ በመንፈስም ሆነ በስጋ ደስ የሚል ስሜት ይፈጥራል።
ዛሬ እነዶ/ር አብይ አህመድ የሚናገሩትን አይነት የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የተላበሰ ንግግር ከአማራ፣ ከትግራይ ነጻ አውጭዎች ወይም ከኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች አንሰማም። ይልቁንም የሁለቱ ህዝቦች ቄሮዎችና ፋኖዎች በደም ያስተሳሰራቸውን መሃላ ፈጽመዋል። እናም የኦሮሞ ልጆች ደም ሲፈስ፤ የአማራ ህዝብ ተቆጥቶ… “የኦሮሞ ህዝብ ደም፤ ደሜ ነው!” ሲል፤ አማራው ሲገደል ደግሞ… “የአማራው ህዝብ ደም፤ ደሜ ነው!” የሚል ሞጋች ትውልድ ተፈጥሯል። እንዲህ አይነቱ የህዝብ ለህዝብ መደጋገፍ ጥንትም የነበረ ኢትዮጵያዊነት ቢሆንም፤ ሌላውን በማጣላት… እሱ ዳኛ ሆኖ መሰንበት የሚፈልገውን ህወሃት ግን ትልቅ የትውልድ መርዶ ነው የሆነበት።

እንግዲህ በዚህ ሁሉ ምስቅልቅል መሃል ነው… በኦሮሚያ ጥሻ ውስጥ የተጣለውን ኢትዮጵያዊነት አንስተው፤ በአንድነታችን ላይ ላይ የተጋረጠውን ጥቀርሻ አጽድተው ወደፊት ለመሄድ የተዘጋጁ አፍላ ጉልበት እና ጎምቱ እውቀት ያላቸውን የኦሮሞ ልጆች ለማየት የበቃነው።
በአጠቃላይ… የአማራ፣ የትግራይ፣ የደቡብ እና ሌሎች የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች በዘር ላይ ያነጣጠረ ፖለቲካዊ አደረጃጀት ይዘው፤ ህወሃትን በማስደሰትና በማሸርገድ መሃል ዥዋዥዌ ሲጫወቱ፤ ኢትዮጵያዊነት ሞቶ ፍታት እየተደረገለት ነው ከሚባልለት ኦሮሚያ ምድር፤ የኢትዮጵያን ትንሳዔ መስማት እኛን የሚያስደስተንን ያህል፤ ጥቂቶችን ህወሃትን ብቻ ሳይሆን፤ በህወሃት ሳንባ የሚተነፍሱትን ጥቃቅን ነፍሳቶች ጭምር ሊያስኮርፋቸው እንደሚችል ይታወቃል።

ይህ የኢትዮጵያዊነት ትንሳዔ… ለህዝብ መነሳሳት የሚሰጠው ፋይዳ ከፍተኛ ቢሆንም፤ “የህዝቡ ጥያቄ ተመልሷል፤ እንባውም ታብሷል” ማለት ግን አይደለም። ላለፉት 27 አመታት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ የተሰራው በደል እና ግፍ አደባባይ ወጥቶ በዳይ እና ተበዳይ ይቅር መባባል አለበት። እርግጥ ነው፤ እርቅና ሽምግልና አራራ እና ጃርሱማ በአማራ እና በኦሮሞ ባህል ይዘወተራሉ። ለሰላም እና ለእርቅ እራሱን የማያዘጋጅ የሰዎች ስብስብ በህገ አራዊት የሚመራ ኋላቀር በመሆኑ፤ ይህንን መልካም ባህል እንደህወሃት ላሉ የራስን ህዝብ ጠላት አድርገው በቂም በቀል መቅጣት ለሚፈልጉ ድርጅቶች ጭምር ማስተዋወቅ ያስፈልጋል።

እኛም የኦቦ ለማ መገርሳንና ዶ/ር አብይ አህመድን ንግግር በሰማን ቁጥር፤ ኢትዮጵያውያንን ወደ ብሄራዊ እርቅ የሚወስደው መንገድ ከርቀት ሊታየን ይችል ይሆናል። ይህ ማለት ግን “ኢህአዴግ ያደረሰብንን በደል እንረሳው” የሚል ማዘናጊያ እንዳይፈጥርብን መጠንቀቅ አለብን። በዚህ ሁካታ እና ግርግር መሃል የስንትና ስንት ወገኖቻችን እንባ እና ደም ሊረሳን አይገባም። አሁን በተፈጠረው የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ላይ ቆመን፤ ብሔራዊ እርቅ የመናፈቃችንን ያህል፤ …የበደሉ በህግ የሚጠየቁበትን፤ የተበደሉም የሚካሱበትን መንገድ ማሰብ ይኖርብናል።

ይህች ኢትዮጵያ ማለት… በህዝቦቿ ባህል እና ታሪክ የከበረች፤ “በአያቶቻችን ደም እና አጥንት፤ ጸሎት እና ጉልጥምት የተገነባች አገር ናት።” ከዚህ በኋላ የምትገነባው ኢትዮጵያ በደም ሳይሆን፤ መሰረቷን ህግ እና እርቅ ልታደርግ ይገባታል። ይህ በሆነ ግዜ… የኛ እና የነሱ፤ ብሎም የዚህ ትውልድ ታሪክ በወርቅ ቀለም ይጻፋል።

እስከዚያው ግን… በዚህ ሁሉ የለውጥ ማዕበል ውስጥ የምትናወጠው የኢህአዴግ መርከብ፤ በነለማ መገርሳ እና በነዶ/ር አብይ አህመድ ካፒቴንነት ከመስጠም ከተረፈች፤ እንደአንድ ጨዋ ኢትዮጵያዊ “እንኳንም እግዜር አተረፋቹህ!” የምንልበትን ቀን በመናፈቅ፤ ካልተመለሱ ህዝባዊ ጥያቄዎቻችን ጋር ዳግም እንደምንገናኝ በማሰብ፤ “ጋሪቲ” ብለን እንሰነባበት።

LEAVE A REPLY