ህወሓት በመላው ኢትዮጵያ እየተደረገበት ባለው ትግልና ጫና ተገዶ፥ እንደዚሁም በኢህአዴግ ራሱ ውስጥ ባሉት ፓርቲዎች መካከልም በተፈጠረው ፉክክርና ፍትጊያ የተነሣ ምስጢር አድርጎ ደብቆት የነበረውን ሐሰትና ማወናበድን አንድ ባንድ እያለ እያጋለጠው ይገኛል። ይህ ሁኔታ እዚህ ላይ የሚቆም ኣይደለም፣ ህዝቡ መብቱን ለማስከበር ቆርጦ ተነስተዋልና።
ቀደም ብሎ የማጥራት ዘመቻ በሚል ኣስመሳይ እንቅስቃሴ፥ የማስተዳደር ድክመት እንዳለው፣ የዴሞክራሲ ሂደቱን እንዲጠብ ማድረጉን፣ ሙስና መንገሱን፣ የሐሰት ሪፖርቶችን በማቅረብ የሌለ ዕድገት እንደተመዘገበ ያሰራጭ እንደነበረ ኣምኗል። ከዚህ ኣልፎም ከሕግ ውጭ የታሠሩ ፖለቲካዊ እሥረኞች የሉም፥ የሉኝምም እያለ ከቆዬ በኋላ አሁን እየፈታኋቸው ያሉት የተቃዋሚ ድርጅቶች አባላት በፈጸሙት ወንጀል ነበር እንጅ በፖለቲካ አመለካከታቸው እንዳልነበረ ገልጿል። ያ የፖለቲካ እሥረኞች የሉንም፣ በፖለቲካ ልዩነት ሰዉን አናሥርም ይል የነበረው እንቶ ፈንቶ የፈጠራ ወሬ ውሃ የማይቋጥር እንደሆነ ህዝቡ አሳምሮ ያውቀዋል።
ይህ ወንጀል፥ በራሱ ላይ እየተፈፀመበት ያለው ህዝባችን ቀርቶ እነኛ ጥቅማቸውን እንዲያስጠብቅላቸው በድጎማ የሚንከባከቡት ምዕራባውያን ጭምር የነቁበት፣ ፀሐይ የሞቀው ገሃድ ሓቅ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ባጠቃላይ፥ በተለይም በትግራይ ውስጥ ዜጎች ምሬታቸውን በመግለጻቸው ምክንያት እንደሚታሠሩ መደበቅ የማይቻል መራራ ሓቅ ነው። ለዚህም ጥሩ አብነት ሊሆን የሚችለው በእግሪ ሓሪባ አርሶ አደሮች ላይ ያደረሰውን ግፍ ያስታውሷል። ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ ለተገለጹት ሓቆች ቀደም ሲል የሥርዓቱ ተቃዋሚ ኃይሎች ከነርሱ መካከልም ትዴት(ታንድ) በተደጋጋሚ ድርጊቱን በመቃወም ቅሬታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል። ሆኖም ግን ይህንን በማለታቸው ብዙዎች ታስረዋል፣ ተገርፈዋል፣ ተገድለዋል ተሰድደዋል። በመሆኑም የፖለቲካ እሥረኞች የሉንም ብሎ ማለት ራስን ከማቄል የዘለለ ትርጉም ስለሌለው፥ በሌላ ደረቅ ወንጀል ካልተሳተፉት በቀር ሁሉም እሥረኞች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በነፃ ተፈትተው በተገቢው ሁኔታ ሊካሱ ይገባል።
ከዚህ ለየት ባለ ሁኔታ ደግሞ ሰሞኑን አቶ ዓባይ ጸሃዬ በሰጡት መግለጫ፣ ተቃዋሚዎች ለሠላሳ ዓመታት ያህል የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚ ሳይሆን እያለ እንደተጠቀመ አድርገው በመቁጠር ዘመቻ ሲያካሂዱ፣ ሳንጋፈጣቸው በመቆዬታችን በኢህአዴግ ውስጥ ያሉት ፓርቲዎችም ጭምር ይህን አመለካከት እንዳላቸውና ጠባብ ብሔራዊ ስሜት ማደጉን፣ ወጣቶቻችንንም ስለ ኢትዮጵያዊነትና አንድነት ዕውቀት እንደሌላቸው፥ ወዘተ… እያሉ ዘርዝረው አቅርበዋል።
በመጀመሪያ ደረጃ የትግራይ ህዝብ ሳይጠቀም እንደተጠቀመ አስመስሎ በቴሌቪዥንና በሁሉ የህዝብ መገናኛ መሳሪያዎች በሰፊው ሲያስተጋባና ሲያራግበው የነበረው የህወሓት አመራር እንደነበር በግልጽ ሊታወቅ ይገባል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ባንድ ወቅት በኢፌዲሪ ፌዴራል ፓርላማ ቀርበው ባሰሙት ንግግር “የትግራይ ገበሬዎች መቶ ፐርሰንት ሞዴል አርሶ አደሮች ሆነዋል” ብለው ሪፖርት ሲያቀርቡ እነ አቶ አባይ ጸሐዬና ሌሎቹ የህወሓት አመራርና አባላቶቹ የት ነበሩ? የሚል ጥያቄ ልናቀርብ እንገደዳለን። ቀጥሎም ህወሓት በባለዋናነት የሚገዛት ትግራይ ገዥዎቿ ሲያቀርቡት በነበረው የዕድገት ሪፖርቶች በመነሣት፣ ትግራይን በዓይኑ ያላያት ኢትዮጵያዊ ወገን ትግራይ ከፍተኛ ዕድገት ላይ ደረሰች፥ ተመነደገች ብሎ ቢናገር ምን ያስገርማል? እንደ ማስረጃ አድርጎ ያቀረበው እኮ ህወሓት ራሱ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ተመርኩዞ ነው።
ትናንት እመሬት ላይ የሌለ የውሸት ሪፖርት እያቀረባችሁ ነው ስንላችሁ፣ የትግራይ ዕድገትን የማያስወድዳቸው መናፍቆች ስትሉን አልነበረንም! መቐለ ከተማ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ዕጥረት አለው ሲባል እኮ ነው የትግራይ የውሃ አቅርቦት 82% ደርሷል እያላችሁ የሀሰት ሪፖርት ስታቀርቡልን የነበራችሁት። ቅንነት ባጠገባችሁም ሲያልፍ አይነካካችሁም እንጅ ቢኖራችሁ ኖሮማ፣ አሁን የምትሉትን ልክ እንደኛው ስትሰሙት ከቆዬ እና የትግራይ ህዝብም ያልበላነውን እንደበላን አድርጋችሁ አታስቆጥሩን ብሎ ሲነግራችሁ ለምንድነው ዉሸቱን ያልታገላችሁት? ባንድ በኩል ህወሓት የሌሉ ጠላቶችን እንዳሉ አስመስሎ እየፈበረከ የትግራይ ህዝብ በስጋት የተነሳ እጉያችሁ ሥር እንዲወሸቅና ከጎናችሁ እንዲሰለፍ ስትሉ፥ ይካሄድ የነበረውን የስም ማጥፋት ዘመቻን በደስታ ስትቀበሉት የቆያችሁት እንዲያዉም በውሸት የትግራይ ህዝብ በወያኔያችን አድጎ ብዙ ነገር አግኝቷል እያላችሁ የመምቻ ዱላ ስታቀርቡ ቆይታችኋል። በሌላ በኩል ደግሞ በተቃዋሚዎችም ላይ ከልክ ያለፈ ንቀት ስለነበራችሁ ነው።
ጠባብነቱስ ቢሆን እንዲነግስ ያደረገው ራሱ ህወሓት/ኢህአዴግ አይደለም ወይ! ህዝቦች ድሮም ቢሆን ለዘመናት እዚያው አብረው ነበር ሲኖሩ የነበሩት፤ ይሁንና ግን አሁን እየታዬ ያለው የጎሳ ጥላቻ እንዳሁኑ ገንኖ የወጣበት ጊዜ ታይቶ አይታወቅም። በመሆኑም በብሔሮችና ብሔረሰቦች መካከል እየታየ ያለውን ቅራኔና ጥላቻ እንዲባባስና እንዲያድግ ያደረገው ህወሓት/ኢህኣዴግ ሲያካሂደው በነበረውና እያስቀጠለው ባለው የተዛባ ፖሊሲ የተነሳ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
ህዝባዊ አንድነትን አጠናክሮ ስምምነቱን በማጠናከር ፈንታ ልዩነቶቹ ላይ በማተኮር እርስ በርሱ እንዲጠላላና እንዲጠራጠር አደረጋችሁ። በኦሮሞ ክልል አርሲ፣ አኖሌ ውስጥ የአማራ ወታደር የኦሮሞ ሴትን ጡት ሲቆርጥ የሚያሳይ ሃውልት ሲሠራ፣ እየሳቃችሁና እየተደሰታችሁ ዝም ነበር ያላችሁት፥ ምክንያቱም በኦሮሞና አማራ ህዝቦች መካከል ቅራኔ እንዲያድግ በመፈለግ ነው። ከደቡብ ኢትዮጵያ በርካታ የአማራ ብሔር ተወላጆች ሲፈናቀሉስ፣ ትክክል አይደላችሁም ብሎ ጥፋቱ እንዲቆም በማድረግ ፈንታ፥ ባካባቢው ያላግባብ የሠፈሩ ሰዎች የአካባቢውን የደን ልማት በማውደማቸው ነው የተባረሩት እየተባለ በኢህአዴግ የመገናኛ ብዙኃን ሲስተጋባ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ከቦታው ተፈናቅሎ በየመንገዱ ለተጣለው ሰው እንኳን ዕርዳታ አልተደረገለትም፥ ህወሓት/ኢህኣዴግ ለነዚህ ዜጎች ያሳዬው ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ርኅራሄ አልነበረም።
መንግሥት ምንም ሊያደርግላቸው ባለመቻሉም የተነሳ ነው በመኢአድ ጽ/ቤት እንዲጠለሉ የተገደዱት። ይህም ኢ-ሰብኣዊ ተግባር ነበር ያ የተፈናቀለው ህዝብና ቀሪው ወገን ይህ መንግሥት አይወክለኝም እንዲል ያበቃው።
ሕገ መንግሥቱ ልዩነቶችን የሚያሰፋ እንጂ አንድነትን የሚያጠናክር አልሆነም። ሙሉ የኢትዮጵያ ሥልጣን ይዛችሁም ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝቦችን በእኩል ዓይን ማየትና ማገልገል ይቅርና አሁንም ድረስ አማራ ጠላት ነው ትላላችሁ። ይህ ኣባባላችሁ እንኳንና ከኣንድ ፖለቲካዊ ሥልጣን የጨበጠ ኃላፊነት የተሸከመ አካል ይቅርና ከተራ ሰውም ልትጠብቀው የምትችል አመለካከት አይደለም።
ይህ አሁን እየተባለ ያለው ነገር ሁሉ እንዳይመጣ ከሚል ገና ከጧቱ ብዙ አዋቂዎች፣ ተቃዋሚ ድርጅቶች እኛም እንደ ትዴት (ታንድ) እና እንደግለሰብም ስናስጠነቅቅና ስናሳስብ ቆይተናል። ለአቶ ዓባይና ለህወሓት መሪዎች የምንጠይቃቸው ለምንድነው ምክሮቹን ልትሰሙ ያልፈለጋችሁት? በኣንጻሩ ግን ለምንድነው ይህንን ምክር ለለገሱላችሁ፣ ፀረ ህዝብ፥ ያማራ ቡችላ፥ ቆሻሾች ወዘተ… እያላችሁ ስም ስታጠፉና ስታሳድዱ የነበራችሁት? እንላቸዋለን።
አሁን ውጥረት ውስጥ ሲገቡ አቶ ዓባይና መሰሎቹ በኢህአዴጎች ውስጥ የነበሩ መሳሳቦችን ምስጢር ማውጣት ጀምረዋል። ለምንድነው ቀደም ብላችሁ ይደረግ የነበረውን ክርክርና ሙግት ህዝብ እንዲያውቀው ይፋ ያላደረጋችሁት? የዚህም ምክንያት በህወሓት ኋላ ቀር ምስጢራዊ አሠራር የተነሣ ነው። የዘረፋችሁትና ያጠፋችሁት እንዳይታወቅባችሁ ለማድረግ የምታደርጉት አካሄድም ነው ብለን እናምናለን። ታዲያ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ራሱ ህወሓት ነው፣ ምክንያቱም ህወሓት መጀመሪያ ላይ ወሳኝ ተራ ስለነበራት በውነት ልትሠራ ብትፈልግ ኖሮ፣ ልታስተካክለውና ትክክለኛ መስመር ልታስይዘው ትችል ስለነበር ነው። የዚህ ሁሉ ድክመትና ምክንያቶች መሠረቱ የህወሓት አመራር ነው። ሌላው ቀርቶ አሁን በሚደረገው የማጥራትና ተሓድሶ ዘመቻ ሳይቀር እንኳን የኋሊት እየሳበና እየጎተተ ያለው የህወሓት አመራር ነው። የፖለቲካ እሥረኞች ይፈቱ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ይስፋ ተብሎ የኦሮሞና የአማራ ክልሎች ተግባራዊ የማድረግ ሥራ በሚያደረጉበት ሁኔታ ላይ፥ በትግራይ ግን የፖለቲካ እሥረኞችን መፍታት አልጀመሩም።
ተቃዋሚዎችንም ሲጋብዙ አልታዩም። ይህንን የለውጥ ሥራ ተግባራዊ እንዳታደርጉ ምንድነው የከለከላችሁ? ባጠቃላይ ሲታይ የህወሓት አመራር ከሚገባው በላይ እንደዛገና ከማስወገድ በቀር ልንጠግነው የሚቻል አለመሆኑን ነው።
ሌላው እዚህ ላይ ሳንጠቅስ ልናልፈው የማይገባ ነጥብ ቢኖር አቶ ዓባይ አንቀጽ 39ኝን ተጠቅሞ መገንጠል መብት እንደሆነ ከገለጸ በኋላ፣ መገንጠል በሃገሪቱ ላይ ስለሚያስከትለው ውድመት ያሳስባል።
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) የመገንጣጠል ጠንቅ ከኢትዮጵያ አልፎም ለመላው የኣፍሪካ ቀንድ ተጽእኖ ከማሳደሩ በላይም አደገኛና የተመሰቃቀለ ውጤት እንደሚኖረው በመገንዘብ አስቀድሞ ፍትሕንና ርትዕን ግቡ ያደረገ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንጂ አንቀጽ 39 መፍትሄ እንደማይሆን አስቀድሞና ደጋግሞ ሲግለጸው የነበረ ጽኑ አቋሙ ስለሆነ እዚህ ላይ ደግመን ዝርዝር ውስጥ መግባቱ አስፈላጊ ሆኖ አይታየንም።
ይሁን እንጂ ህወሓት/ኢህ አዴግ ከዚህ ከሚያጋጥመው ችግር ትምህርት ወስዶ ከሆነና እነኛ አቶ ዓባይ ያቀረባቸው ስጋቶችን ከምር የሚቀበል ከሆነና ለመፍትሄነቱም ከተጋ፣ የተጠቀሰዉን አንቀጽ ጨምሮ ህገ መንግሥታዊ ክለሳ ማካሄድ ለምን ዳገት ሆነበት? እነኛ አቶ ዓባይ በትክክል የገለጻቸው አሉታዊ ውጤቶች ለህወሓት/ኢህአዴግ ግልጽ የሆኑለት ከሆነ፣ መገንጠል እንደ አማራጭ ተደርጎ በህወሓት መሪዎችና ተላላኪዎቻቸው እየተደጋገመ የሚነሳውና የሚበረታታው ያለው ለምንድነው?
እንደ ትግራይ ህዝብ ያለን አማራጭ ከመላው ኢትዮጵያውያን ህዝቦች ጋር ሆነን ህወሓትን በማስወገድ የሚጠቅመንን ድርጅት መደገፍ ወይንም ማቋቋም ነው። ምክንያቱም ትግራይ ከህወሓት አመራር ሌላ ወልዳ እንደመከነች ካልተቆጠረ በስተቀር ከህወሓት ጋር ተጣብቃችሁ ኑሩ ተብሎ ህዝባችን ሊገደድ አይገባም፣ ኣይሆንምም። ስለዚህ ይህን ራሱን በስብሻለሁ ብሎ ያመነ አመራር ራሱን ከገለጽበት የተሻለ አባባል ስለማይኖር፣ ያለፈ የትግል ታሪኮቹን አቅቦ ለተተኪው ወጣት ትውልድ ኃላፊነቱን በሠላማዊና የሠለጠነ መንገድ እንዲያስረክብ አበክረን ማሳሰብ እንፈልጋለን።
ት.ዴ.ት. 25.02.2018