የጽዮን ደጆች… /ታሪኩ ደሳለኝ/

የጽዮን ደጆች… /ታሪኩ ደሳለኝ/

…በምስራቃዊቷ የፍቅር ከተማ (አንጋፋ የዘፈን ግጥም ደራሲያን ሳይቀሩ ለበርካታ ስራዎቻቸው ህያው ገፀ- ባህሪ ባደረጓት) ድሬደዋ ተወልዳ ያደገች ብርቱ ጋዜጠኛ ናት፣ ጽዮን ግርማ።

ጽዮን በምትወደው የጋዜጠኝነት ሙያ ላይ አብሪ ኮከብ መሆን ከቻለች እነሆ አስራ ሦስት አመታትን አስቆጥራለች (የድሬደዋ ሁለተኛ ደረጃ ት/ ቤት ሚኒ ሚዲያ ሲቪዋ ሳይካተት) ። ይህ ሁሉ የድል ጉዞ ግን በቄጤማና ፈንድሻ ብቻ የታጀበ አልነበረም፣ የጥምዝዮሽና የችንካር እንጂ። በመንገዷ የፈተኗትን አያሌ መሰናክሎችን በትዕግስት ብቻ ሳይሆን በዝረራ በማሸነፍ ጭምር ቀጥ ብላ መቆም መቻሏን ደግማ ደጋግማ አሳይታናለች።

ሰሞነኛውን አይነት “ደጆቿ”ን (መርህዎቿን) አንዳንዶች በመሰሪነት፣ ሌሎች ደግሞ በስሁት አረዳድ ለማፈራረስ የተደረጉ ሙከራዎች ሁሉ እንደ ጠዋት ጤዛ ከንቱ ቀርተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለመክሊቷ ምቹ በሆነው ግዙፉ የቪኦኤ ስቱዲዮ ውስጥ አስር ሜትር ረዝማ እያየናት ነው። ይኽም ሆኖ ግን ኑፋቄው አልቀረላትም። ያውም ባልዋለችበት ኩበት የሚያስለቅም።

…ዛሬ ዛሬ እንደ አክሱም ሥልጣኔ፣ እንደ ዛጉዬ ሥረዎ መንግስት በታሪክነት እየተጠቀሰ ባለው ምርጫ 97 ቀውጢ ወቅት የሰራቻቸው ዘገባዎች ምን ያህል ሀቀኝነትን እና ቁርጠኝነትን የተላበሱ እንደነበረ ድፍን የሸገር ሰዎች እና ለንባብ የበቁ ዘገባዎቿ ምስክር ናቸው።

ከጦሰኛው ምርጫ 97 በኋላም ቢሆን በአገዛዙ ቅጥ ያጣ እመቃ ተበግራ ዝም-ጭጭ አላለችም። በፆታ አምሳያዎቿ ዘንድ ያልተሞከረውን አስቸጋሪ እና እንቅፋት የዕለት ቀለቡ የሆነውን የህትመት ሚዲያ ደፍራ በመግባት የግሏን ” እምቢልታ” የተሰኘ ጋዜጣ መስርታ ለንባብ ማብቃቷ በግላጭ የሚታይ እውነታ ነውና (አደራችሁን እዚህ ጋ የሚሚ ስብሃቱን “ኢፍቲን” ጋዜጣ በቀዳሚነት በሴት የተመሰረተ የ”ግል ፕሬስ” ብላችው በመጥቀስ እኔን ብቻ ሳይሆን ማሚቱንም በሳቅ አፍርሳችው ልቧን ቀጥ እንዳታደርጉት)።

የሆነ ሆኖ ፅዮን ግርማ አዲስ አድማስን በአዘጋጅነት ከመምራቷም በላይ ሀገር ቤት እያለችም ሆነ የስደት ዓለሙን ከተቀላቀለች በኃላ የአብዮት አዋላጅ በነበረችው ” ፋክት” መፅሔት ላይ ዛሬም ድረስ ከእልፍ አእላፍቶች ህሊና ያልደበዘዙ፣ ሕዝባዊ ወገንተኝነትን የተላበሱ ጥልቀት ያላቸው መጣጥፎችን በማበርከት እንዳስደመመችን ከቶም ከኔ በላይ ማን ይመስክር!? በነገራችን ላይ ጺዮን የብርሃን ፊርማ የተሰኝ ፊልም በፕሮዲውሰርነትና በፅሀፊነት ስትሰራ እኔ ደግሞ በሲኒማቶግራፈርነት በመስራቴ በቅርብ እንዳውቃት አድርጎኛል።

በመጨረሻም አንድ ምክር ለጓዶች ማካፈልን ወደድኩ፣ እንዲህ የሚል: – ፅዮን ግርማ ከፍ ብላ እየበረረች ነውና በሃሳውያን ስብከት ተታላችው ተው አታሰናክሏት። አበርክቶዋ እውነትንም ፍትሕንም ከማገልገሉም በተጨማሪ የነፃነት መንገዱን አግዞታልና። ከዚህ ባለፈ በተራ ቅናት ተነሳስታችው፣ አሊያም ለአምባ ገነኖች በመወገን ክቡድ መንፈሷን ለማሳደፍ የምትታትሩ እንጀራችሁ ስለሆነ ስለእናንተ አንጨነቅም መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችው። የኔ ምክር ከዚህ አይነቱ እኩይ ምግባር ራሳቸውን ነፃ ላወጡ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ብቻ ነው።

ፅዮን ሆይ እውነት እውነት እልሻለሁ ዛሬም እንደትላንቱ የቆምሽበትን አትልቀቂ-በጣም ልክ ነሽና።

የካቲት 22/2010ዓም

LEAVE A REPLY