/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ አቶ ሽፈራው ሽጉጤን የድርጅቱ ሊቀ-መንበር አድርጎ ሾመ። የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ላለፉት 21 ቀናት ስብሰባውን ሲያካሂድ ቆይቶ ዛሬ ማምሻውን በፓርቲው ፌስቡክ እንደ አስታወቀው አቶ ሽፈራውን ሊቀ-ምንበር እንዲሁም አቶ ሲራጅ ፈጌሳን ምክትል ሊቀ-መንበር አድርጎ መሾሙን አስታውቋል።
ደኢህዴን ይፋ ባደረገው መግለጫ የድርጅቱ ሊቀ-መንበር ተደርገው የተመረጡት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ እንዲሁም የወቅቱ የክልሉ ፕሬዚዳንት ደሴ ዳልኬ ምክትል ሊ/መንበር አድርጎ እንደመረጠ ይፋ ቢያደርግም “ለውጥ” ተደርጎበት የሚከተለውን ጹሁፉ በፓርቲው ኦፊሺያል የፌስ ቡክ ፔጅ ላይ ይፋ አውጥቷል።
“ማምሻውን የደኢህዴን ማእከላዊ ኮሚቴ ጽሀፈት ቤት በላከልን መግለጫ የጠዋቱ ውሳኔ የመጀመሪያ ዙር ውጤት እንደሆነና በስህተት እንደተላከ በማስታወስ የተስተካከለውን የምርጫ ውጤት አሳውቆናል። በዚህም መሰረት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ሲራጅ ፈጌሳን ደግሞ የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡”የደኢህዴን የምርጫ ውጤት ሲቀየር ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
በሌላ በኩል የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለአርብ አስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቷል።አጀንዳውም የካቲት 9/2010ዓ.ም ጀምሮ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስራ ላይ ያዋለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሆነም ታውቋል።የምክር ቤቱ አባላቱም ከነገ ጀምረው ሪፖርት እንዲያደርጉ ታዘዋል።
ከነገ ወዲያ ሐሙስ ተሰብሶ የፓርቲውን ሊ/መንበርና የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ይመርጣል የተባለው ኢህአዴግ ምክር ቤትም ዴኢህዴን ዘግይቶ በመጨረሱ ምክንያት ከሐሙስ ወደ ቅዳሜ ሊሸጋገር እንደሚችል በስፋት እየተነገረ ነው።