~ለ15 ቀናት እጆቼን የፍጥኝ ታስሬ የተለያዩ ማሰቃያዎች እየተፈፀሙብኝ ቆሻሻ ስበላ ሰንብቻለሁ። ለሁለት ሳምንት የሰው ሽንት የተነከረ ጨርቅ ከአንገት በላይ ፊቴን እንዲሸፍን ተደርጎ ጠልቆልኛል። ለ15 ቀናት እጅና እግሬ ታስሮ፣ ለ360 ሰዓታት ተራ በተራ እየተፈራረቁ ሲደበድቡኝ ሰነበቱ። ደብዳቢዎቼ እየደከማቸው ቢፈራረቁ እኔ የማልቀያየረው በመደንዘዜ እና በመድከሜ ዱላውን ሁሉ እንደአመጣጡ ተቀብያለሁ።
~ጉጠት በሚመስል ነገር የቀኝ እጄን ትንሽ ጣት ጥፍር ነቀሏት። ስቃዩን አልቻልኩትም። ሙሉ ሰውነቴ ተሸነፈ። በደነዘዘው ሰውነቴ፣ በተጎዳው አንደበቴ ያልሰራሁትን ሁሉ “ሰርቻለሁ” ስል አመንኩላቸው።
~በማጎሪያ ቤት ምንም አይነት የመብት ጥያቄ ማንሳት ነውር ነው። የመብት ጥያቄ ያነሳ ውጉዝ ከመ አርዮስ ነው። መነሻው ድብደባ መድረሻው ጨለማ ቤት ነው።
(በአብርሃም ሞገስ)
አብርሃም ሞገስ እባላለሁ። የምፅፈው ሁሉ እውነት በመሆኑ ማንነቴን ሳልፈራ እናገራለሁ። በእርግጥ ትክክል አይደለህም የሚለውን ሁሉ በሚያስር መንግስት ስር የትክክለኛ ሰዎች መገኛ እስር ቤት ይሆናል። በእስር ቤት ስለተገኘሁ ብቻ ትክክል ነኝ ባልልም የምፅፈውና የምኖርበት እውነታ ለእስር አብቅቶኛል።
ዕለቱ ሚያዝያ 29/07 ዓም ጎንደር ሊቦ ከምከም ወረዳ ሀገር አማን ብዬ የተለመደ የሕይወት እንቅስቃሴዬን በማከናውንበት ጊዜ ነበር ድንገት ተይዤ የታሰርኩት። ለ15 ቀናት እጆቼን የፍጥኝ ታስሬ የተለያዩ ማሰቃያዎች እየተፈፀሙብኝ ቆሻሻ ስበላ ሰንብቻለሁ። ለሁለት ሳምንት የሰው ሽንት የተነከረ ጨርቅ ከአንገት በላይ ፊቴን እንዲሸፍን ተደርጎ ጠልቆልኛል። ለ15 ቀናት እጅና እግሬ ታስሮ፣ ለ360 ሰዓታት ተራ በተራ እየተፈራረቁ ሲደበድቡኝ ሰነበቱ። ደብዳቢዎቼ እየደከማቸው ቢፈራረቁ እኔ የማልቀያየረው በመደንዘዜ እና በመድከሜ ዱላውን ሁሉ እንደአመጣጡ ተቀብያለሁ።
ግንቦት 13/07 ዓም 18 ሰዎች በአንድ ወደታጨቁበት ጠባብ ክፍል ተዘዋወርኩ። ሁሉም ” እንኳን ደህና መጣህ” እያሉ ያላቸውን አቀረቡልኝ። እኔም ደስተኛ ነበርኩ። እስር ቤት ውስጥ “እንኳን ደህና መጣህ” መባል ስላቅ ይመስላል፣ ነገር ግን አይደለም። በብርድ ሲንዘፈዘፍ ለነበረ ሰው፣ ቁራጭ ብርድ ልብስ ቢያገኝ ይጠላል? ከነበርኩበት አንፃር አሁን የገባሁበት ክፍል ቢጠብም፣ እስር ቤት ቢሆንም አብረውኝ ሌሎች ሰዎች አሉና የቅንጦት ያህል ነው። መጀመርያ የታሰርኩበት እስር ቤት በደም የተነከረ ፍራሽ፣ ደም ለጣዕኦት የሚቀርብበት ይመስል ነበርና ተስፋ አስቆራጭ ነበር። ለዚህም ነው በጠባቧ ክፍል 18 ሰዎች ሳገኝ በጣም ደስ ያለኝ።
አራት ሰዓት ያህል ያረፍኩ ይመስለኛል። በግምት ከምሽቱ 3 ሰዓት ላይ በሩ ተከፈተ። “አብርሃም ሞገስ” ስሜ ተጠራ። ወጣሁ! በእጆቼ ላይ ካቴና ገባ። ለሌላ ዙር ዱላ ጉዞው ወደቢሮ ቁጥር 30 ሆነ። ለሌላ ዙር ስቃይ። በዱላው መሃል “በተስፋሁን ዘዋለ ተመልምለሃል” ፣ “አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ይዘሃል” የሚሉ ጥያቄዎች ይነሱልኝ ነበር። ያልፈፀምኩትን ፈፅሜያለሁ ማለት አልነበረብኝምና በፅናት ቆየሁ።
ግንቦት 16/2007 ዓም ግን ተረታሁ። ጉጠት በሚመስል ነገር የቀኝ እጄን ትንሽ ጣት ጥፍር ነቀሏት። ስቃዩን አልቻልኩትም። ሙሉ ሰውነቴ ተሸነፈ። በደነዘዘው ሰውነቴ፣ በተጎዳው አንደበቴ ያልሰራሁትን ሁሉ “ሰርቻለሁ” ስል አመንኩላቸው። ዱላ……ስቃይ……ውሸት………ድብቅ ቁስል! የዚህ ስቀይ ከፍታ ስም ማዕከላዊ ነው። ስፍራው ሲኦል ይመስለኛል። መርማሪዎቹ የሰይጣን ጥፍሮች ይመስሉኛል። ስለማዕከላዊ ብዙ ተብሏልና ስለፍርድ ቤቱም ጥቂት ልበል።
የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ሆነው የቀረቡብኝ ደሞዝ የሚቆረጥላቸው፣ ቋሚ የስራ መደብ የተከፈተላቸው ፣ በሀሰት ምስክር የስራ መደብ የሚተዳደሩ ሁለት ግለሰቦች ናቸው። ሁለቱም ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ ነው። ምስክርነት የሚሰጡት በማያውቁት፣ ባልዋሉ ባላደሩበት ሰፈር፣ ጎንደር ውስጥ ተከናወነ ስለተባለ ጉዳይ ነው። ስንታየሁ አንበሴና እንዳለ በርሄ ይባላሉ ምስክሮቹ። የማዕከላዊ የሀሰት የስራ ዘርፍ ዋና የስራ ሂደት ባለቤት ያመጣቸው ናቸው። ቢሮው በይፋ ባይቋቋምም! አዲስ አበባ ሆነው ጎንደርን አይቸዋለሁ ብለው ሲመሰክሩ እንዲህ ነበር። “ከአቶ ተስፋሁን ዘዋለ ጋር የኢትዮጵያ ባንዲራን በድረ ገፅ ይላላካል፣ የግንቦት 7 ባንዲራ ነው የተላላኩት” ብለው መሰከሩ።
ዲሞክራሲ እና ነፃነት በሌለበት ሀገር ትክክለኛ ሰዎች ወህኒ እንደሚገኙ ቀድሞም አውቃለሁ። ይህንን ያወኩት ከ1993 ጀምሮ ይህን ዘውጌ ስርዓት ስቃወም ቆይቻለሁ። የመኢአድ አባል፣ የድርጅቱ የጎንደር ወጣቶች ምክትል ሰብሳቢ ሆኜ አገልግያለሁ። ትግሌን አሁንም እቀጥላለሁ።
እስር የእኔን ሞራል ለማላሸቅ የተጫነብኝ ቀንበር መሆኑን አልስተውም። ያለ ምንም ጥፋት የስርዓቱ አምባገነናዊ ሰለባ የሆኑት እስከ ማበድ ደርሰዋል። ያለ ጥፋት ከመታሰራቸው ባሻገር በፖለቲካ የታሰረ በወንጀለኛ ድንጋጌው የተቀመጠውን “አመክሮ” የማግኘት መብት ተነፍጓል።
“እስረኞች ሰብአዊ መብታቸው ተከብሮ በአግባቡ ተይዘዋል፣ በአግባቡ ምርመራ ይደረጋል” የሚሉ ጆሮ አደንቁር ድስኩሮች ስሰማ በዙሪያየ ያለውን እስረኛ እቃኛለሁ። በደረቅ እንጨት ውስጥ እግርን መግረፍ፣ ጨለማ ቤት መወርወር፣… …እስረኛን በአግባቡ መያዝ ከሆነ፣ ያለ አግባብ ያዝናቸው የሚሉን ምን ቢያደርጉን ነበር?
በማጎሪያ ቤት ምንም አይነት የመብት ጥያቄ ማንሳት ነውር ነው። የመብት ጥያቄ ያነሳ ውጉዝ ከመ አርዮስ ነው። መነሻው ድብደባ መድረሻው ጨለማ ቤት ነው።
ይህ ፅሑፍ የወግ ሽርሽር አይደለም፣ አላማዬ ማዕከላዊና ፍርድ ቤቶች ማስቃኘትም አይደለም። ይህ ፅሑፍ ዱላ ከሚፈጥረው ህመም፣ የጥፍር መነቃል ከሚፈጥረው ስቃይ፣ የመብት ጥሰት ከሚፈጥረው ምሬት፣ በአካል ላይ ከሚታይ ቁስል፣ ቁስል ጥሎ ከሚያልፈው ጠባሳ ባሻገር በውስጥ ተዳፍኖ የሚኖር፣ በግፍ እሳት እየተቆሰቆሰ የሚዘልቅ የድብቅ ቁስልን እንዲያስታውስልኝ ነው። …… ከዘመናት በፊት ስልጣኔ ማማ ላይ የነበረች ሀገር በዘውጌ በትር ስትመታ፣ ሰንደቅ አላማ ትርጉም አልባ ሆኖ የአንድ ድርጅት መገለጫ ሲሆን፣ ስለ እውነት በመታገሌ መሰቃየቴ፣ ድብቅ ቁስሌን ያደማብኛል፣ የድብቅ ቁስሌን ይወጋብኛል።……ግን የነፃነት ትግላችን ጮራ የድብቅ ቁስሌ ላይ ሲበራ ፈውስ እንደማገኝ አምናለሁ!
እግዚያብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
/አብርሃም ሞገስ ይህን ፅሁፍ የፃፈው ከአንድ አመት በፊት በእስር ላይ እያለ ነው። አብርሃም ከሳምንት በፊት የተፈታ ሲሆን ፅሑፉ ፌስቡክ ላይ የወጣው ዛሬ የካቲት 20/2010 ዓም ነው!/