/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክ ቲለርሰን ወደ አዲስ አበባ ሊያመሩ ነው ተባለ። ሚስተር ቲለርሰን በመጭው ማክሰኞ (እ፣ኤ.አ 6/2018) ጀምሮ በቻድ፣ ጅቡቱ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ናይጀሪያ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሚሆነውን የስራ ጉብኝታቸውን ለ8 ቀናት እንደሚያከናዉኑ የስቴት ዲፓርትመንት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የየሀገራቱን መሪዎችንና በአዲስ አበባ ከሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ጋር ተገናኝተው ዩናይትድ ስቴትስ ከአፍሪካ ጋር ሲለሚኖራት አጋርነት፣ መልካም አስተዳድርን ስለማስፈን፣ሽብርተኝነትን በመከላከል፣በንግድና ኢንቨስትመንትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚወያዩም ተገልጿል።
የሚስተር ሬክ ቲለርሰን በአፍሪካ የስራ ጉብኝታቸው ወቅት በተለይ በኢትዮጵያ የተከሰተውን የፖለቲካ ቀውስ ትኩረት እንደሰጡት እየተገለጸ ነው።አዲስ ስታንዳርድ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያን የተከሰተውን የፖለቲካ ቀውስ በቅርበት እንደሚከታተለውና በአዲስ አበባ ቆይታቸውም ወቅት ቀውሱን ለመፍታት ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ውይይቶችን በማድረግ ወደ “መሀል” ለማምጣት ነው ተብሏል።
ሚስተር ቴለርሰን ከአቶ ሀይለማርያም ደሳለኝና ከሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናትና ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመገናኘት በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ውጥረትና በመፍትሔው ዙሪያ ለመምከር መርሀ-ግብር መያዙ ታውቋል።
የአሜሪካ መንግስት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ለሁለተኛ ጊዜ ስራ ላይ የዋለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በጽኑ መቃወሙ የሚታወስ ሲሆን የስርዓቱ ባለስልጣናት አምባሳደር ሚካኤል ሬይነርን(በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር) ኤምባሲው ያወጣውን መግለጫ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁ ቢሆንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመቃወም አቋማቸው የጸና መሆኑን ባለፈው ሳምንት መግለፃቸው የሚታወስ ነው።
የዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ ቢን ሱልጣን አል-ናህያን በሚቀጥለው ሰኞ(እ.ኤ.አ መጋቢት 5/2018) እንዲሁም የሩሲያው ውጭ ገዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ሐሙስ መጋቢት 8/2018 የስራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ዛሬ አስታውቋል።